ከካማሺ ዞን ጥቃት ያመለጡ ዜጎች ተማጽኖ
ሰኞ፣ ሰኔ 20 2014
ከሳምንት በፊት ሰኔ 11/2014 ዓ.ም ከምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌና ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን «ሴኔ» ቀበሌ የደረሰውን ጥቃት ሸሽተው የተፈናቀሉ ዜጎች መንግሥት ወደ ሰላማዊ አካባቢዎች እንዲያሰፍራቸው ጠየቁ፡፡ ከጥቃቲ ያመለጡ 3000 ያህል ሰዎች አርጆ ጉደቱ በተባለች ከተማ እንደሚገኙ ተናግረዋል፡፡ ከስፍራው የሸሹ ነዋሪ እንደተናገሩት በሰው ላይ ከደረሰው ጉዳት በተጨማሪ በንብረት ላይም ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ገልጸው 25 ከብቶች እና 37 ፍየሎች በግለሰብ ደረጃ እንደተወሰደባቸው ተናግረዋል፡፡ መንግሥት ወደ ተሻለ ቦታ በመውሰድ ህይወታቸውን እንዲያድንም ጠይቀዋል፡፡
በምዕራብ ወለጋ ጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ እና ከቶሌ ቀበሌ በቅርብ ርቀት ላይ በሚትገኘው የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ካማሺ ዞን ቦሎ ጅጋንፎይ (ሚዥጋ) ወረዳ «ሴ»" በተባለች ቀበሌ ውስጥ በደረሰው ጥቃት በመቶዎች የሚቆጠሩ ንጹሀን ዜጎች ህይወት ማለፉና በሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ደግሞ ቀያአቸውን ጥለው ወደ አርጆ ጉደቱ ወረዳ እና ሌሎች ስፍራዎች መሸሻቸው ተገልጸዋል፡፡
ሴኔ የተባለች የካማሺ ዞን ቦሎጅጋንፎይ ወይም ምዥጋ ተብሎ የሚታወቀው ወረዳ አንድ ቀበሌ ስትሆን ከጊምቢ ወረዳ ቶሌ ቀበሌ ያለው ርቀት 9 ኪ.ሜ ወይም የ30 ደቂቃ የእግር ጉዞ ነው፡፡ በሴኔ ቀበሌ የተፈናቀሉ ነዋሪ እንደተናገሩት ጥቃቱ በሁለቱም ቀበሌዎች በተመሳሳይ ሰዓት የጀመረ ሲሆን ሴኔ ቀበሌ በአንድ ስፍራ ብቻ 19 ሰዎች መሞታቸውን ወደ አርጆ ጉዳቱ ከተማ የሸሹ ነዋሪ አመልክተዋል፡፡
በዕለቱ በተለያዩ ቦታዎች በደረሰው ጥቃት የጉዳት መጠኑን በተለያዩ ሰዎች የተለያዩ ቁጥር እየተገለጸ ሲሆን ያነጋርናቸው አራት የአካባቢው ነዋሪዎች እንደነገሩን አንድ ቦታ 130 ሰዎች በጅምላ መቀበራቸውን ተናግረዋል፡፡ በቶሌ ቀበሌ ስልሳው የተባለ ሰፈር ውስጥ ደግሞ አንድ ቦታ 65 ሰው፣ ሌላ ቦታ ደግሞ 15 ሰዎች በጅምላ መቀበራቸውን እንደሚያውቁ ነዋሪዎቹ ገልጸዋል፡፡ ጥቃቱ በተለያዩ ቦታ የደረሰ በመሆኑ የጉዳት መጠኑን በቀላሉ ማወቅ አልተቻለም፡፡ የፌደራል መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስትር ዶ/ር ለገሰ ቱሉ ሰሞኑን ጉዳዩን አስመልክቶ ለዶቼ ቬለ እንደተናሩት መንግሥት በአካባቢው የደረሰውን የጉዳት መጠን እያጣራ ይገኛል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
ታምራት ዲንሳ
አዜብ ታደሰ