1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በዩክሬን ጦርነት ወደ ጀርመን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን

ማክሰኞ፣ ጥር 30 2015

አቶ ውልጫፎ ጦርነቱ ሲቆም ወደ ሀገራቸው መመለስ ይፈልጋሉ። ጦርነቱም በዩክሬን አሸናፊነት ያበቃል ብለው ነው የሚያምኑት። ለአቶ አሸናፊ ጦርነቱ ቢቆም እንኳ የሀገሪቱ ኤኮኖሚ እና ደኅንንነትዋ እንዲህ በቀላሉ ይስተካከላል ብለው አያስቡም። በጦርነቱም ቢሆን ዩክሬንም ሆነች ሩስያ አሸናፊ አይሆኑም ነው ያሉት።

Leipzig Gemeinschaftsunterkunft  für Flüchtlinge
ምስል Jan Woitas/dpa/picture alliance

ከዩክሬን የተሰደዱ ኢትዮጵያውያን በጀርመን

This browser does not support the audio element.

በዩክሬኑ ጦርነት ምክንያት ወደ ተለያዩ ሀገራት ከተሰደዱት ሰዎች መካከል ኢትዮጵያውንም ይገኝበታል። ከጦርነቱ የሸሹ ኢትዮጵያውያን ከተጠጉባቸው የአውሮጳ ሀገራት አንዷ ጀርመን ናት።   
አንድ ዓመት ሊሞላው ሦስት ሳምንታት የቀሩት የዩክሬኑ ጦርነት በአስር ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት አጥፍቷል ፣ ሚሊዮኖችን ከቀያቸው አፈናቅሏል ፤ መጠኑ በውል ያልተነገረ ንብረትም አውድሟል።ጦርነቱ ከተጀመረበት ጊዜ አንስቶ እስካለፈው ዓመት ግንቦት ድረስ ብቻ ከ8 ሚሊዮን ባላይ የተገመቱ ሰዎች ከዩክሬን ተሰደዋል። የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ቁጥርም እንዲሁ በዚሁ ጊዜ 8 ሚሊዮን ደርሶ ነበር። ጦርነቱ ከዩክሬን ካፈናቀላቸው መካከል ኢትዮጵያዊው አቶ ውላጫፎ ነጋሽ እና ቤተሰባቸው ይገኝበታል። ጦርነቱ ሲጀመር ለ35 ዓመታት ከኖሩባት ከዩክሬን ከቤተሰቦቻቸው ጋር ወደ ጀርመን ከተሰደዱ 11 ወራት ተቆጥረዋል። ጦርነቱ በተጀመረ በአስረኛው ቀን ነበር ከዩክሬን የወጡት። 
በአንድ ቀን ጉዞ ከክየቭ ጀርመን መግባት የቻሉትን እነ አቶውልጫፎን ማንሀይም የወሰዷቸው የማያውቋቸው በጎ ፈቃደኛ ጀርመናውያን ሁሉን ነገር ችለው ለሶስት ወር ተኩል ያህል በቤታቸው አኑረዋቸዋል። ከመንግስት እርዳታ ማግኘት ከጀመሩ በኃላ ደግሞ መንግሥት ኪራዩን በሚከፍልላቸው ቤት ውስጥ ነው የሚኖሩት ። መንግስት  ጀርመንኛ ቋንቋ የመማር እድልም ሰጥቷቸዋል። ከዩክሬኑ ጦርነት ሸሽተው አምና ጀርመን የገቡት ሌላው ኢትዮጵያዊ አቶ አሸናፊ ታመነ ዩክሬን ዋና ከተማ ክየቭ በሚገኝ አንድ ድርጅት ውስጥ ተቀጥረው ይሰሩ ነበር። የነጻ ትምህርት እድል አግኝተው በሄዱባት በዩክሬን ለ33 ዓመታት  የኖሩት አቶ አሸናፊ ክየቭን ለቀው ለመውጣት የወሰኑት ጦርነቱ በተጀመረ በጥቂት ቀናት ውስጥ ነበር። ልጆቻቸውን ጥለው መምጣት የከበዳቸው ባለቤታቸው ግን እዚያ ለመቅረት ተገደዱ ።በክራንች ድጋፍ የሚንቀሳቀሱት አቶ አሸናፊ  ብዙ ውጣ ውረድ አሳልፈው ነው ጀርመን የገቡት።  ከክየቭ ወደ ፖላንድ የሚጠጋ አካባቢ  የሚሄድ ባቡር እከሚገኝበት ቦታ ድረስ በመኪና መሄድ ቢችሉም እዚያ ከደረሱ በኋላ እንደ ሌሎቹ ፈጥነው መንቀሳቀስና መጋፋት ባለመቻላቸው ተንገላተዋል። በስተመጨረሻ ግን  በልጆቻቸው እገዛ ተሳክቶላቸዋል። እዚያ ከደሩሱ በኋላም በሃይማኖት ድርጅቶች እርዳታ ከፖላንድ ጀርመን መግባት ችለዋል።
በቤተሰባቸው ግፊት ባለቤታቸውንና ሁለት ወንዶች ልጆቻቸውንም እዚያ ትተው ነበር የወጡት።  መንታ ልጆቻቸው ግን ከዩክሬን መውጣት አልተፈቀደላቸውም ነበር ። ላይፕሺስ ጀርመን እንደገቡም በጎ ፈቃደና ቤተሰቦች ተቀብለዋቸው ጥቂት ቀናት ካረፉ በኋላ ወደ ስደተኞች መጠለያ ካምፕ ገብተው ነበር። እዚያም ሳይስማማቸው ቆይቶ አንዱ ልጃቸው በጤና ችግር ምክንያት ከሀገር መውጣት ተፈቅዶለት እርሳቸው ጋ ከመጣ በኋላ ባለፈው ነሐሴ ቤት  አግኝተው አብረው እየኖሩ ነው። የክየቩ ቤታቸው ባይጎዳም ልጃቸውን ሲሉ እዚያ የቀሩት የባለቤታቸውና የልጃቸው ሁኔታ ግን ያሳስባቸዋል። ወደ ጀርመን ከተሰደዱት ዩክሬናውያን መካከል በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ሀገራቸው የተመለሱ አሉ። ከመካከላቸው የአቶ ውልጫፎ ባለቤት ይገኙበታል። ልጃቸውም ጃፓን የትምህርት እድል አግኝታ ወደዚያው በመሄዷ ጀርመን የቀሩት እርሳቸው ብቻ ናቸው። በንግድ ይተዳደሩ የነበሩት አቶ ውልጫፎ ጦርነቱ ሲቆም ወደ ሀገራቸው መመለስ ይፈልጋሉ። ጦርነቱም በዩክሬን አሸናፊነት ያበቃል ብለው ነው የሚያስቡት። እንደ አቶ ውልጫፎ ሁሉ ለአቶ አሸናፊም  የጦርነቱ መራዘም ጀርመን  የመቆየታቸው ምክንያት ሆኗል ።ጦርነቱ ቢቆም እንኳ የሀገሪቱ ኤኮኖሚ እና ደኅንንነትዋ እንዲህ በቀላሉ ይስተካከላል ብለው አያስቡም። በጦርነቱ ዩክሬንም ሆነች ሩስያ አሸናፊ አይሆኑም ነው የሚሉት። 

የስደተኞች ማቆያ በጀርመን ምስል Xander Heinl/photothek/imago images
ጀርመን ኪርሽዜኦን ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት የተጠለሉ ዩክሬናውያን ምስል Wolfgang Maria Weber/IMAGO

ኂሩት መለሰ
እሸቴ በቀለ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW