1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከዋግሕምራ ወረዳዎች የተፈናቀሉ ዜጎች እሮሮ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 11 2015

በአማራ ክልል ዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በህወሓት ስር ከሚገኙ ሁለት ወረዳዎች በተለየዩ ምክንያቶች ሰዎች እየተፈናቀሉ ወደ ማሃል ዋግኽምራ እየመጡ እንደሆነ ተፈናቃዮችና ባለስልጣናትአመለከቱ። ነባር ተፈናቃዮች ደግሞ በእርዳታ እጦት ምክንያት ለልመና እና ለህመም መዳረጋቸዉን እየገለፁ ነዉ።

Äthiopien | Lager für Binnenvertriebene in Waghemra
ምስል Waghemra Disaster Prevention Office

bwageምራ ተፈናቃዮች ርዳታን እየጠበቁ ነዉ

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ዋግሕምራ ብሔረሰብ አስተዳደር በህወሓት ስር ከሚገኙ ሁለት ወረዳዎች በተለየዩ ምክንያቶች ሰዎች እየተፈናቀሉ ወደ ማሃል ዋግኽምራ እየመጡ እንደሆነ ተፈናቃዮችና ባለስልጣናት ገለፁ። ከዚህ ቀደም ከቦታዉ የተፈናቃሉ ሰዎች እርዳታ እጦት ምክንያት ለልመናና ለህመም እየተዳረጉ እንደሆነ ለዶይቼ ቬሌ ገልጸዋል። የዋህግምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና መምሪያ ግን እርዳታ ሳይቆራረጥ እየተሰጠ እንደሆነ ምላሽ ሰጥቷል፡፡

መንግስትና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ ፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት ካደረጉ በኋላ በበርካታ አካባቢዎች እርዳታ እየደረሰ ቢሆንም በህወሓት ቁጥጥር ስር ባሉ የአማራ ክልል፣ ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳ ነዋሪዎች እርዳታ ማግኘት ባለመቻላቸው ወደ ሰላማዊ የብሔረሰብ አስተዳደሩ አካባቢዎች እየተፈናቀሉ መሆናቸውን ተፈናቃዮች አመልክተዋል፡፡
በቅርቡ ከፃግብጂ ወረዳ ተፈናቅለው ከመጡት መካከል አንዱ ለመፈናቀላቸው ምክንያት የሆነውን ጉዳይ ገልጸውልናል፡፡
“በጣም ችግር ያለ አሁን ተፈናቃዩ ሁለት ዓይነት መሆኑ ነው ፣ መጀመሪያ ዓመትና ከዓመት በላይ የተፈናቀለው ማህበረሰብ በጦርነቱ እዚህ ከርሟል ሁለተኛ ደግሞ (አበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች) በኑሮ ውድነትና በገበያ መዘጋት ምክንያት ማህበረሰቡ እንዳለ ንቅል ብሎ ገብቷል ( ወደ መሐል ዋግኽምራ) ”
ሌላው ከአበርገሌ ወረዳ ተፈናቅለው ሰሞኑን ወለህ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ ከደረሱ ተፈናቃዮች መካከል አካባቢያቸው በነበሩበት ወቅት እርዳታ አያገኙም፣ ሌሎች ችግሮችም ያጋጥሙ እንደነበር አብራርተዋል፡፡
“የጥቅምት ሚካኤል ነው የመጣሁ (2015 ዓ ም) ጉዳዩ በማስገደድ ይህን አውጣ፣ይህን ስራ፣ እንዲህ አድርግ፣ … የሚባሉ ነገሮች አሉ፣ አዝመራ የለም ርሀብ በጣም ፀንቶብናል፣ እርዳታ የለም ቢመጣም እኮ በእኛ ጉዳይ ሲመጣ ውስጣዊ ጥቃት አለ፣ ማስገደድ አለ” ብለዋል፡፡ በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪ ወ/ሮ ዝናሽ ወርቁ፣ አዳዲስ ተፈናቃዮች ከሁለቱም ወረዳ እየመጡ እንደሆነ ጠቁመው እርዳታ እስካሁን እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡
“ወደ 4ሺህ 662 ሰው ከፃግብጂና ከአበርገሌ ወረዳዎች አዲስ ተፈናቃዮች የመጡ አሉ፣ ምንም ዓይነት ድጋፍ አላገኙም፣ ድጋፍ ጠይቀናል ወደ 15 እና 20 ቀን እየሆነ ነው ድጋፍ ከጠየቅን እስካሁን ግን አልመጣም፣ ለትግራይ ክልል እየተደረገለት እንዳለው ድጋፍ ለምንስ ወደ እነርሱ ወረዳዎች (ፃግብጂና አበርገሌ) እርዳታ አይገባም? ነፃ ነው ይባላል ግን እስካሁን ነፃ አይደለም፣ ሰው እንደ አዲስ እየመጣ ነው ያለው እና የሰላሙ ጉዳይ ቶሎ ሰላም የሚሆን ከሆነ ድጋፉን ማግኘት ይችላሉ፡፡” ነው ያሉት፡፡ ይህ በእንዲህ እንዳለ ነባር ተፈናቃዮች እርዳታ ካገኙ ወራት መቆጠራቸውንና አንዳንዶቹ ለልምና እየወጡ ነው ሲሉ ተፈናቃዮቹ አስረድተዋል፡፡
“ከሚያዝያ (2015 ኣ ም) ወዲህ እኮ ምንም ድጋፍ የለም፣ ሲቸግረው ግማሹ ሰው ከተማ ላይ ይለምናል፣ ተፈናቃዩ በጣም ችግር ውስጥ ነው ያለው፣ አሁን የባሰ ችግር ነው በፊትማ የተለያዩ ድርጅቶችም ይሁኑ፣ የአገር ውስጥ ደጋፊዎችም ትንሽ ትንሽ እየደገፉን ነው የነበሩት እስከ ሚያዝያ ድረስ፣ አሁን ምንም ድግፍ የለም ተቸግሮ ነው ያለው ተፈናቃዩ”
ሌላው ተፈናቃይ በበኩላቸው በምግብ እጥረት ምክንያት አንዳንዶቹ ለህመም ተጋልጠዋል ነው ያሉት፡፡
“ወር ከሁለት ሳምንት ሆኗል ድጋፍ ከተሰጠ፣… ህፃናትና ሽማግሌዎች ተቸግረው ነው አልጋ የያዙ አሉ በርሀብ የተኙ ሰዎች አሉ፡፡”
የብሔረሰብ አስተዳደሩ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት የቅድመ ማስጠንቀቂያና ምላሽ ቡድን መሪዋ ወ/ሮ ዝናሽ ግን ምንም እንኳ እርዳተው በቂ ነው ባይባልም ለእያንዳንዱ ተፈናቃይ መደበኛ እርዳታው እየተሰጠ ነው ብለዋል፡፡
“ሚያዝያ አይደለም የአስቸኳይ ጊዜ እርዳተውን እንደ እርዳታ ስለማያዩት ነው፣ 4ኛ ዙር ወስደዋል፣ አሁን 5ኛ ዙር ይገባላቸዋል፣ ምንም የተቋረጠ ነገር የለም፣ መደበኛ እርዳታው፣ የሚሰጠው 15 ኪሎግራም ስንዴ፣ 1. 5 ኪሎግራም ክክና 0.45 ሊትር ዘይት ለእያንዳንዱ ተፈናቃይ ይሰጣል፣ 10 ቤተሰብ ካለ በዚህ ተሰልቶ ይሰጣል፣ ይህ መደበኛና የማይቋረጥ ነው፡፡” ከክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ማስተባባሪያ ኮሚሽን ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት ለዛሬ አልተሳካልኝም፡፡
በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር የወለጋን ተፈናቃዮች ጨምሮ ከአበርገሌና ፃግብጂ ወረዳዎች የተፈናቀሉ 67ሺህ ወገኖች ይገኛሉ፣ አብዛኛዎቹ ከማህበረሰቡ ጋር የሚኖሩ ሲሆን፣ 17ሺህ የሚሆኑት ደግሞ ማይቡሊት፣ ሜቴክ፣ ጥርቂና ወለህ በሚባሉ መጠለያ ጣቢያዎች ይኖራሉ፡፡

ፎቶ ከማህደር፤ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል ምስል Privat
ፎቶ ከማህደር፤ ተፈናቃዮች በአማራ ክልል ደባርቅምስል Debark Woreda Food Security/Disaster prevention Office


ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW