1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ከአፍሪቃ የዘር ሐረግ የሚመዘዙት ድንቅ የአውሮጳ ተጨዋቾች

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 6 2016

በእሁዱ የዩሮ 2024 የፍጻሜ ጨዋታ ስፔን እንግሊዝን ትገጥማለች ። ከአፍሪቃ የዘር ሐረግ የሚመዘዙት እንደ ላሚን ያማል፣ ኒኮ ዊሊያምስ እና ቡካዮ ሳካ ያሉ ተጫዋቾችም ውድድሩን አድምቀዋል ። በእሁዱ የፍጻሜ ፍልሚያ የትኛውም ቡድን የአሸናፊነት ክብሩን ይቀዳጅ ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ ግን ማንነታቸውን ከወዲሁ አስመስክረዋል ።

አዳጊው ላሚን ያማል ባቆጠረው ድንቅ ግቡ ስፔንን ለፍጻሜ አብቅቷል
አዳጊው ላሚን ያማል ባቆጠረው ድንቅ ግቡ ስፔንን ለፍጻሜ አብቅቷልምስል፦ Manuel Blondeau/AOP.Press/IMAGO

አፍሪቃ፦ የእግር ኳስ ጠቢባን መፍለቂያ

This browser does not support the audio element.

«ዩሮ 2024፦ አፍሪቃ የእግር ኳስ ጠቢባን ሲራቀቁ ዕያየች ነው» ይለናል በካይ ኔቤ የቀረበው ዘገባ ። እንደሚከተለው ለአድማጭ በሚመች መልኩ አሰናድተነዋል ።

በእሁዱ የዩሮ 2024 የፍጻሜ ጨዋታ ስፔን እንግሊዝን ትገጥማለች ። ከአፍሪቃ የዘር ሐረግ የሚመዘዙት እንደ ላሚን ያማል፣ ኒኮ ዊሊያምስ እና ቡካዮ ሳካ ያሉ ተጫዋቾችም ውድድሩን አድምቀዋል ። በእሁዱ የፍጻሜ ፍልሚያ የትኛውም ቡድን የአሸናፊነት ክብሩን ይቀዳጅ ላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ ግን ማንነታቸውን ከወዲሁ አስመስክረዋል ።

ሁለቱ የስፔን ብሔራዊ የእግር ኳስ ቡድን የክንፍ ተጨዋቾች  በዩሮ 2024 ግጥሚያ  እንዲያቆሟቸው የተመደቡ የየትኛውም ሀገር ተከላካዮች ፈርዶባቸዋል ማለት ይቻላል ። የፍጻሜ ግጥሚያው እስከተደረገበት ቀን አንድ ቀን ድረስ ከ16ኛ ዓመቱ ያልዘለለው ላሚን ያማል ከኢኳቶሪያል ጊኒ እና ሞሮኮ ወላጆች ነው የተወለደው ። ይህ ድንቅ የኳስ ጥበበኛ 17ኛ ዓመቱ የሚሞላው በአውሮጳ ፍጻሜ ጨዋታ ማግስት ነው ።  ይህ የባርሴሎና ቡድን አዳጊ ተጨዋች በዩሮ ታሪክ ትንሹ ተሰላፊ ነው ። ያም ብቻ አይደለም በግማሽ ፍጻሜው ፈረንሳይ ላይ ድንቅ ግብ በማስቆጠርም በዩሮ የእግር ኳስ ታሪክ ትንሹ ግብ አስቆጣሪ ሆኖ ተመዝግቧል ።

«ያማል ገና ብሩኅ ተስፋ ያለው አፍላ ጮርቃ ተጨዋች ነው ዛሬ ግብ ያስቆጥራል ብዬ እገምታለሁ »

ስፔናዊው የላሚን ያማል አድናቂ ላሚን ግብ ባስገባበት ቀን ከጨዋታው በፊት የሰጠው ግምት ነው ። በእለቱ በእርግጥም የስፔኑ ደጋፊ ግምት ሠርቷል ። ያማል ስፔንን ለፍጻሜ ያበቃትን ድንቅ ግብ ከመረብ አሳርፏል ።  ሌላኛው የስፔን ድንቅ ኒኮ ዊሊያምስ የተወለደው አሰቃቂውን  የሰሐራ በረሃ አቋርጠው ስፔን አዲስ ሕይወት ከጀመሩ ጋናውያን ቤተሰቦች ነው ። ኒኮ በአትሌቲኮ ቢልባዎ ቡድን በስፔን ላሊጋ ከታላቅ ወንድሙ ኢናኪ ዊሊያምስ ጋ በመሰለፍ ቡድኑ የነበረበትን ዋንጫ የማንሳት ድርቀት ባለፈው የጨዋታ ዘመን ወደ ታሪክነት ቀይረውታል ። ኢናኪ ዊሊያምስ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር በ2022 ለጥቋቁር ከዋክብቱ የጋና ብሔራዊ ቡድን በመሰለፍ ብቃቱን አስመስክሯል ። 

ታናሽ ወንድሙ ዘንድሮ ዋንጫ ለማንሳት ጫፍ ደርሷል ። በእርግጥ የስፔን ቡድን ጨዋታ ውጤት በላሚን ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ ብቻ የሚገደብ አይደለም ።  ግን ደግሞ እነ ያማልም ሆኑ ሌሎች ከአፍሪቃ ሐረግ ከሚመዘዝ ቤተሰብ የሚወለዱ የዩሮ 24 ተሳታፊ ሃገራት ተጨዋቾች ለአውሮጳው እግር ኳስ ልዩ ቅመም ናቸው ። ይህን ያሉት ጃኮብ ሙሌ ናቸው፤ የኬንያ ብሔራዊ ቡድን የቀድሞ አሰልጣኝ  ።

ስፔን የዩሮ 2024 ክብርን ለመቀዳጀት በምታደርገው ጥረት ሁለቱ ምርጥ ተጨዋቾች ማለትም ላሚኔ ያማል እና ኒኮ ዊሊያምስ እጅግ ወሳኝ ናቸው ምስል፦ Irakli Gedenidze/REUTERS

«ከአፍሪቃ የዘር ሐረጋቸው የሚመዘዝ ተጨዋቾች ምናልባትም በርካታ የአውሮጳ ተጨዋቾች ያጡት ነገር አላቸው ። ምክንያቱም አፍሪቃውያን ተጨዋቾች ኳስ ሲጫወቱ የደነሱ ያህል ነው ። መድረክ ላይ የወጡ ነው የሚመስለው ። ለጨዋታው የሚሰጡት የተለየ ውበት አለ ። ማለቴ ጄጄ ኦካቻን ተመልከቱ፤ እንደ ኬሊያን እምባፔ ያሉ ተጨዋቾችን እዩ፤ ቡካዮ ሳካን ሳይቀር ተመልከቱ፤ ለጨዋታው የሚሰጡት የተለየ ቅመም አለ ። ያን የተወገደ ጊዜ ጨዋታው በሙሉ ወዝ አልባ ነው የሚሆነው ባይ ነኝ ።»

እነዚህ እና ሌሎች ከአፍሪቃውያን ቤተሰቦች የሚወለዱ ተጨዋቾች በውድድሩ ላይ መድመቃቸው በአፍሪቃ ልዩ ትኩረትን ስቧል ።

እንግሊዝ በዘንድሮ ውድድር ለውጥ ዐሳይታለች፤ ግን ደግሞ የቀድሞውን ዩሮ ፍጻሜ ሽንፈት መቀልበስ ትሻለችምስል፦ BEAUTIFUL SPORTS/Orangepictures/picture alliance

«በአሁኑ ወቅት  ዩሮ 2024  ጀርመን ውስጥ እየተካሄደ ነው ። ፍላጎት ከፍተኛ ነው ። አብዛኞቹ የሬዲዮ ጣቢያዎች የቀጥታ ሥርጭት ሽፋን እየሰጡ ነው ። ሰዉ በሙሉ በዩሮ ወቅት ቴሌቪዥን ላይ ተለጥፎ ነው የሚውለው ።»

በአውሮጳ ምድር ገንነው የወጡት ከአፍሪቃ ዘራቸው የሚመዘዝ ተጨዋቾች በእየ ፊናቸው ቡድናቸውን ለልዩ ክብር አብቅተዋል ። ያም ብቻ አይደለም ። የእነዚህ ተጨዋቾች ስኬት ለብዙዎች በአፍሪቃ ምድር ላሉ አዳጊዎችም ራሳቸውን ወደፊት አሻግረው የሚመለከቱበት አንዳች ተምሳሌት በመፍጠር አርአያነቱ እጅግ ላቅ ያለ ነው ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ፀሐይ ጫኔ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW