1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ምርጫ ምን ይጠበቃል?

ማክሰኞ፣ ግንቦት 27 2016

ለአራት ቀናት በአውሮጳ ኅብረት አባል ሀገራት የሚካሄደው ይህ ምርጫ ከቀድሞዎቹ የምክር ቤት ምርጫዎች በተለየ ትኩረት ስቧል። ውጤቱም አጓጊ ሆኗል። ምክንያቶቹም በተለይ ካለፉት አራትና ሦስት ዓመታት ወዲህ አውሮጳን ጨምሮ በዓለማችን የተከሰቱ ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ለውጦች በምርጫው ውጤት ላይ ሊያሳድሩ የሚችሏቸው ተጽእኖዎች ናቸው ።

በቡዳፔስት የኦርባን ደጋፊዎች ሰልፍ
በቡዳፔስት የኦርባን ደጋፊዎች ሰልፍምስል Bernadett Szabo/REUTERS

ከአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ምርጫ ምን ይጠበቃል?

This browser does not support the audio element.

የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ምርጫ ሊካሄድ በጣት የሚቆጠሩ ቀናት ቀርተውታል። የአሁኑ ምርጫ ከከዚህ ቀደሞቹ በተለየ ትኩረት ስቧል።በምርጫ አብላጫውን የምክር ቤት መቀመጫ ያሸንፋሉ ተብለው ያሰጉት ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተለያዩ የአውሮጳ ዋና ዋና ከተሞች ጠንከር ያሉ የምርጫ ዘመቻዎች አካሂደዋል። የአውሮጳ ኅብረት ፓርላማ ምርጫ ከህንድ አጠቃላይ ምርጫ ቀጥሎ በዓለም ሁለተኛ ደረጃን የሚይዝ የዴሞክራሲ መገለጫ ይባላል። ከጎርጎሮሳዊው ሰኔ 6 ቀን አንስቶ እስከ ሰኔ ዘጠኝ ቀን በሚካሄደው ምርጫ 450 ሚሊዮን ከሚጠጉ የህብረቱ አባል ሀገራት ዜጎች ወደ 370 ሚሊዮኑ ለመምረጥ ተመዝገበዋል።በአውሮጳ የስደተኞች ቁጥር መጨመር በአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ምርጫ ላይ ሊያሳድር የሚችለው ተጽእኖ

ዜጎች ይህን አጋጣሚ በመጠቀም መጻኤ እድላቸውን ለመወሰን ድምጻቸውን እንዲሰጡ በምርጫ ዘመቻ ወቅት ከተለያዩ ፓርቲዎች ጥሪዎች ቀርበውላቸዋል ። ከመካከላቸው ባለፈው ሳምንት መጨረሻ በተለያዩ የኅብረቱ አባል ሀገራት ዋና ከተሞች በተካሄዱ ሰልፎች ላይ ፖለቲከኞች የህዝቡን ቀልብ ለመሳብ ያካሄዷቸው ቅስቀሳዎች ይገኙበታል።  የፍልሰት ደንብንና ኅብረቱ ለዩክሬኑ ጦርነት በቢሊዮኖች ዩሮ የሚቆጠር ገንዘብ መስጠቱን ጨምሮ ሌሎች የኅብረቱን ፖሊሲዎች የሚቃወሙት የሀንጋሪው ፕሬዝዳንት ቪክቶር ኦርባን የሀንጋሪ ዜጎች  መንግሥታቸውን ከደገፉ ሀገራቸው በዩክሬን ጦርነት ተሳታፊ አትሆንም ሲሉ ቃል ገብተውላቸዋል። 14 ዓመት በስልጣን ላይ የቆዩት ኦርባን ባለፈው ቅዳሜ በዋና ከተማይቱ በቡዳፔስት በተጠራ ሰልፍ ላይ  ባሰሙት ንግግር በአውሮጳ የሚጎሰመውን የጦርነት ነጋሪት እናስቁም በማለት ለህዝባቸው ጥሪ አቅርበዋል።  
«አውሮፓ ዛሬ ለጦርነት እየተዘጋጀች ነው።  ወደ ሲኦል የሚወስደው መንገድ የሌላኛው ክፍል ርክክብ በየቀኑ እየተነገረ ነው። በየቀኑ በመቶ ቢሊዮኖች የሚቆጠር ዩሮ ለዩክሬን ስለመስጠት ፣በመሀል አውሮፓ የኒዩክልየር ጦር መሣሪያዎችን ስለማሸጋገር ፣ ወንዶች ልጆቻችንን በውጭ ጦር ውስጥ ማስመዝገብ፣ በዩክሬን የኔቶ ተልዕኮ እና ለዩክሬን የአውሮፓ ጦር ኃይል ክፍሎች  በየቀኑ የሚናገሩት ነው።ወዳጆቼ !ጦርነትን የሚደግፈው ባቡር ፍሬን የለውም፤ሾፌሩም አብዷል። በአውሮጳ ምክር ቤት ምርጫ ይህን ባቡር ከማስቆም በስተቀር ሌላ ተግባር አይኖረንም።» ኦርባንና ፓርቲያቸው ፊዴስጥ ከኅብረቱ አባል ሀገራት የሩስያና የፕሬዝዳንቷ የቭላድሚር ፑቲን የቅርብ ወዳጅ የሚባሉ ናቸው። ሀንጋሪ ከሩስያ ጋር ጦርነት ለምታካሂደው ለጎረቤቷ ዩክሬን  የጦር መሳሪያ ድጋፍ መሰጠቱን ትቃወማለች። ለዩክሬን የሚሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ ለማደናቀፍና እና በሞስኮ ላይ የሚጣሉ ማዕቀቦችንም ለማስቆም ስትዝት የቆየችም ሀገር ናት።

የኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅዮ ሜሎኒና የሀንጋሪው ፕሬዝዳንት ቪክቶር ኦርባንምስል Attila Kisbenedek/AFP/Getty Images

 ከሳምንቱ መጨረሻ የምርጫ ቅስቀሳዎች ሳንወጣ በጣልያን በተካሄደው የመጨረሻው የምርጫ ዘመቻ ላይ «ብራዘርስ ኦፍ ኢታሊ» ወይም «የኢጣልያ ወንድማማቾች» የተባለው የቀኝ ክንፍ ፓርቲ መሪ የኢጣልያ ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጅዮ ሜሎኒ ባሰሙት ንግግር በተለይ ፓርቲያቸው በሚቃወመው ሕገ ወጥ በሚባለው ስደት ኢጣልያ መቸገሯን ለማስቆም ወሳኙ መራጩ ህዝብ መሆኑን አበክረው ተናግረዋል።
«ውጤታማ ባልሆነው ፍልሰተኞችን በሌላ አካባቢ ስለማስፈር እና ወደ ሀገራችን ማን ይግባ አይግባ የሚለውን ህገ ወጥ የሰዎች አዛዋሪዎች እንዲወስኑ ስለመፍቀድ መፈላሰፍ ወይስ ሕገ ወጡን ጉዞ አስቁመን በሕገ ወጥ መንገድ የመጡትን መመለስ። አውሮጳ ቁጥጥር በማይደረግበት ፍልሰት መሰቃየቷ መቀጠል አለመቀጠሉን መወሰን የናንተ ድርሻ ነው። »ጀርመናዊትዋ የመከላከያ ሚኒስትር ለአውሮጳ ኮሚሽን ፕሬዚደንትነት ታጩ


ባለፈው ሳምንት በጀርመን ይፋዊ ጉብኝት ያደረጉት ከአውሮፓ ኅብረት አንቀሳቃሽ ሞተሮች አንዷ የሆነችው የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ የምስራቅ ጀርመንዋን ከተማ ድሬስደንን በጎበኙት ወቅት  ህዝቡ የቀኝ ጽንፈኞችን የታመመ መንፈስ ለመከላከል እንዲነቃ ጥሪ አቅርበው ነበር።
 

የፈረንሳይ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮ በድሬስደን ጀርመንምስል Annegret Hilse/REUTERS

«ዴሞክራሲዎቻችን ባሉበት ጽንፈኞች የሚያነሷቸው ሀሳቦች ያብባሉ።በተለይም የቀኝ ጽንፈኞች ሀሳቦች፤ ይህ የታመመ ነፋስ በመላው አውሮጳ እየነፈሰ ነው። ይህ እውነታ ነው። ስለዚህ እንንቃ።»    
ለአራት ቀናት በአባል ሀገራት የሚካሄደው ይህ ምርጫ ከቀድሞዎቹ የምክር ቤት ምርጫዎች በተለየ ትኩረት ስቧል። ውጤቱም አጓጊ ሆኗል። የዶቼቬለ የብራሰልስ ዘጋቢ ገበያው ንጉሴ ምክንያቶቹ በተለይ ካለፉት አራትና ሦስት ዓመታት ወዲህ አውሮጳን ጨምሮ በዓለማችን የተከሰቱ ማኅበራዊ ፖለቲካዊና ኤኮኖሚያዊ ለውጦች ናቸው ይላል። በነዚህ ተመሳሳይ ምክንያቶች የጀርመን የፖለቲካ ፓርቲዎችም በዚሁ ተጽእኖዎች ስር መውደቃቸውን ነው የበርሊኑ ወኪላችን ይልማ ኃይለ ሚካኤልም ያስረዳው።በመጪው እሁድ በሚጀመረው የአውሮጳ ኅብረት ምክር ቤት ምርጫ የፈረንሳይ የጀርመንና የሌሎች የኅብረቱ አባል ሀገራት ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲዎች ከከዚህ ቀደሙ የበለጠ መቀመጫ ያገኛሉ ተብሎ ይጠበቃል። ይሁንና የጀርመኑ ቀኝ ጽንፈኛ ፓርቲ«አማራጭ ለጀርመን»በቅርብ ጊዜያት የፖለቲከኞቹ ንግግሮችና ድርጊቶች መንስኤ የፈረንሳይና የጣልያን ቀኝ ጽንፈኞች ከሚገኙበት ኅብረት መባረሩ የቀድሞውን ትንበያ ቀይሮታል።

የአውሮጳ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርዙላ ፎን ዴር ላየንምስል Mohamed Azakir/REUTERS

 
 በአሁኑ የአውሮጳ ፓርላማ ምርጫ በፓርላማው የእስካሁኑ የኅብረቱ አባል ሀገራት የኃይል አሰላለፍ ሊለይ ይችላል የሚል ግምት አለ ። የአሁኑ የኅብረቱ ኮሚሽን ኮሚሽነር ኡርዙላ ፎን ዴር ላየን በህብረቱ ኮሚሽን ፕሬዝዳንትነት ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን መመረጥ መቻል አለመቻላቸው ከምርጫው አጓጊ ገጽታዎች አንዱ ነው። ፎን ዴር ላየን ለመመረጥ  ከ27 የኅብረቱ አባል ሀገራት መሪዎች የአብዛኛዎቹን ድጋፍ ማግኘት ይጠበቅባቸዋል።  ከፓርላማው 720 አባላት አባላት ቢያንስ የ361ዱን ድምጽ ማግኘትም አለባቸው። የምርጫ ቅስቀሳቸው በምርጫው ሊቀየር ይችላል የተባለው የኃይል አሰላለፍ ተጽእኖ ሳያደርግባቸው መቀጠል የሚችሉበትን መንገድ የሚያመቻች ነበርየአውሮጳ ሕብረት መሪዎች ምርጫ

በአባል ሀገራት የህዝብ ብዛት መሠረት ከሚከፋፈለው የምክር ቤቱ 720 መቀመጫ 97ቱ የጀርመን ነው ። በጀርመን ህዝቡ ለምርጫው እንዲወጣ ቅስቀሳዎች ቢካሄዱም መምረጥ ከሚችሉት ዜጎች ጥቂት የማይባሉ ድምጽ ለመስጠት ፈቃደኛ አለመሆናቸው አሳስቧል። ከ10 ጀርመናውያን አራቱ ለምርጫ እንደማይወጡ በቅርቡ ARD የተባለው የጀርመን መገናኛ ብዙሀን ባካሄደው የአስተያየት መመዘኛ ማወቁን ዘግቧል። 

 

ኂሩት መለሰ

ሸዋዬ ለገሠ 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW