1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከዓመታት በፊት በውሃ ሙላት የፈናቀሉት የዳሰነች ነዋሪዎች ችግር ላይ ናቸው

ዓርብ፣ ግንቦት 16 2016

በአሁኑ ጊዜ ከዳሰነች ወረዳ 40 ቀበሌዎች 28ቱ፤ማለትም ከወረዳው የቆዳ ስፋት 65 በመቶው በውሃ ተውጦ እንደሚገኝ ኮሚሽኑ ጠቁሟል፡፡ ከዚህ አኳያ ተፈናቃዮችን ወደ መደበኛ ኑሮ በመመለስ በዘላቂነት ለማቋቋም የተጠናከሩ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ መጠቆሙን የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡

በደቡብ ኦሞ ዞን የውሃ ሙላት የዛሬ ዓመት
በደቡብ ኦሞ ዞን የውሃ ሙላት የዛሬ ዓመትምስል South Omo Zone Government

ከዓመታት በፊት በውሃ ሙላት የፈናቀሉት የዳሰነች ነዋሪዎች ችግር ላይ ናቸው

This browser does not support the audio element.

የኦሞ ወንዝ ተፈናቃዮች አቤቱታ

 

ወይዘሮ ኝቤት ሎኩ እና አቶ ቱቢ ሞርቲ  ከዛሬ አራት ዓመት በፊት በደቡብ ኦሞ ዞን ዳሰነች ወረዳ ነብረሙስ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ይኖሩ እንደነበር ይናገራሉ ፡፡  በ2012 ዓም ቀበሌያቸው በኦሞ ወንዝና በቱርካና ሐይቅ  ሙላት በውሃ አካል መሸፈኑን ተከትሎ መንደራቸው ትተው ወጡ  ፡፡ ከዚያን ጊዜ አንስቶ ወደ አካባቢያቸው መመለስ አስቸጋሪ እንደሆነባቸው የጠቀሱት ተፈናቃዮቹ “ አሁን ላይ ኑሯቸንን   በመጠለያ ጣቢያዎች እየገፋን እንገኛን ፡፡ ቀደምሲል የነበሩ የትምህርት ፣ የጤና እና ሌሎች ማህበራዊ አገልግሎቶች በውሃው ሙላት ለጉዳት በመዳረጋቸው በችግር ውስጥ እንገኛለን ፡፡ በእርግጥ በመጠለያው ጣቢያዎቹ የዕለት ቀለብ እየተሰጠን ይገኛል ፡፡ እኛ ግን በመጠለያዎቹ ውስጥ የመቆየት ፍላጎት የለንም ፡፡ በዘላቂነት በመቋቋም ከዚህ ለመውጣት በሚመለከተው አካል በኩል ድጋፍ አላገኘንም “ ብለዋል ፡፡በደቡብ ከ62 ሺህ በላይ ሰዎች በወንዝ ሙላት ተፈናቀሉ 

ትኩረት ያሻዋል የሚለው የኢሰመኮ ሪፖርት

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ትኩረት አላገኙም ባላቸው የዳሰነች ተፈናቃዮች ያሉበትን ሁኔታ አስመልክቶ ባለ 26 ገፅ ሪፖርት ይፋ አድርጓል ፡፡ በወረዳ ከ2012 እስከ 2016  ዓ.ም ድረስ በኦሞ ወንዝ ሙላት ምክንያት በሰዎች፣ በእንስሳት፣ በሰብል፣ በግል ንብረቶች እና በመንግሥት አገልግሎት መስጫ ተቋማት ላይ የተለያዩ ጉዳቶች መድረሳቸውን ኮሚሽኑ በሪፖርት ጠቅሷል ፡፡

ወይዘሮ ራኬብ መሰለ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ምክትል ኮሚሽነር የዛሬ ሁለት ዓመት መግለጫ ሲሰጡምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

አሁን ላይም በወረዳው ካሉት 40 ቀበሌዎች 28ቱ ከጠቅላላው የወረዳው የቆዳ ስፋት 65 በመቶው በውሃ ተውጠው እንደሚገኙ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ ጠቁሟል ፡፡ ከዚህ አኳያ ተፈናቃዮችን ወደ መደበኛ ኑሮ በመመለስ በዘላቂነት ለማቋቋም የተጠናከሩ ሥራዎችን ማከናወን እንደሚያስፈልግ ኮሚሽኑ በሪፖርቱ መጠቆሙን የኮሚሽኑ ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ መሰለ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል ፡፡ከኦሞ ወንዝ በተነሳዉ ጎርፍ ከ15 ሺህ በላይ ሰዉ ተፈናቀለ

በተፈናቃዮቹ ሁኔታ ላይ በአንዳንድ የሰብአዊ መብቶች ዙሪያ  ላይ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻሎች መኖራቸውን የጠቀሱት ምክትል ዋና ኮሚሽነር ራኬብ “ ነገር ግን በተቻለ መጠንና ፍጥነት የምግብ፣ የውሃ፣ የመጠለያ፣ የሕክምና እና ሌሎች የጤና አገልግሎቶች፣ የንጽሕና፣ የትምህርት እና ሌሎች አስፈላጊ ማኅበራዊ አገልግሎቶችን ያካተተ በቂ የሰብአዊ ድጋፍ የማግኘት መብቶች ላይ ክፍተቶች መኖራቸውን ያሳያል። በተጨማሪም ተፈናቃዮችን በቋሚነት በማቋቋም ረገድ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግሥት በኩል የተጀመሩ ሥራዎች መጠናከር አለባቸው “ ብለዋል ፡፡

ሥለመልሶ ማቋቋም የአካባቢው አስተዳደር  ምን ይላሉ ?

ተፈናቃዮቹ በቅድሚያ ህይወታቸውን ከውሃ ለመታደግ ትኩረት መስጠቱን የጠቀሰው የደቡብ ኦሞ ዞን የአደጋ ሥጋት ሥራ አመራር መምሪያ አሁን ላይ አሥፈላጊውን ዕለት ደራሽ ድጋፍ እያደረገ እንደሚገኝ የመምሪያው ሃላፊ አቶ ኤርሚያስ ኖንጎዲዮ ገልጸዋል ፡፡

የኦሞ ወንዝ ሙላት ከዛሬ ሁለት ዓመት በፊት በዳሰነች ያደረሰው መጥለቅለቅ ምስል Shewangizaw Wegayehu

አቶ ኤርሚያስ እንደሚሉት ተፈናቃዮቹ በ12 የመጠለያ ጣቢያዎች ከሠፈሩበት ከ2012 ዓም ጀምሮ  ምግብና ምግብ ነክ ድጋፎችን እየተደረጉ እንደሚገኙ ተናግረዋል ፡፡አስቸኳይ ድጋፍ የሚሹት የዳሰነች ተፈናቃዮች

ተፈናቃዮቹን በዘላቂነት በማቋቋም ወደ መደበኛ ኑሯቸው ለመመለስ ድጋፍ አልተደረገላቸውም በሚለው የተፈናቃዮቹ ቅሬታም ሆነ ከኢሰመኮ በቀረበው ጥቆማ ዙሪያ በዶቼ ቬለ የተጠየቁት አቶ ኤርሚያስ “ ኢሰመኮ ባወጣው ሪፖርት እኛም እንስማማለን ፡፡ ነገር ግን መልሶ የማቋቋም ተግባር ሠፊ በጀት ይፈልጋል ፡፡  በእኛ በኩል በወረዳ ፣ በዞን እና በክልል ደረጃ በአጭር ፣ በመካከለኛና በረጅም ጊዜ ሊከናወኑ የሚገባቸው ሥራዎችን ለይተናል ወደ ሥራ ገብተናል “ ብለዋል ፡፡

 

ሸዋንግዛው ወጋየሁ

ኂሩት መለሰ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW