ከአዲሱ የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ነዋሪዎች ምን ይጠብቃሉ?
ረቡዕ፣ ሚያዝያ 1 2017
ከደም አፋሳሹ ጦርነት ማግስት በከባድ ፖለቲካዊ ሁኔታ ውስጥ ባለችው ትግራይ ክልል ሥራ ላይ የቆየው ጊዜያዊ አስተዳደር ትናንት አዲስ ፕሬዝደንት ተሹሞለታል። የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ የሆኑት እና ላለፉት ሁለት ዓመታት ጊዜያዊ አስተዳደሩን በምክትል ፕሬዝደንት መዐረግ ሲመሩ የቆዩት ጀነራል ታደሰ ወረደ ለአንድ ዓመት ይቆያል የተባለው ጊዜያዊ አስተዳደርን ሊመሩ ሥልጣን ተረክበዋል። ጀነራል ታደሰ ወረደ ከሕገመንግሥት እና የፕሪቶርያ ውል ያፈነገጡ የተባሉ እንቅስቃሴዎችን ለማስቆም መስማማታቸውን የተሰራጨ «የትግራይ ክልል አካታች ጊዜያዊ አስተዳደር የተልዕኮ አፈፃፀም የቃል ኪዳን ሰነድ» የተሰኘ ባለስምንት ነጥብ ጽሑፍ ያመለክታል።
በተጨማሪም ተፈናቃዮችን የመመለስ ተግባርም ቀዳሚ ሥራቸው እንደሚሆን ተገልጿል። ከዚህም ሌላ ክልሉን ለዴሞክራሲያዊ ምርጫ እንዲያዘጋጁ፣ የክልሉ ሕዝብም በሀገራዊ ምክክር መድረክ እንዲሳተፍ እንዲያደርጉ፣ ትጥቅ የመፍታት እና የቀድሞ ተዋጊዎችን ወደ ሰላማዊ ሕይወት የመመለስ ሥራ በአፋጣኝ እንዲፈፀሙ ማድረግ የሚሉ ነጥቦች ተካተውበታል።
ለቀጣይ አንድ ዓመት የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደርን እንዲመሩ ከአቶ ጌታቸው ረዳ ሥልጣን የተረከቡት የትግራይ ኃይሎች ዋና አዛዥ እና አዲሱ የክልሉ ፕሬዝደንት ጀነራል ታደሰ ወረደ፥ በክልሉ ካለው የተወሳሰበ ሁኔታ አንፃር የተረከቡት ሀላፊነት ከባድ ቢሆንም፥ ከተሠራበት ደግሞእንደመልካም አጋጣሚ የሚታይ መሆኑን ትናንት ባደረጉት ንግግር ገልፀዋል። በአዲሱ ፕሬዝደንት ሹመት ጉዳይ በትግራይ የተለያዩ አስተያየቶች እየተሰጡ ሲሆን ያነጋገርኛቸው የክልሉ ነዋሪዎች እንደ አዲስ ወደ ሥራ ከሚገባው ጊዜያዊ አስተዳደር በዋነኝነት ሰላም ማረጋገጥ፣ ለተፈናቃዮች ጉዳይ መቋጫ መስጠት እና ኢኮኖሚ የሚነቃቃበትን ሁኔታ ማመቻቸት የመሳሰሉ ተግባራትን ይጠብዋሉ። ይህ በእንዲህ እንዳለ ጀነራል ታደሰ ወረዳ ካቢኔያቸውን በቅርቡ እንደሚያሳውቁ ይጠበቃል።
ሚሊየን ኃይለ ሥላሴ
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ