1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከሃዲያ ዞን የተለቀቁ የትግራይ ተወላጆች

ዓርብ፣ ሚያዝያ 7 2014

ባለፈው ኣመት ሐምሌ ወር ውስጥ አዲስ አበባ ተይዘው ወደ አፋር ክልል ተወስደው ጥቂት ቀናትን ቆይተው ወደ ደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን ሾኔ ከተማ መወሰዳቸውን የነገሩን ከእስሩ መፈታታቸውን የሚገልፁት አስተያየት ሰጪ፤ባለፈው ማክሰኞ ሚያዚያ 04 ቀን 2014 ዓ.ም። የተለቀቁት ከዘጠኝ ወራት በኋላ መሆኑን አብራርተውልናል፡፡

Karte Äthiopien englisch

ከሃዲያ ዞን የተለቀቁ የትግራይ ተወላጆች

This browser does not support the audio element.

ባለፈው ሐምሌ 2013 ዓ.ም. በሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት የህወሓት ኃይሎች ወደ አጎራባች ክልሎች ሲስፋፉ በደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን ሾኔ በሚባል ስፍራ ለወራት ታስረው የቆዩት የትግራይ ተወላጆች በዚህ ሳምንት መለቀቃቸውን ተናገሩ፡፡ባለፈው ማክሰኞ ተፈተው አዲስ አበባ የገቡ ታሳሪዎች በሰጡት አስተያየት በተያዙበት ሾኔ በምትባል ከተማ የታሰሩ ብቻ ቁጥራቸው ከ1000 በላይ ነው። በዚህ ሳምንት ሚያዚያ 04 ቀን 2014 ዓ.ም. አዲስ አበባ ቃሊቲ መናኻሪያ በአውቶብሶች ተጭነው ከመጡ በኋላ መለቀቃቸውን ለዶቼቬለ ተናግረዋል፡፡ ዶይቼ ቬለ ጉዳዩ የሚመለከታቸው ባለስልጣናት አስተያየታቸውን እንዲሰጡት ያደረገው ሙከሪያ ግን ለዛሬ አልተሳካም፡፡ ስዩም ጌቱ ከአዲስ አበባ ዝርዝር ዘገባ አሰናድቶበታል፡፡
ባለፈው ኣመት ሐምሌ ወር ውስጥ አዲስ አበባ ተይዘው ወደ አፋር ክልል ከተወሰዱ በኋላ ውስን ቀናትን ቆይተው ወደ ደቡብ ክልል ሃዲያ ዞን ሾኔ ከተማ መወሰዳቸውን የነገሩን ከእስሩ መፈታታቸውን የሚገልፁት አስተያየት ሰጪ፤ባለፈው ማክሰኞ ሚያዚያ 04 ቀን 2014 ዓ.ም. የተለቀቁት ከዘጠኝ ወራት በኋላ መሆኑን አብራርተውልናል፡፡ በዚህ ስፍራ የታሰሩት 1300 ያህል የትግራይ ተወላጆች ናቸው የሚሉት እኚህ አስተያየት ሰጪ፤ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀውን ወራትን ባሳለፉበት በስፍራው ሰዎች በተለያዩ ጊዜያት ሲመጡ እንደነበርም አንስተውልናል፡፡ በስፍራው በቆዩባቸው ጊዜያት መቼ እንደሚለቀቁ ሳይነገራቸው መቆየታቸውንና በመጨረሻም ሳይነገራቸው ድንገት መፈታታቸውንም በአስተያየታቸው አክለዋል፡፡ የታሰሩበትን ምክንያት እንደማያውቁ እና ለፍርድ ቤትም እንዳልቀረቡ ነው የሚናገሩት፡፡ 
መንግስት በትግራይ የተናጥል የተኩስ አቁም ማወጁን ተከትሎ ሐምሌ 11 ቀን 2013 ዓ.ም. ወደ ትግራይ ክልል ለመጓዝ ቃሊቲ መናኻሪያ ለመሳፈር በሄዱበት ተይዘው በማግስቱ ለ9 ወር ወደ ቆዩበት ሾኔ ከተማ መወሰዳቸውን የተናገሩት ሌላኛው ከእስሩ መለቀቃቸውን የሚገልጹት አስተያየት ሰጪ ከአዲስ አበባ በተጨማሪ አፋር እና ሌሎች ስፍራዎች ላይ ተይዘውም ወደዚያ መወሰዳቸውን አክለው ነግረውናል፡፡ ለወራት ታስረው የተፈቱቱ አክለውም በሰጡት አስተያየታቸው የሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆን ከጽዳት ጋር ተያይዘው ችግር ውስጥ መቆየታቸውን እና ለፍርድ ቤት ቀርቦ ሚያውቅ ከመካከላቸው አለመኖሩንም ነው የሚናገሩት፡፡ 
ዶይቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ ለመጠየቅ ለመንግስት ኮሚዩኒኬሽን እና ፍትህ ሚኒስቴር ባለስልጣናት በተደጋጋሚ ያደረገው የስልክ ጥሪ ምላሽ አላገኘም፡፡ በፍትህ ሚኒስቴር የአቃቤ ህግ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ፈቃዱ ፀጋ ትናንት ለዛሬ ቀጠሮ ቢሰጡንም በተደጋጋሚ ያደረግንላቸው የስልክ ጥሪ እና መልእክት ምላሽ አላገኘም፡፡
ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ተቋማት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን እና የተመድ ተቋማት የህወሓት ኃይሎች ከባለፈው ሐምሌ ጀምሮ ወደ አጎራባች ክልሎች መስፋፋታቸውን ተከትሎ በትግራይ ተወላጆች ላይ የጁምላ እስር ይፈፀማል በማለት በተለያዩ ጊዜያት ሪፖርት ማውጣታቸው ይታወሳል፡፡
ስዩም ጌቱ 
ኂሩት  መለሰ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW