ከኢትዮጵያም ሆነ ከውጪ መንግሥታት “ምንም የተሰጠኝ ዋስትና የለም” አቶ ልደቱ አያሌው
ሰኞ፣ ጥር 19 2017
አቶ ልደቱ አያሌው በበይነ መረብ አማካይነት ባካሄዱት በዚሁ ጋዜጣዊ መግለጫ፣አጽንኦት ሰጥተው በኢትዮጵያ የሰላማዊ ትግልን አጠናክሮ የመቀጥል አስፈላጊነትን ነው። ፖለቲከኛው በዚህ በዩናይትድስቴትስ የነበራቸውን ሕክምና ከተከታተሉ በኋላ፣ በቅርቡ በሀገር ቤት ወደ ሀገር ቤት በመመለስ ሰላማዊ ትግሉን አጠናክረው የወሰኑት በትግሉ ዘላቂነት አሁንም ጽኑ እምነት ስላላቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
"በሰላማዊ ትግል እምነት ያለን ሰዎች ስላለን፣ እምነት የላቸው ድርጅቶች ስላሉ፣ ደካማም ይሆኑ፣አገር ቤት ከ ሃምሳ ከስድሳ በላይ በሰላማዊ ትግል ውጤት ማምጣት እንችላለን ብለው የተደራጁ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ድጋፍ ባይሰጣቸውም እየተንቀሳቀሱ ተስፋ ያልቆረጡ አሉ።ስለዚህ በሰላማዊ ትግል የምናምን ሰዎች አለን፣ሰላማዊ ትግልበአዋጅ እስካልተከለከለ ድረስ ባለው ጠባብ ሁኔታ ገብተን ለውጥ ማምጣት እንችላለን የሚል እምነት ያለን ሰዎች አለን።"
የአቶ ልደቱ አያሌው አዲሱ ሰነድና የኢትዮጵያ ፖለቲካ
ይህ ወደ አገር ቤት የማደርገው ጉዞ አዎንታዊ ወይም አሉታዊ ውጤት ሊያስከትል ይችላል የሚሉት አቶ ልደቱ፣ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰው እንደማንኛውም ዜጋ የግል ሕይወታቸውን የመኖር ከተቻለም ቀድሞ ሲንቀሳቀሱበት የነበረው ኢዴፓን እንደገና ማቋቋም እንደሚፈልጉ ጠቁመዋል።
"በሰላማዊ ትግል የህዝብን እመራለሁ የሚል አንድ ሰው ውጤታማ ሊሆን የሚችለው የሚገባውም ሀገር ውስጥ ችግሩ ያለበት የሚጨቆነው የሚገደለው ህዝብ ባለበት፣ሃገር ውስጥ ሆኖ ነው መምራት ያለበት። ሰላማዊ ትግል የሞራልም ጉዳይ ነው። ስለዚህ አንድ የሰላማዊ ትግል መሪ አርአያ ሆኖ ማሳየት አለበት። በሰላማዊ ትግል ቀድመው የሚታሰሩት፣ የሚሞቱት የችግር ሰለባ የሚሆኑት ተከታዮች ሳይሆኑ መሪዎች ናቸው። ይሄ የታወቀ ነገር ነው፤ስለዚህ ከመሪነት ሞያ አንፃር ውጭ አገር ሳይሆን አገር ውስጥ ሆኖ መታገል ነው አስፈላጊው የሚል ነው።"
ፖለቲከኛው፣ካማቴ ኦራ አደራ የበላው ትውልድ እና ስኬት የራቀው ትውልድ በሚል ርዕስ ያዘጋጁትን ጽሑፍ ዶይቸ ቨለን ጨምሮ ለሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ተቋማት አሰራጭተዋል።
በዚሁ ጽሑፋቸውንም፣ በኢትዮጵያ የሚካሄደው የፖለቲካ ትግል ዘላቂ መፍትሔ ሊያገኝ የሚችልባቸውን መንገዶች ሲያብራሩ፣ ግልጽ በሆነ አስተባባሪና አሻጋሪ አገራዊ የፖለቲካ አጀንዳ ከተመራ እንደሆነ አመልክተዋል።
ልደቱ አያሌው በሕመም ሳቢያ ከፖለቲካ መገለላቸውን አስታወቁ
ለትግሉ የሚመጥን ዕውቀት፣ልምድና ስነምግባር ባላቸው ግለሰቦች ከተመራ፣ቢቻል ብሔር ተሻጋሪ በሆነ ሀገራዊ አደረጃጀት፣ከተቻለም መለስተኛ የጋራ አጀንዳዎች ላይ መስማማት በቻሉ ድርጅቶች ጥምረት መሆኑንም አክለዋል።
ሦስት ዐስርት ዓመታት በተሻገረ የፖለቲካ ትግል ጉዞአቸው ውስጥ በርካት የሚያጸጽቱና የሚያስቆጩ የስተሳሰብ ድክመቶች እንደነበሩባቸው ያወሱት፣አቶ ልደቱ ከነዚህ ድክመቶች በመማር ብዙ የአመለካከት ለውጦች ማድረጋቸዉን ገልጸዋል።
እስካሁን በነበራቸው የውጭ አገር ቆይታ በሰላም ላይ በሚሰሩ ሁለት ስብስቦች ውስጥ አባል በመሆን መስራታቸውን፣ የአገሪቱን ወቅታዊ ሁኔታ በማሳወቅ ረገድ የተወሰኑ ያሏቸውን የዲፕሎማሲ ስራዎች ማከናወናቸውንም አስረድተዋል።
ታሪኩ ኃይሉ
እሸቴ በቀለ
ጸሀይ ጫኔ