ከአገልግሎት በኃላ የሚጣሉ ፕላስቲክ ኮዳዎች ለዳግም አገልግሎት
ረቡዕ፣ ግንቦት 16 2015
በድሬደዋ አብዛኛው ነዋሪ ዘንድ በስፋት ጥቅም ላይ የሚውሉ የታሸጉ ውኃን የሚይዙ ፕላስቲክ ኮዳዎች ከአገልግሎት በኃላ እዚህም እዚያም በመጣላቸው ሳቢያ የከተማዋ የፍሳሽ መውረጃዎችን ከመድፈን ባለፈ ወደ ዋባ ዋና መንገዶች ወጥተው በገፅታዋ ላይ እየፈጠሩ ያሉትን አሉታዊ ተፅዕኖ መታዘብ ብዙም ከባድ አይደለም።
እስቀ ቅርብ ጊዜ የከተማዋን አካባቢ የገፀ ምድር መልክ ከማበላሸት ባለፈ አካባቢን በመበከል ዘርፈ ብዙ ችግር እያስከተሉ የሚገኙ ያገለገሉ የፕላስቲክ ኮዳዎች ግን ዛሬ መፍትሄ እያገኙ ያሉ ይመስላል። በእለቱ የአካባቢ እና ሳይንስ መሰናዶ ለእዚህ መሰል ችግሮች እየተከናወኑ ያሉ ጥረቶችን እንዳስሳለን።
ከአገልግሎት በኃላ የሚጣሉቱ ፕላስቲኮች መበራከት ዋነኛው መንስዔ ለሌላ ግልጋሎት አለመዋል ወይም እንዲውሉ ማድረግ የሚያስችል ፋብሪካ አለመኖር ነው። እስከ ቅርብ ጊዜ ችግር ሆነው የቆዩትን አገልግለው የሚጣሉ ፕላስቲክ ዉኃ መያዣዎች ግብዓት አድርገው ለሌላ አገልግሎት እንዲውሉ የሚያደርጉት ፋብሪካዎች ወደ ስራ መግባትን ተከትሎ በርካቶች እነዚህን የወዳደቁ ፕላስቲኮች ሰብስቦ ወደ ገቢ መቀየር ስራ ላይ ተጠምደዋል።
ብዙዎች ወደ ዘርፉ ዓይናቸውን ከመጣላቸው ቀደም ብሎ ስራውን ይሰራ እንደነበር የሚናገረው አቶ ጀማል መሀመድ ከዚህ አንዱ ምስክር ነው። "በወቀቱ የምሰራው ስራ የእብደት ይመስላቸው የነበሩ ሰዎች ነበሩ" ይላል- ስለ ጅማሮው ሲናገር። ሌላኛው አስተያየት ሰጪ ወጣት እንድሪስ ዘርፉ ስራ እንደፈጠረለት በመግለፅ ስራው ባይፈጠር "የጎዳና ህይወት እንመራ" ነበር ሲል አስተያየቱን ሰጥቷል።
አቶ ሙሀባ እነዚህ ከከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚሰስሰቡ ያገለገሉ ፕላስቲኮች በሺያጭ የሚሰባሰቡበት አሸዋ ዳርቻ በስራ ላይ ያገኘነው ነው። እሱም ስለስራው ተከታዩን አስተያያት አክሏል። በስራው ላይ ተሽከርካሪ ላይ የመጫን እና የማውረድ ስራን እንደሚሰራ ያጫወተን ሌላኛው አስተያየት ሰጭ ቀደም ሲል የከተማዋን አካባቢ አስቀያሚ አድርጎ የቆየው ያገለገሉ ፕላስቲክክች ክምችት ዛሬ የስራ እድል መፍጠሩን ይገልፃል።
ከጎዳና ህይወት መውጣቱን የነገሩን ወጣት እንድሪስ እየሰራ ባለው ስራ ደስተኛ መሆኑን ለፕሮግራማችን በሰጠው አስተያየት ጠቁሟል። በድሬደዋ በቅርቡ ወደ ስራ የገባውን ጨምሮ በሌሎች ሀገሪቱ አካባቢዎች ብቅ ማለት የጀመሩ እና እነዚህን የወዳደቁ ፕላስቲኮች መልሶ ለሌላ አገልግሎት ለማዋል የሚያስችል ስራን የሚሰሩ ፋብሪካዎች መፍትሄ መሆናቸውን በመግለፅ በቅርቡ በድሬደዋ ያቋቋሙትን ኤም አይ ጂ የተሰኘው ፋብሪካ በአብነት የጠቀሱልን የፋብሪካው ባልደረባ ናቸው።
ለኤም አይጂ በግብዓትነት የሚያገለግሉትን ያገለገሉ ፕላስቲኮችን ስለማሰባሰብ ስራቸውም ተከታዩን ብለዋል። አቶ ደረጀ አቢቲ በድሬደዋ አካባቢ ደንና አየር ንብረት ባለስልጣን የአካባቢ ህግ ተከባሪነት እና የፕሮጀክቶች ተፅዕኖ ግምገማ ቡድን መሪ ናቸው። ባለሞያው እነዚህ የወዳደቁ ያገለገሉ ፕላስቲኮች በአካባቢ ላይ ስለሚኖራቸው ተፅዕኖ ነግረውናል።
በዘርፉ የተሰማሩ አምራች ድርጅቶች ምርቶችን በተለይም የዉኃ ማሸጊያዎችን ደረጃቸውን እብዲጠብቁ ከማድረግ ባለፈ አገልግለው በአግባቡ እንዲጣሉ በማድረግ በኩልም ኃላፊነት እንዳለባቸው አስረድተዋል። እርሳቸው እንዲህ ይበሉ እንጂ እስካሁን አተገባበሩ እንዲያ ነው ለማለት የሚያስደፍሩ ነገሮች ብዙ አይዱሉም።
አቶ ደረጀ በድሬደዋ በስፋት ይታይ የነበረውን ችግር ለመፍታት በአሁን ሰዓት እየተከናወነ ስላለው እንቅስቃሴም ተከታዩን ብለዋል። በአሁኑ ሰዓት በድሬደዋ በርካታ ሰዎች በዚህ አገልግለው የተጣሉ ፕላስቲኮችን አሰባስቦ ወደ ገንዘብ በመቀየር ስራ ላይ በስፋት ተሰማርተው ይታያሉ። ከየአካባቢው ተሰባስበው የመጡ ፕላስቲኮችን በስፋት የሚገዙ አካላት በድሬደዋ እና ከድሬደዋ ውጭ ፍላጎቱ ላላቸው ፋብሪካዎች እያቀረቡ መሆባቸውን ተመልክተናል።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በድሬደዋ የተጀመረው ይህ ጥረት በዚሁ መልክ የቀጠለ እንደሆን የከተማዋን ገፅታ አጥፍቶ የነበረው ሁኔታ ለአንዴ እና ለመጨረሻ እንዲያበቃ የሚያደርግ በጎ ተግባር እንደሚሆን አያጠራጥርም።
መሳይ ተክሉ
አዜብ ታደሰ