ከዓመታት በኋላ የአክሱም ጽዮን ደማቅ አከባበር
ዓርብ፣ ኅዳር 21 2016
ዓመታዊ የአክሱም ጽዮን በዓል ዘንድሮ በአክሱም ከተማ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ሕዝብ በተገኘበት በድምቀት ተከበረ ። ዛሬ በአክሱም የተከበረው ሃይማኖታዊ የአክሱም ጽዮን በዓል፥ ከዓመታት በኋላ ለመጀመርያ ግዜ፥ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ በርከት ያሉ እንግዶች የታደሙበት ሆኗል። በዓሉ ከሃይማኖታዊ ትርጉሙ ባለፈ፥ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ወደቀድሞ መመለስ ላይ ትልቅ ሚና እንዳለው ይገለፃል። ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በዓሉ ለማክበር አክሱም የተገኙት አነጋግረናል።
ሁሌም ኅዳር 21 የአክሱም ጽዮን ዓመታዊ በዓል ሲከበር ትደምቅ የነበረችው ታሪካዊቷ አክሱም ከተማ ባለፊት የጦርነት ዓመታት የቀድሞ ሁኔታዋ አጥታ ቆይታለች። ከትግራዩ ጦርነት መቆም በኋላ በተለየ ድባብ የአክሱም ፅዮን በዓል ዛሬ በከተማዋ በድምቀት ሲከቀር የዋለ ሲሆን፥ እንደቀድሞው በርከት ያሉ የሀገር ውስጥ እና ውጭ እንግዶች ለበዓሉ በብዛት ተገኝተዋል። ከሦስት ዓመት በኋላ በተሻለ ድባብ ዛሬ የተከበረው ዓመታዊ የአክሱም ጽዮን ሃይማኖታዊ በዓል፥ ከአዲስ አበባ ጨምሮ ከተለያዩ የኢትዮጵያ ክፍሎች የመጡ በርካታ እንግዶች በብዛት ታድመውበታል።
በጦርነቱ ወቅት የወደመው የአክሱም አውሮፕላን ማረፍያ አሁንም ባለመጠገኑና ወደ ሥራ ባለመመለሱ፥ እንግዶች ወደ ከተማዋ የሚደርሱት በመኪና ጉዞ ሲሆን፥ በአክሱም ከተማ መግቢያዎች የከተማዋ ወጣቶች ሁሌም እንደሚያደርጉት የእንግዶች እግር እያጠቡ ሲቀበሉ ተመልክተናል።
በዓሉ ከሃይማኖታዊ ትርጉሙ ባለፈ፥ የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነት ወደቀድሞ መመለስ ላይ ትልቅ ሚና እንዳለው ይገለፃል። ከተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በዓሉ ለማክበር አክሱም የተገኙት አነጋግረናል።
ከሩቅ ለሚመጣው ብቻ ሳይሆን በትግራይ ውስጥም ቢሆን ባለፉት ዓመታት የትራንስፖርት አገልግሎት መስተጓጐል ስለነበረ በርካቶች የቀድሞ ልማዳቸው አቁመው ቆይተው ነበር። ከመቐለ ለበዓሉ አክሱም መጥቶ ያገኘነው ሙልጌታ ገብረ፣ ሁኔታው ልዩ ደስታ ፈጥሮለታል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ