1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ከኢትዮጵያ የ2018 አጠቃላይ በጀት 24 በመቶ ገደማ ለዕዳ ክፍያ ተመደበ

ረቡዕ፣ ሰኔ 4 2017

ከ2018 የኢትዮጵያ 1.93 ትሪሊዮን ብር በጀት 463 ቢሊዮን ብር ለዕዳ ክፍያ ተመድቧል። የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት “የተሟላ” የሚሉት የኢኮኖሚ ማሻሻያ ላይ ያተኮረው በጀት ለአዳዲስ ፕሮጀክቶች ገንዘብ አልመደበም። በቀጣዩ ዓመት 1.2 ትሪሊዮን ብር ገቢ ከሀገር ውስጥ ለመሰብሰብ አዳዲስ የታክስ ፖሊሲዎች ሥራ ላይ እንደሚያውል መንግሥት አስታውቋል።

የኢትዮጵያ የገንዘብ ሚኒስትር አቶ አሕመድ ሽዴ
የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ “የመደበኛ በጀቱን ያሳበጠው” ለዕዳ ክፍያ የተመደበው እንደሆነ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል።ምስል፦ Michael Tewelde/Xinhua News Agency/picture alliance

ከኢትዮጵያ የ2018 አጠቃላይ በጀት 24 በመቶ ገደማ ለዕዳ ክፍያ ተመደበ

This browser does not support the audio element.

የኢትዮጵያ መንግስት ለ2018 ካዘጋጀው 1.93 ትሪሊዮን ብር በጀት 463 ቢሊዮን ብር ለዕዳ ክፍያ እንዲውል መድቧል። “ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ሀገር” ዕዳ ክፍያ የተደለደለው የገንዘብ መጠን ከአጠቃላይ የ2018 በጀት 24 በመቶ ገደማ፤ ከመንግስት የመደበኛ ወጪ 39 በመቶ  ድርሻ አለው።

ለ2018 የተዘጋጀው በጀት ከተያዘው ዓመት ጋር በ494 ቢሊዮን ብር ጨምሯል። ይህ ከ2017 መደበኛ እና ተጨማሪ በጀት 34.4 በመቶ ዕድገት አለው። በ2018 በጀት ለፌድራል መንግሥት መደበኛ ወጪ 1.8 ትሪሊዮን ብር፤ ለካፒታል ወጪ በአንጻሩ 415 ቢሊዮን ብር ገደማ ተመድቧል። ከሚቀጥለው ዓመት በጀት የክልሎች ድጋፍ 315 ቢሊዮን ብር ድርሻ ሲኖረው ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ 14 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ “የመደበኛ በጀቱን ያሳበጠው” ለዕዳ ክፍያ የተመደበው እንደሆነ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስረድተዋል። ከዕዳ ክፍያ ውጪ ያለው መደበኛ በጀት ከካፒታል በጀት ሲነጻጸር “እጅግ ጤናማ እና ለልማት ሥራዎች ከፍተኛ ትኩረት የሰጠ” እንደሆነ የገንዘብ ሚኒስትሩ አስረድተዋል።

“መደበኛ በጀት በዝቶ አይደለም” ያሉት አቶ አሕመድ “ለዕዳ የምንከፍለው በጀት ከፍተኛ ነው። እየከፈልን ያለንው ዕዳ ደግሞ ባለፉት 15 እና 20 ዓመታት ስንበደር የነበሩ ዕዳዎች ነው” ሲሉ ተደምጠዋል። የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ ትላንት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በሰጡት ማብራሪያ መንግሥታቸው የወጪ ድልድል ሲያደርግ ቅድሚያ የሚሰጠው ለዕዳ ክፍያ እንደሆነ ተናግረዋል።

የክልሎች በጀት፣ ደመወዝ፣ ሥራ ማስኬጃ እና ካፒታል በጀት እንደ ቅደም ተከተላቸው ትኩረት እንደሚጣቸው የገንዘብ ሚኒስትሩ አስረድተዋል። ገንዘብ ሚኒስቴር ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረበው ሰነድ እንደሚያሳየው በ2017 በጀት ዓመት ለዕዳ ክፍያ የተመደበው 324.3 ቢሊዮን ብር ነው። ለመጠባበቂያ በአንጻሩ 244.4 ቢሊዮን ብር ተመድቦ ነበር።

በ2018 በጀት “ለዕዳ መክፈያ እና ለመጠባበቂያ ተብሎ የተቀመጠው 732 ቢሊዮን ብር” መድረሱን የጠቀሱት የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሐመድ “መጠባበቂያ እና የዕዳ [ክፍያ] ብቻ አንድ ሦስተኛ በጀቱን ወስዶታል” ሲሉ ይናገራሉ። ለዕዳ ክፍያ እና ለመጠባበቂያ የተመደበው “በጣም ከፍተኛ ጭማሪ ነው በጀቱን እንዲለጠጥ ያደረገው” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ይኸ በጣም ያስፈራል። አንድ አራተኛ የሀገሪቱ በጀት ለዕዳ መክፈያ ይውላል ማለት ነው” ሲሉ አስረድተዋል።

መንግሥት በሐምሌ 2016 ተግባራዊ ያደረገው የውጪ ምንዛሪ ሥርዓት ኢትዮጵያ መክፈል ያለባት የውጪ ዕዳ “በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጎታል” ሲሉ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል፦ Shewangizaw Wegayehu/DW

የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አሕመድ ሽዴ የመንግሥታቸው በጀት “በአጭር እና በመካከለኛ ጊዜ እየጨመረ” መጥቷል ላሉት የዕዳ ክፍያ እየዋለ እንደሚገኝ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት አስገንዝበዋል። በግምዣ ቤት ሰነድ ሽያጭ “የተወሰዱና አዲስ የሚወሰዱ ብድሮች ክፍያ የወለድ ምጣኔ በአንጻራዊነት ካለፉት ዓመታት አንጸር ከፍ ያሉ በመሆናቸው የብድር ክፍያ ወጪው ከፍ እንዲል” ማድረጉን የገንዘብ ሚኒስትሩ የበጀት መማብራሪያ ይጠቁማል።

መንግሥታቸው ከአበዳሪዎች ጋር ያደረጋቸው የዕዳ ሽግሽግ ድርድሮች “ውጤታማ በመሆናቸው ጫናው የቀነሰ” መሆኑን የጠቀሱት አቶ አሕመድ “ይኸ ባይሆን ኖሮ የዕዳ ክፍያ ጫናው ከዚህ በላይ ከፍ ይል እንደነበር” ተናግረዋል። የኢትዮጵያ መንግሥት በ2017 የየበጀት ጉድለት ለመሙላት ምንም ዓይነት የቀጥታ ብድር ከብሔራዊ ባንክ እንደማይወስድ አስታውቋል። በምትኩ የግምዣ ቤት ሰነድ በመሸጥ በሀገር ውስጥ ብድር የሚገጥመውን የበጀት ጉድለት የመሙላት አካሔድ እየተከተለ ነው።

“የሀገር ውስጥ ዕዳ ለምሳሌ የግምዣ ቤት ሰነድ በአጭር ጊዜ መከፈል ያለበት ነው። የረዥም ጊዜ ዕዳ አይደለም” የሚሉት ዶክተር አብዱልመናን “ወለዱም ቀላል” እንዳልሆነ ይገልጻሉ። “ከ16 በመቶ በላይ ነው ለግምዣ ቤት ሰነድ ላይ የሚከፈለው ወለድ። መቶ ቢሊዮን [ብር] ዕዳ ካለብህ እኮ በዓመት 16 ቢሊዮን ብር ወለድ አለብህ። [መንግሥት የግምዣ ቤት ሰነድ በመሸጥ ከሀገር ውስጥ የተበደረው] በመቶዎች ቢሊዮን ነው” ሲሉ አብራርተዋል።

መንግሥት በአበዳሪዎቹ የዕዳ አከፋፈል ሽግሽግ ቢደረግለት እንኳ በሐምሌ 2016 ተግባራዊ በተደረገው የውጪ ምንዛሪ ግብይት ሥርዓት ለውጥ ምክንያት የኢትዮጵያ ዕዳ “ከእጥፍ በላይ” አድጓል። ዶክተር አብዱልመናን መሐመድ እንደሚሉት “የውጪ ምንዛሪ ሥርዓቱ ባልተሸጋሸገው ዕዳ ላይ” የመንግሥትን ክፍያ “በጣም በከፍተኛ ሁኔታ እንዲጨምር አድርጎታል።”

ከዕዳ ክፍያ ቀጥሎ የነዳጅ እና የማዳበሪያ ድጎማን ጨምሮ ለበጀት ድጋፍ 186 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። የ2018 በጀት የኢትዮጵያ ባለሥልጣናት “የተሟላ” የሚሉት የኢኮኖሚ ማሻሻያ መርሐ-ግብር ላይ ትኩረት ያደረገ ነው። ከጠቅላላ ካፒታል በጀት “ከ74.5 በመቶ በላይ” የወሰዱት እና “ከፍተኛ ትኩረት” የተሰጣቸው ዘጠኝ የሥራ ዘርፎች ናቸው። “ለዋና እና ለአገናኝ መንገዶች ግንባታ እና ነባሮቹን ለማጠናከር እና ለማሻሻል ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች” 93.6 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።

በ2018 በጀት “ለዋና እና ለአገናኝ መንገዶች ግንባታ እና ነባሮቹን ለማጠናከር እና ለማሻሻል ለተጀመሩ ፕሮጀክቶች” 93.6 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።ምስል፦ Imago/Xinhua Afrika

ለከፍተኛ ትምህርት ነባር ፕሮጀክቶች ማስፈጸሚያ፣ ለቴክኒክና ሙያ ስልጠና ኢንስቲትዩት እና ለአጠቃላይ ትምህርት ጥራት ማሻሻያ የተመደበው 44.5 ቢሊዮን ብር ነው። የመስኖ ልማትን ለማስፋፋት፤ ለነባር እና ለትላልቅ መስኖዎች ግንባታ የውጭ ፋይናንስን ጨምሮ ብር 18.3 ቢሊዮን ብር ተመድቧል። ለመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ብር 15.3 ቢሊዮን ብር፤ በግብርናው ዘርፍ ለተፈጥሮ ሀብት ልማት እና ጥበቃ ብር 2.6 ቢሊዮን ብር ተመድቧል።

በገጠር የስራ ዕድልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ለልማታዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ብር 48.7 ቢሊዮን ብር የተመደበ ሲሆን፤ ለከተማ ምግብ ዋስትናና ልማታዊ ሴፍቲኔት ብር 24.1 ቢሊዮን ብር እንደተመደበ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው የበጀት ሰነድ ያሳያል። ለጤና ዘርፍ ጠቅላላ ብር 48.0 ቢሊዮን ብር፤ በጦርነቱ ምክንያት የወደሙ ንብረቶች እና አገልግሎት መስጫ ተቋማት ወደ ነበሩበት እንዲመለሱ ለማድረግ 10 ቢሊዮን ብር እንዲሁም ለመንግሥት ቢሮዎች ግንባታ ፕሮጀክት ብር 4.0 ቢሊዮን ብር ተደልድሏል።

በ2018 የኢትዮጵያ መንግሥት 1.5 ትሪሊዮን ብር ገቢ የመሰብሰብ ዕቅድ አለው። ከዚህ ውስጥ 1.2 ትሪሊዮን ብር ከሀገር ውስጥ ገቢ፤ 235.5 ቢሊዮን ብር ከቀጥታ የበጀት ድጋፍ ዕርዳታ እንዲሁም 46.9 ቢሊዮን ብር ከፕሮጀክቶች ዕርዳታ ሊሰበሰብ የታቀደ ነው። ለሚቀጥለው ዓመት የታቀደው የገቢ መጠን ከ2017 ጋር ሲነጻጸር በ62 በመቶ ላቅ ያለ ነው።

መንግሥት ከዓለም አቀፍ አበዳሪዎቹ ገቢውን ለማሳደግ በተስማማው መሠረት በ2018 አዳዲስ የታክስ ፖሊሲዎች በሥራ ላይ እንደሚያውል አስታውቋል። የመንግሥትን ገቢ ለማሳደግ በሥራ ላይ ያዋላቸውን የታክስ ፖሊሲዎች በተጠናከረ ሁኔታ ተግባራዊ እንደሚያደርግ አቶ አሕመድ አስረድተዋል።

አርታዒ ኂሩት መለሰ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW