1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከኬንያ የምክክር ኮሚሽን ኢትዮጵያ ምን ትማር?

ረቡዕ፣ መስከረም 18 2015

ከኬንያው «ብሔራዊ ትስስር እና ውሕደት ኮሚሽን» በእንግሊዝኛው (National Cohesion and Integration Commission) ለኢትዮጵያ ምን የሚጠቅም ልምድ ይኖር ይሆን? መንግሥታዊ ተቋሙ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጋር ተመሳሳይና ተቀራራቢ ዓላማ ይዞ የተቋቋመው ነው።

Karte Kenia Kapenguria Englisch

የኬንያው «ብሔራዊ ትስስር እና ውሕደት ኮሚሽን»

This browser does not support the audio element.

ከኬንያው «ብሔራዊ ትስስር እና ውሕደት ኮሚሽን» በእንግሊዝኛው (National Cohesion and Integration Commission) ለኢትዮጵያ ምን የሚጠቅም ልምድ ይኖር ይሆን? መንግሥታዊ ተቋሙ ከኢትዮጵያ ሀገራዊ የምክክር ኮሚሽን ጋር ተመሳሳይና ተቀራራቢ ዓላማ ይዞ የተቋቋመው ነው። ኮሚሽኑ በትምህርት ሥርዓቱ ላይ ሀገራዊ እሴቶችን በማስረጽ ማሻሻያዎችን በማድረግ፣ በጎሳዎች መካከል ተፈጥሮ የነበረውን ከፍተኛ ጥላቻ በእርቅ እና መቀራረብ እንዲስተካከል በማድረግ፤ የጥላቻ ንግግሮች በሀገሪቱ እንዲረግቡ አሠራር በመዘርጋት እና ፍትኃዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር በማድረግ ውጤት የታየባቸው ሥራዎች መከወኑን ለዶቼ ቬለ ገልጿል። 

"ናሽናል ኮሄዥን ኤንድ ኢንተግሬሽን ኮሚሽን" የተባለው የኬንያ መንግሥታዊ ተቋም በዋናነት ኬንያ ውስጥ እስከ 40 በሚሆኑት የተለያዩ ጎሳዎች እንዲሁም ሃይማኖቶች መካከል ያሉ በጎ እድሎችን ለማዳበር፣ በመካከላቸው መልካም ግንኙነትን ለማጠናከር ፣ ዘላቂ ስምምነትን ለማስፈን ብሎም ሰላማዊ አብሮ መኖርን ለማመቻቸት እና ለማስተዋወቅ ኃላፊት ይዞ የተቋቋመ ነው። 

ተቋሙ የተባበሩት ምንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት አደረኩት ባለው ምርመራ ከሀገሪቱ ከ2017ቱ ምርጫ ማግስት በተከሰተው ቀውስ 1200 ሰዎች ከተገደሉ፣  በሽዎች የሚገመቱት የአካል ጉዳት ደከደረሰባቸው፣ 300,000 ያህሉ ከተፈናቀሉና በአራት አሥርት ሺህ የሚቆጠሩት መኖሪያና የንግድ ቤቶች ተዘርፈው እና የጎሳ ጥላቻ እና መከፋፈል ከተንሰራፋ በኋላ የተቋቋመ ነው። የዚሁ ተቋም የሥራ ኃላፊ ከሆኑት አንደኛዋ ወይዘሮ ጀሲካ ኦቲኖ ተቋማቸው ብሔራዊ እርቅን ለመፍጠር በዋናነት የትምህርት ሥርዓቱ ላይ ማሸሻያዎችን ማድረግ ላይ በሰፊው መሥራቱን ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። 

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ጎልቶ እየተስተዋለ ባለ ተመሳሳይ ችግር ውስጥ የምትገኘው ኢትዮጵያ በተለይ መቻቻልን ፣ ሰላምን እና ልዩነትን ማክበርን በዋና ዋናዎቹ መገናኛ ብዙሃን እና ማህበራዊ መገናኛዎች ልትሰራባቸው የሚገቡ ኮሚሽናቸው ተጨባጭ ውጤት ያገኘባቸው የሥራ ዘርፎች መሆናቸውንም አብራርተዋል። በኬንያ ፍትሓዊ የሀብት ክፍፍል እንዲኖር በኮሚሽኑ ተሰራ ያሉት ሥራ ውጤት ማምጣቱንም የሥራ ኃላፊዋ ገልፀዋል።

ምስል Ben Curtis/AP/picture alliance

በተለይ በመሬት አጠቃቀም እና በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ውስጥ የዜጎች ፍትሓዊ ተሳታፊነት እና የቅጥር ተገቢነት ላይ ተከናወነ ያሉት ተግባር ሙስና እና ብልሹ አሰራር በተንሰራፋባት ኬንያ ውስጥ በጊዜ ሂደት ውጤቱ በተጨባጭ እየተስተዋለ ያለ ግኝት መሆኑን ዘርዝረዋል። "በ2021 በመንግሥት አምስት ዋና ዋና ተቋማት ውስጥ የሠራተኞች ሁኔታ ምን ይመስላል የሚለውን መመርመር ጀመርን። በወቅቱ ያረጋገጥነው ነገር በአምስቱ ዋና ዋና የመንግሥት ተቋማት ውስጥ 90 በመቶ ያህሉ የቅጥር ሁኔታ የሕብረተሰቡን ብዝሃነት ያማከለ የሠራተኛ ቅጥር መኖሩን ነው። ወደታችኛው መዋቅር ወረድ ብለን ስንመለከት ግን 75 በመቶ ያህሉ የቅጥር ሁኔታ አብዛኛውን የህብረተሰብ ክፍል ያላካተተ እና ዋና ዋና ብሄረሰቦች የመንግሥት ሥራዎችን በበላይነት የተቆጣጠሩበት ነበር" ብለዋል።

ኬንያ ከዓምስት ዓመታት በፊት ከነበረው ምርጫ ማግስት የተከሰተው አውዳሚ ቀውስ ላይ በዚህ ኮሚሽንና በሌሎችም አካላት ብዙ መሰራቱ ከወራት በፊት በተከናወነው ተመሳሳይ የምርጫ ሁነት ላይ ምንም ችግር ያልተስተዋለበት ሰላማዊ ድኅረ ምርጫ ውጤት አስተናግዶላታል። በሀገሪቱ የተንሰራፋ የነበረውን የጥላቻ ንግግር እና የሀሰተኛ መረጃዎችን ስርጭት ከመመርመር ባለፈ ኮሚሽኑን የሚያግዙ ከ 3000 በላይ የፖሊስ አባላት በልዩ ሁኔታ ሰልጥነው እንዱሰሩ መደረጋቸው ጥሩ እንዳገዛቸውም ጀሲካ ይገልፃሉ።

"የሀገሪቱ ዋና ዐቃቤ ሕግ በጥላቻ ንግግር ዙሪያ ጠንካራ ሥራ እንድንሰራ አበረታች ሁኔታ ፈጥረውልናል። አምስት ልዩ ችሎቶችን በማቋቋም እና ዳኞችን በመመደብ በልዩነት የጥላቻ ንግግሮችን የተመለከቱ ጉዳዮችን እንዲዳኙ አድርገዋል።"

አዲስ ተመራጩ የኬንያ ፕሬዝዳንት ዊሊያም ሩቶ የቀድሞው የሀገሪቱ መሪ ዑህሩ ኬንያታ ኢትዮጵያ ውስጥ ሁለት ዓመታት የደፈነው ጦርነት በሰላም እንዲቋጭ የማገዝ ኃላፊነት ሰጥተዋቸዋል።
ይህንን በተመለከተ የተጠየቁት የኬንያ የብሔራዊ ትስስር እና ውህደት ኮሚሽን የሥራ ኃላፊ ዑህሩ በሀገራቸው ውስጥ እርቅ እንዲሰፍን አድርገዋል ያሉትን ጥረት በማስታወስ ትክክለኛ ውሳኔ መሆኑን ይገልፃሉ ብለዋል ኃላፊዋ።

ምስል Simon Maina/AFP via Getty Images

"ፕሬዝዳንት ዑሁሩ የእርቅ ጉዳዮችን ለማከናወን ትክክለኛ ሰው ናቸው ብየ አምናለሁ። ምክንያቱም ያንን ኃላፊነት በሀገራችን ውስጥ አድርገውት ተመልክተናል" ሲሉም ያላቸውን ተስፋ ገልፀውልናል። የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኢትዮጵያ ውስጥ "መተማመን የሰፈነበት አዲስ የፖለቲካ ሥርዓት ለመፍጠር" ይሠራል የሚል ተስፋም ተጥሎበታል። የኬንያው መሰል ዓላማ ያነገበው ተቋም በተቃቋመ በጥቂት ዓመታት ውስጥ ከእነ ችግሮቹ ለውጦች ማምጣቱን መመልከት ይቻላል። 

የኢትዮጵያ አገራዊ የምክክር ኮሚሽን የሀገር ውስጥ የሰላምና የእርቅ እውቀትና ሀብቶችን ከመጠቀም ባሻገር መሰል አቻ ተቋማትን ማሰሱ ለሥራው ሥኬት ሊበጀው እንደሚቻ መመልከት ይቻላል።

ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW