ከኤጀንሲዎች ተቃውሞ የቀረበበት የውጪ ሀገር ሥራ ሥምሪት ማሻሻያ አዋጅ በምክር ቤት ሊጸድቅ ነው
ሰኞ፣ ሰኔ 23 2017
ፈቃድ ተሰጥቷቸው “ሠራተኛን በውጭ ሀገር ለሥራ ለአሠሪ የማቅረብ አገልግሎት” የሚሠጡ ኤጀንሲዎች ላይ “ከሥራ ያስወጣናል” የሚል ሥጋት የፈጠረው የውጪ ሀገር ሥራ ሥምሪት ማሻሻያ ረቂቅ አዋጅ ነገ ማክሰኞ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይጸድቃል ተብሎ ይጠበቃል።
የአዋጅ ረቂቁ “ወደ ውጭ ሀገር በመሄድ ለመሥራት ፍላጎት ያላቸው እና ብቁ የሆኑ ኢትዮጵያውያን መብታቸው፣ ደህንነታቸው እና ክብራቸው ተጠብቆ ባላቸው ችሎታና አቅም ሠርተው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል” የተዘጋጀ እንደሆነ በመግቢያው ላይ ሠፍሯል።
አዋጁ ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች ወደ ውጪ ሀገራት የሚልኩ ኤጀንሲዎች ለፈቃድ እንዲሁም “ለመብት ክብር እና ደህንነት ዋስትና ማስከበሪያ” እንዲያሲይዙ የሚጠየቁት የገንዘብ መጠን ላይ ከፍተኛ ለውጥ አድርጓል። እስካሁን ሥራ ላይ በቆየው አዋጅ በኢትዮጵያውያን የተቋቋመ የንግድ ማኅበር ፈቃድ ለማግኘት “ከአንድ ሚሊዮን ብር ያላነሰ የተዋጣ መዋጮ” ያስፈልገው ነበር።
አዲሱ የማሻሻያ አዋጅ “ሠራተኛን በውጭ ሀገር ለሥራ ለአሠሪ የማቅረብ አገልግሎት” የሚሠጡ ኤጀንሲዎችን በአምስት ደረጃዎች ይከፋፍላቸዋል። ደረጃ አንድ የተባለው ፈቃድ የሚሰጠው ከፍተኛው “20 ሚሊዮን ብር ካፒታል ወይም አክሲዮን ወይም መዋጮ ያለው” መሆን እንዳለበት ዶይቼ ቬለ የተመለከተው የአዋጅ ረቂቅ ይደነግጋል። ለደረጃ ሁለት 15 ሚሊዮን ብር፣ ለደረጃ ሦስት 10 ሚሊዮን ብር፣ ለደረጃ አራት 7.5 ሚሊዮን ብር እንዲሁም ለደረጃ አምስት ፈቃድ 5 ሚሊዮን ብር “ካፒታል ወይም አክሲዮን ወይም መዋጮ” በቅድመ ሁኔታነት ተቀምጧል።
ኤጀንሲዎቹ እንደሚሰጣቸው ፈቃድ ደረጃ ወደ ውጪ ሀገር ለሚልኩት “ሠራተኛ መብት ክብር እና ደህንነት ዋስትና ማስከበሪያ” የሚያስቀምጡት ገንዘብ የተለያየ መጠን ያለው ነው። በዚህም መሠረት የደረጃ አንድ ፈቃድ ባለቤት የሚሆኑ ኤጀንሲዎች 250,000 ዶላር ማስቀመጥ አለባቸው። ሁለተኛ ደረጃ ለሚሰጠው ፈቃድ 200,000 ዶላር፣ ለሦስተኛ ደረጃ 150,000 ዶላር፤ ለአራተኛ ደረጃ 100,000 ዶላር እንዲሁም ለመጨረሻው አምስተኛ ደረጃ ፈቃድ 50,000 ዶላር ማስያዝ አለባቸው።
ይህ ገንዘብ “ለሠራተኛው መብት ክብር እና ደህንነት ዋስትና ማስከበሪያ” የሚውል እንደሆነ ዶይቼ ቨለ የተመለከተው ረቂቅ አዋጅ ላይ ሠፍሯል። ይህ የሚሆነው ግን ኤጀንሲው ሠራተኛን ወደ ሀገር የመመለስ ግዴታውን ካልተወጣ ይሆናል።
በነባሩ አዋጅ መሠረት የተጠየቀውን ዋስትና በጥሬ ገንዘብ ያልከፈሉ ኤጀንሲዎች “ለ100 ሺሕ ዶላር ተመጣጣኝ የሆነ ቤት ወይም ሌላ ንብረት ለባንክ አስይዞ ማስተማመኛ ደብዳቤ ለሥራ እና ክኅሎት ሚኒስቴር” በማቅረብ ሥራውን ሲያከናውኑ መቆየታቸውን አንድ ስማቸው እንይጠቀስ የጠየቁ የድርጅት ባለቤት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።
በአዲሱ የአዋጅ ረቂቅ ግን ኤጀንሲዎቹ ገንዘቡን በዶላር ወይም ተመጣጣኙን በብር በሥራ እና ክኅሎት ሚኒስቴር የባንክ ሒሳብ ማስቀመጥ እንዳለባቸው ተደንግጓል።
ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁት የኤጀንሲ ባለቤት የተጠየቀው የገንዘብ መጠን “ተጋኗል” የሚል አቋም አላቸው። በዘርፉ ለ20 ዓመታት ገደማ የሠሩት ግለሰብ “ይህንን የሚያክል ገንዘብ ዋስትና ለማስያዝ” የኤጀንሲዎችን አቅም “በጣም የሚፈታተን” እና አብዛኞቹን “ከሥራ ውጪ ሊያደርግ የሚችል” እንደሆነ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ነገ ማክሰኞ አዋጁን ሲመለከት “ጉዳዩን አጢኖ ተገቢውን የማስተካከያ ሥራ ይሥራልን” የሚሉት የኤጀንሲ ባለቤት “አዋጁ ተሻሽሎ የሕዝቦችን ደሕንነት፣ ክብር እና ጥቅም የሚያስከብር አይሁን እያልን አይደለም” ሲሉ አስረድተዋል።
ኤጀንሲዎቹ በአምስቱ ደረጃዎች ሲከፋፈሉ ወደ ውጪ የሚልኳቸው ሠራተኞች ቁጥር የተለያየ ይሆናል። ከዚህ በተጨማሪ ኤጀንሲዎቹ በብር መዳከም ምክንያት ለዋስትና ባስያዙት ገንዘብ ላይ የሚከሰተውን ለውጥ እያሟሉ መሔድ እንደሚጠበቅባቸው ሌላ ስማቸው እንዳይጠቀስ የጠየቁ የኤጀንሲ ባለቤት ተናግረዋል።
ዶይቼ ቬለ ያነገራቸው ሌላ የኤጀንሲ ባለቤት ለደረጃ አንድ ፈቃድ የተጠየቀው 250 ሺሕ ዶላር “ከፍተኛ ገንዘብ ነው። አቅልለው እንደሚያዩት ትንሽ ብር አይደለም” ሲሉ ይናገራሉ። ማንነታቸው እንይገለጽ የጠየቁት እኚሁ የኤጀንሲ ባለቤት የኢትዮጵያ መንግሥት ባለሥልጣናት ሠራተኞች ወደ ውጪ የመላክ ሥራ “በኮርፖሬት ደረጃ መሠራት አለበት” የሚል ዕምነት እንዳላቸው ታዝበዋል።
ኢትዮጵያውያንን ወደ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤሚሬቶች እና ዮርዳኖስ የመሳሰሉ ሀገራት የሚልክ ኤጀንሲ የሚመሩት ግለሰብ በረቂቅ አዋጁ የተቀመጠው ቅድመ-ሁኔታ “የሆኑ ሰዎችን ገፍቶ፤ የሆነ ሰዎችን የማስገባት ፍላጎት” እንዳይሆን ሥጋት አላቸው።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያንን ወደ ውጪ የሚልኩ 1,400 ገደማ ኤጀንሲዎች መኖራቸውን የሚናገሩት ግለሰብ ከእነዚህ “ግማሹ [የተጠየቀውን የገንዘብ መጠን] ማስያዝ ይችላል ተብሎ አይጠበቅም” ሲሉ ተናግረዋል።
ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ከሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር ለመጠየቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካም። የሥራ እና ክህሎት ሚኒስቴር የሕግ ክፍል ኃላፊ ሲቲና መንግሥቱ የአዋጅ ማሻሻያው ሲዘጋጅ “ያለውን የገበያ ሁኔታ፣ የገንዘብ የግሽበት መጠን” ታሳቢ ተደርጎ መሆኑን በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በጉዳዩ ላይ በተደረገ ውይይት ላይ ተናግረዋል። እስካሁን ሥራ ላይ በሚገኘው አዋጅ ኤጀንሲዎች 100 ሺሕ ዶላር ለዋስትና ማስያዝ እንደሚጠበቅባቸው ያስታወሱት ሲቲና “አሁን በሥራ ላይ የሚገኙ ኤጀንሲዎች ከገበያ እንዳይወጡ” 50 ሺሕ ዶላር መደረጉን አብራርተዋል።
አርታዒ ነጋሽ መሐመድ