1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከወለጋ የተፈናቃሉ ሰዎች ስጋት በምልሶ ማቋቋም ሂደት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 4 2016

ከደቡብ ወሎ ቃሉ ወረዳ ደጋን የአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካምፕ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ተፈናቃይ በሚገኙበት የተፈናቃዮች ካምፕ የሚደርሳቸው የእርዳታ መጠን እጅግ አነስተኛ መሆኑን በማስረዳት አሁን ደግሞ ያፈናቀላቸው የግጭት መዘዝ ከምንጩ ሳይደርቅ ወደ ነባሩ ቀዬያቸው እንድመለሱ ግፊት መኖሩን አስረድተዋል፡፡

በኦሮሚያ ክልል በወለጋ ዞኖች የሚደረገዉን ግጭትና ጥቃት ሸሽተዉ ደቡብ ወሎ ዞን ከሠፈሩ ተፈናቃዮች በከፊል
ከኦሮሚያ ክልል ሸሽተዉ አማራ ክልላዊ መስተዳድር ደቡብ ወሎ ዞን ከሠፈሩ ተፈናቃዮች በከፊል ምስል Aleminew Mekonnen

ከወለጋ የተፈናቃሉ ሰዎች ስጋት በምልሶ ማቋቋም ሂደት

This browser does not support the audio element.

 

ከኦሮሚያ ክልል ከተለያዩ የወለጋ ዞኖች ተፈናቅለው አማራ ክልል የሠፈሩ ሰዎች የተሟላ ሠላም ሳይሰፍን ወደየቀያቸዉ እንዲመለሱ መታቀዱ እንዳሰጋቸዉ አስታወቁ።በወለጋ ዞኖች በተደጋጋሚ የተደረገዉን ግጭትና ጥቃት የሸሹ በብዙ ሺሕ የሚቆጠሩ በአብዛኛዉ የአማራ ተወላጆች አማራ ክልል ሠፍረዋል።

በተለይ በደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ ሀይቅ ዉስጥ በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች የሰፈሩ ተፈናቃዮች ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ወደሚገኘዉ የቀድሞ ቀያቸዉ እንዲመለሱ ግፊት እየተደረገባቸዉ ነዉ።ተፈናቃዮቹ እንዲመለሱ የታቀደበት እንደ አቤዶንጎሮ እና ጃርዴጋጃርቴ የመሳሰሉት የሆሮጉዱሩ ዞን አካባቢዎች ሰሞኑን ግጭት ሲደግባቸዉ እንደነበር ተዘግቧል።

በተፈናቃዮች ካምፕ ያለው የድጋፍ እጥረት

ከደቡብ ወሎ ቃሉ ወረዳ ደጋንየአገር ውስጥ ተፈናቃዮች ካምፕ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ተፈናቃይ  በሚገኙበት የተፈናቃዮች ካምፕ የሚደርሳቸው የእርዳታ መጠን እጅግ አነስተኛ መሆኑን በማስረዳት አሁን  ደግሞ ያፈናቀላቸው የግጭት መዘዝ ከምንጩ ሳይደርቅ ወደ ነባሩ ቀዬያቸው እንድመለሱ ግፊት መኖሩን አስረድተዋል፡፡

“በዚህ መጠለያ ከመጣን ጊዜ ጀምሮ በወራት ውስጥ ይህቺ 15 ኪሎ ስንዴ ትሰጠናለች፡፡ ከእንጨት ጀምሮ ገዝተን ነው የምናበስለው፡፡ አሁንም በዚህ አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ሆነን አሁን እርዳታውን ስሰጡን ትሄዳላችሁ በሚል እየመዘገቡን ነበር” ብለዋል፡፡  

ከሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ተፈናቅለው ወደ ተፈናቃዮቹ ካምፕ መግባታቸውን የገለጹት አስተያየት ሰጪው ከሰሞኑ በዞኑ አቤዶንጎሮ እና ጃርደጋ ጃርቴ የተቀሰቀሰው አለመረጋጋት አሁን ላይ ትልቁ ስጋት እንደሆነባቸውም አልሸሸጉም፡፡ “አሁን ከሀሙስ ጀምሮ በተቀሰቀሰው ግጭት የሰዎች ህይወት እለት እለት እያለፈ መሆኑን እየሰማን በዚህ በኛ መካከል የሚገኙም መርዶ እየሰሙ እየተላቀሱ ነው” በሚል አሁን እንዲመለሱበት የተጠየቁበት አከባቢ ወደ ፍጹም መረጋጋት አለመመለሱን በስጋት አንስተዋል።

በኦሮሚያ ክልል በተለይ በወለጋ የተለያዩ ዞኖች የሚደረገዉን ግጭትና ጥቃት ከሸሹ ተፈናቃዮች በከፊልምስል Alemnew Mekonen/DW

በመልሶ ማቋቋም ውስጥ የሚታይ ስጋት

አስተያየት ሰጪው አክለውም እስካሁን በይፋ ወደ ቀዬያቸው የሚመለሱበት ቀን ባይነገራቸውም እሳቸው የሚገኙበት የተፈናቃዮች ካምፕ ውስጥ የሚገኙ ነዋሪዎች ከወዲሁ ወደ ቀዬያቸው ከሚመለሱት ከተባሉት ውስጥ መመዝገባቸውንም አስረድተዋል፡፡ “በጣም ስጋት አለን፡፡ ከአንድ ቤት ሰባት ቤተሰብ ሁሉ ማለቁን የተመለከትንበት ግጭት ነበር፡፡ አሁን ህይወታችን የተረፈው ወደ አሙሩ ወረዳ የወጣን ሰዎች ነን፡፡ በዚያ የቀሩት ግን በርካቶች አልቀዋል፡፡ አሁንም በዚህ ክረምት ብንሄድ እንዴት እንሆናለን በሚል ስጋት ላይ ነው ያለነው” በማለት አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡

ሌላው ከደቡብ ወሎ ዞን ጃሬ የተፈናቃዮች መጠለያ ካምፕ አስተያየት የሰጡን ተፈናቃይም ባለፈው ዓርብ ግንቦት 30 ቀን 2016 ዓ.ም. ቱርክ ካምፕ ከተባለ የተፈናቃዮች ካምፕ እና እሳቸው ከሚገኙበት የተፈናቃዮች ካምፕ ከ60 በላይ መንግስት ባቀረበላቸው ትራንስፖርት የማጓጓዝ ስራ መጀመሩንም አስረድተዋል፡፡ ይሁንና በዚህ በመጠለያ ካምፑ ድሎት ባይኖርም ምርጫቸው አሁንም በዚሁ መቆየት የሚሆንበት ምክኒያት ያፈናቀላቸው የጸጥታ እጦት አሁንም እልባት ማግኘቱን በእጅጉ መጠራጠራቸው መሆኑን አስረድተዋልም፡፡ “ሰዎችን ለመመለስ የወሰዱት ከሀይቅ ቱርክ ካምፕ እና መካነ እየሱስ ካምፕ ነው” ያሉት አስተያየት ሰጪው፤ ትራንስፖርት ተዘጋጅቶላቸው ልተገኙ ተፈናቃዮች ቤታቸው መታሸጉን ገልጸዋል፡፡ ሰው ስጋት እያለበት በግድ እንዲጓዝ ይደረጋልም ያሉት አስተያየት ሰጪው ተፈናቃይ፤ ፍላጎታቸው ጸጥታው አስተማማኝ የሆነ አከባቢ  ላይ መቆየት መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡ ከአምስት ኣመት በፊት ያፈናቀላቸው ግጭት መሰረተልማትን በማውደሙ ነገሮች ወደ ነባር ስፍራው እስኪመለሱ ወደዚያ የመመለስ ፍላጎት እንደሌላቸውም ጠቁመዋል፡፡

ከኦሮሚያ ክልል ሆሮጉዱሩ ወለጋ ዞን ከተፈናቀሉ ነዋሪዎች በከፊል ምስል Seyoum Getu/DW

አስተያየት ሰጪው ከምዕራብ የአገሪቱ አከባቢዎች ተፈናቅለው አሁን ላይ በሀይቅ በተለያዩ ካምፖች ብቻ ከሰባት ሺህ በላይ ተፈናቃዮች መኖራቸውን ይጠቁማሉ፡፡

ከዚህ በፊት አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የኦሮሚያ ቡሳጎኖፋ ቢሮ ኃላፊ ከ6000 በላይ ተፈናቃዮች በተለያዩ መንገዶች ወደ ምዕራብ ኦሮሚያ ቀዬያቸው መመለሳቸውን ገልጸው ተፈናቃዮችን በመመለስ ሂደት የሚደረግ የኃይል ጫና አለመኖሩን መናገገራቸው ይታወሳል፡፡

ሥዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW