1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ትምህርትኢትዮጵያ

ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ትምህር ቤት የተመለሱ የጎሮዶላ ተማሪዎች

ሥዩም ጌቱ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 14 2017

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን ስር በተዋቀረው ጎሮዶላ ወረዳ በ2016 የትምህርት ዘመን በስፋት የመማር ማስተማር ሂደቱ በመቋረጡ12 ክፍል ብሔራዊ ፈተና ጭምር ሳይሰጥ ቀርቶ ነበር፡፡ በወረዳው በወረዳው የ2017 ትምህርት ቢጀመርም አሁንም ወደ ትምህርት ቤት ያልተመለሱ ተማሪዎች አሉ።

የኦሮሚያ ትምህርት ቢሮ ሎጎ
በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ቦረና ዞን ስር በተዋቀረው ጎሮዶላ ወረዳ ትምህርት ቢጀመርም ሁሉም ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት አልተመለሱም። ምስል Seyoum Getu/DW

ከአንድ ዓመት በኋላ ወደ ትምህር ቤት የተመለሱ የጎሮዶላ ተማሪዎች

This browser does not support the audio element.

“ይህ የመዋቅር ችግር በ2015 መጨረሻ አከባቢ ካጋጠመን ወዲህ በተለይም ባለፈው ዓመት ትምህርት አቋርጠናል፡፡ እኔም አምና ካቋረጥኩ በኋላ አሁንም አልተመለስኩበትም፡፡ አሁንም ህብረተሰቡ ጥያቄውን በመቀጠሉ አይረጋጋም ብዬ ነው ፈርቼ ከ11ኛ ክፍል የተውኩት፡፡ አምና ከዚህ ወረዳ ውጪ ሄደው ትምህርታቸውን የተከታተሉ ጓደኞቼ ነበሩ፡፡ እኔ ግን በገቢ ችግር ምክንያት ለማቋረት ተገደድኩ፡፡ ዘንድሮ ደግሞ እዚህም ስጀመር አንዴ ጓደኞቼ ጥለውኝ አልፈዋል ብዬ ለስነልቦናዬ ስላልተስማማን አቋረጥኩ በቃ” ሲል አስተያየቱን ያጋራን አምና ከ11ኛ ክፍል ትምህርቱን እንዳቋረጠ አሁንም ድረስ ወደ ትምህርት ቤት ደጃፍ ያልተመለሰው የጎሮዶላ ወረዳ ተማሪ ነው፡፡

ይህ ተመማሪ አሁን ላይ ከትምህርቱም ከስራም ሳይሆን እንዲሁ መቀመጡንም በአስተያየቱ አመልክቷል፡፡

በወረዳው የትምህርት በተሻለ መልኩ መቀጠል

ሌሎች አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ ተማሪዎች እና የተማሪ ቤተሰቦች ግን በዘንድሮ የትምህርት ዘምን ከአምናው ሻል ባለ ሁኔታ የመማር ማስተማር ሂደቱ መጀመሩን አስረድተዋል፡፡ “አሁን ትምህርት ተጀምሯል፡፡ በርግጥ እንደ ሌላው ጊዜ በመደበኛነት ሁሉም የአከባቢው ልጆች ወደ ትምህርት ቤት አምርተው ባይሆንም ትምህርት እየተሰጠ ነው”ሲሉም ሀሳባቸውን ገልጸዋል፡፡

ትምህርት ያልተጀመረበት ጎሮዶላ ወረዳ

በ2015 ዓ.ም. ሚያዚያ ወር ኦሮሚያ ክልል ይፋ ባደረገው የዞን እና ከተማ አስተዳደሮች መዋቅር ተከትሎ ህዝባዊ ቅሬታ በማስነሳቱ አለመረጋጋት የተሳነው ይህ ቀደም ሲል በጉጂ ዞን ይተዳደር የነበረው የጎሮዶላ ወረዳ አዲሱን መዋቅር አንቀበልም በሚል መረጋጋት ተስኖት ቆይቷል፡፡ በዚህም በ2016 ዓ.ም. በወረዳው የመማር ማስተማር ሂደቱ በስፋት በመስተጓጎሉ የ12ኛ ክፍል ብሔራዊ ፈተናም ሳይሰጥመቅረቱ ይታወሳል፡፡

የተማሪ ወላጅ የሆኑት የአከባቢው ነዋሪ እንደሚሉት ዘንድሮ ግን ትምህርት የግድ ከተቋረጠበት እንዲቀጥል የሆነው ማህበረሰቡ ትምህርት የማቋረጥ ተጽእኖን በመገንዘቡ ነው፡፡ “ያለው ችግር እልባት ባያገኝም ተማሪ ጥያቄውን መጠየቅ ያለበት እየተማረ እንጂ ትምህርት ማቋረት ብዙ ችግር ሊያመጣ ይችላል የሚል መደምደሚያ ላይ በመደረሱ ነው፡፡ አምና እንኳ በትምህርት መቋረጥ ምክንያት ብዙ ተጽእኖ ተማሪዎች ላይ ደርሷል፡፡ ወደ ትምህርት ቤት መሄድ ያቆሙ ተማሪዎች ለያለ እድሜ ጋብቻ በስፋት ተዳርገዋል፡፡

አንድ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የጎሮዶላ ወረዳ ባለሥልጣን በአካባቢው ትምህርት በመቋረጡ ወደ 2000 ተማሪዎች እድሜያቸው ሳይደርስ ማግባታቸውን ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በአከባቢው የጸጥታ ችግርም ስላለ ትምህርት ካቋረጡት ውስጥ በአከባቢው ወደ ሚንቀሳቀሱ ሸማቂዎችም የተቀላቀሉ አሉ፡፡ ከዚህ ውስብስብ ችግር የተነሳም የተማሪዎች ወላጆች ተማሪዎች ወደ ትምህርት ገበታቸው እንዲመለሱ ያላሰለሰ ጥረት አድርገዋል”ብለዋል፡፡

ሌላም የአከባቢው ነዋሪ የተማሪ ወላጅ አስተያየታቸውን ሲያክሉ፤ “አምና ተማሪው ትምህርቱን ሲያቋርጥ የነበረው ጥያቄ መንግስት ከመዋቅር ጋር ተያይዞ ላነሳነው ጉዳይ ምላሽ እስካልሰጠን ድረስ ወደ ትምህርት አንመለስም የሚል ሃሳብ ነበር የትምህርት ማህበረሰቡ ጋር፡፡ ዘንድሮ ግን በአገር ሽማግሌዎች፣ የሃይማኖት አባቶች እና አባገዳዎች ምክር ይህ ነገር ትውልድን ወደ በጎ አያመራም የሚል ተመክሮበት ተማሪው ወደ ትምህርት ገበታው እንዲመለስ ተደርጓል፡፡ ተማሪውም ማንነታችንን ያከበረ መዋቅር እንዲዘረጋ መጠየቃችን እየቀጠልን የሚል ቃል ሰጥተው ምክሩን ተቀብለው በብዛት ወደ ትምህርት ቤት ተመልሰዋል” ነው ያሉት፡፡

በምስራቅ ቦረና፤ ጎሮዶላ የተማሪዎች ተቃውሞ እስር

አስተያየት ሰጪዋ የአከባቢው ነዋሪ ሀሳባቸውን ቀጠሉ፤ “አሁንም ግን ስጋቶች አሉ፡፡ አሁን ትናንት በአከባቢው የምስራቅ ቦረና የሚል ታፔላ ይቁም ስባት ተማሪዎች ተቃውመው ረብሸው ነበር፡፡ ያለው ስሜት አሁንም ጥሩ እንዳልሆነ በዚሁ ትረዳለህ፡፡ ያ ሲሆን ትምህርት እንዳይቋረጥ እንሰጋለን” ብለዋል፡፡

ተቋርጦ የነበረው ትምህርት ያስከተለው ማህበራዊ ጉዳት

ከሁሉ በላይ ደግሞ በትምህርት መቋረጥ ምክንያት የተከሰተው ማህበራዊ ቀውስ ወላጆችን ያሰጋው ትልቁ ጉዳይ ሆኗል፡፡ “ለምሳሌ ከኔው ቤተሰብ በ15 ዓመታ የተዳረች ልጅ አለች፡፡ በ17 ዓመቱ ያገባ ልጅም አለ፡፡ ይህ የአምናው ትምህርት የመቋረጥ ተጽእኖ ነው፡፡ እነዚህ ልጆች አሁን ለራሳቸው ልጅ ናቸውና እንዴት ቤተሰብ አፍርተው ሊያስተዳድሩ ይችላሉ” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡

የጉጂ ዞን ከፍተኛ የጸጥታ ችግር ውስጥ የቆየ አካባቢ ነው ምስል Private

በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ቦረና ዞን የተማሪዎች ጥያቄ

በወረዳው ይህ ጉዳይ የሚመለከታቸው ግን ደግሞ አለብኝ ባሉት የጸጥታ ስጋት ማንነታቸውን ከመግለጽ ተቆጥበው አስተያየታቸውን የሰጡን የአከባቢው ባለስልጣን ባለፈው ዓመት በተቋረጠው የመማር ማስተማር ሂደት ምክንያት ወደ 2000 ተማሪዎች እድሜያቸው ሳይደርስ ለጋብቻ ተዳርገዋል ነው ያሉት፡፡ አዲሱ የዞን መዋቅር ወደ አከባቢው እንዲተገበር ጫና ከተደረገ ወዲህ ከፍተኛ ያሉት ማህበራዊ ምስቅልቅሎች መከሰታውን የገለጹት የአከባቢ ባለስልጣን አምና የሁሉም መንግስታዊ መዋቅር በተለይም እነደ ጤና እና ትምህርት ያሉ አገልግሎቶች ተስተጓጉለው መቆየታቸውን አስረድተዋል፡፡

በማህበረሰቡ ግፊት ዘንድሮ በተሻለ መልኩ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤት ብመለሱም አሁንም ወደ ትምህርት ቤት የተመለሰው የተማሪ ቁጥር ግን አመርቂ አለመሆኑንም ጠቁመዋል፡፡ “በወረዳው ባሉ 84 ትምህርት ቤቶች ውስጥ በ2015 ዓ.ም. ከ52 ሺኅ በላይ ተማሪዎች ነበሩ፡፡ አምና ትምህርት ባለመኖሩ ወደ ሸማቂዎች የተቀላቀሉና ለያለእድሜ ጋብቻ የተዳረጉ ብዙ ተማሪዎች አሉ፡፡ ቤተሰቦቻቸው አቅም ያላቸውና ወደ አጎራባች ወረዳዎች ልከው ያስተማሩም ነበር፡፡ ግን እነዚያም ልጆች ስለሆኑ ከቤተሰቦቻቸው ስለዩ ለተለያዩ ስነልቦና ጉዳቶች የተዳረጉ ነበር፡፡ አሁን ትምህርት በወረዳው ስጀመር ቁጥሩ መጨመር ስገባው 20 ሺህ ገደማ ነው ወደ ትምህርት የተመለሰው፡፡ ቀሪው 30 ሺህ ገደማስ ብባል መልስ የለንም” ብለዋል፡፡

ሥዩም ጌቱ

እሸቴ በቀለ

ማንተጋፍቶት ስለሺ  

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW