1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ የሚልቀው የ 2017 ተጨማሪ በጀት አንድምታ

ሰለሞን ሙጬ
ረቡዕ፣ ኅዳር 18 2017

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት ተጨማሪ 582 ቢሊየን ብር በጀት ትናንት ማክሰኛ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።ተጨማሪ በጀቱ የዋጋ ንረትን እንዳያስከትል እና በንግድ ማኅበረሰቡ ላይ ጫና እንዳይፈጥር በምክር ቤቱ አባላት በሥጋትነት ቢነሳም የገንዘብ ሚኒስቴር ግን መንግሥት በጀትን በጥናት ተመስርቶ እና በጥናት መሰራቱን አመልክቷል።

Geldscheine
ምስል DW/E. Bekele Tekle

ከግማሽ ትሪሊዮን ብር በላይ የሚልቀው የ 2017 ተጨማሪ በጀት አንድምታ

This browser does not support the audio element.

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለ2017 በጀት ዓመት በሚኒስትሮች ምክር ቤት ተደግፎ የቀረበለትን ተጨማሪ 582 ቢሊየን ብር በጀት ትናንት ማክሰኛ በአብላጫ ድምጽ አጽድቋል።ይህንን ተከትሎ የዓመቱ አጠቃላይ የሀገሪቱ በጀት ወደ 1.5 ትሪሊዮን ብር ከፍ እንዲል ሆኗል።ተጨማሪ በጀቱ የዋጋ ንረትን እንዳያስከትል እና በንግድ ማኅበረሰቡ ላይ ከልክ በላይ ጫና እንዳይፈጥር በምክር ቤቱ አባላት በሥጋትነት ቢነሳም የገንዘብ ሚኒስቴር መንግሥት ይህንን ጭማሪ በጀት በጥናት ተመስርቶ እና በጥንቃቄ እንዳዘጋጀው አስታውቋል።በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የምጣኔ ሐብት እና የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያዎች ተጨማሪ በጀቱ ከብሔራዊ ባንክ ወደሚገኝ ብድር የሚሄድ ከሆነ በገበያ ንረት ላይ ዐሉታዊ ተጽዕኖ እንደሚኖረው አስጠንቅቀዋል። ባለሙያዌቹ ካለፉት ዓመታት አንፃር የዚህኛው ዓመት በጀት ከፍተኛ ጭማሪ ያሳየበትን ምክንያትም ተጠይቀው ማብራሪያ ሰጥተዋል።

የፀደቀው ተጨማሪ በጀት ለምን ዓላማ የሚውል ነው?

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ሕዳር 12 ቀን 2017 ዓ.ም ባካሄደው 40ኛ መደበኛ ስብሰባው በሙሉ ድምፅ 582 ቢሊየን ብር ተጨማሪ በጀት ያፀደቀ ሲሆን በውሳኔው ላይ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንት ማክሰኞ ሕዳር 17 ቀን 2017 ዓ . ም ተወያይቶበታል።በሦስት ተቃውሞ እና በአምስት ድምፅ ተዐቅቦ በአብላጫ ድምፅ የፀደቀው ተጨማሪ በጀት ለምን ለምን ዓላማ ሊውል እንደተተለም በምክር ቤቱ የመንግሥት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ አብራርተዋል።"ተጨማሪ በጀቱ ለሀገር ውስጥ እና ለውጪ ዕዳ ክፍያ፣ ለማህበራዊ ድጋፍ ክፍያ፣ ለካፒታል ፕሮጀክቶች ማስተካከያ፣ ለማህበራዊ ሴፍቲኔት ፕሮግራም ማስፋፊያ እንዲሁም የለጪ አሸፋፈን ማስተካከያ የሚውል ይሆናል"።

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሥጋትነት ያነሷቸው ጥያቄዎች

971.2 ቢሊዮን ብር ሆኖ በመደበኛነት ቀርቦ የፀደቀ የነበረው የ 2017 በጀት ውስጥ 612 ቢሊዮን ብሩ ከግብር እና ግብር ነክ ካልሆኑ ምንጮች የሚሰበሰ ሲሆን 358 ቢሊዮን ብር ያህሉ ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ በሚገኝ ብድር የሚሸፈን የበጀት ጉድለት ያለው መሆኑ መገለፁ ይታወቃል። አሁን ተጨማሪ በጀቱ ሲፀድቅ አጠቃላይ የዓመቱ በጀት ከ1.5 ትሪሊየን ብር በላይ ሆኗል። ከዚህ በመነሳት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ሥጋታቸው ገልፀው ነበር።

ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲስ አበባፎቶ ከማኅደርምስል Solomon Muche/DW

"ትንሽ የበዛ መሰለኝ። በፊት ካፀደቅነው ባጀት ከግማሽ በላይ ነው የሚሆነው [ተጨማሪ በጀቱ]። ይህ የዋጋ ንረትን አያባብስም ወይ? "ተጨማሪ በጀት የሚቀርበው ተጨማሪ ገቢ መኖሩ ሲታወቅ ነው"  ገንዘብ ሚኒስቴር የኢትዮጵያ መንግሥት ሐምሌ 22 ቀን 2016  ዓ.ም ገበያ መር የውጭ ምንዛሪ ሥርዓት ተግባራዊ አድርጓል። ይህንን ተከትሎ 27 ቢሊዮን ዶላር ከተለያዩ ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በብድር እና በድጋፍ መገኘቱንም የገንዘብ ሚኒስቴር በቅርቡ አስታውቋል። ይህ ሀብት ከ 3 እስከ 4 ዓመታት የሚለቀቅ ስለመሆኑ ነው የተነገረው። ለተነሱ ጥያቄዎች ምላሽ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ "ተጨማሪ በጀት የሚቀርበው ተጨማሪ ገቢ መኖሩ ሲታመንበት" መሆኑን በመግለጽ፣ መንግሥት ይህንን እንደሚያሳካው እና "እንደምናገኘው እርግጠኛ ሆነን ያመንበትን ገቢ ነው ይዘን የቀረብነው" ብለዋል።

"አንድ በአንድ ሒሳቡ ተሠርቶ እንደምናገኝ በእርግጠኝነት እና በአስተማማኝነት የተረጋገጠ ገቢ ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።
አሁን መንግሥት ተጨማሪ የ2017 በጀት አድርጎ ያቀረበው ከግማሽ ትሪሊየን ብር በላይ ሀብት ትናንት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲቀርብ 281 ቢሊዮን ብር ያህሉ ከግብር የሚመነጭ መሆኑ ተገልጿል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ግን ይህ እንዴት ሆኖ የሚል ጥያቄ እንዲያነሱ አድርጓቸዋል።

የምጣኔ ሐብት እና የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያዎች አስተያየት

ተረበብሾ ያለውን ኢኮኖሚ የበለጠ እንዳይረጋጋ አያደርገውም ወይ? እንደገና ሌላ ተጨማሪ ጫና ማህበረሰቡ ላይ አያመጣም ወይ ? በዚህ ጉዳይ ላይ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡት የፋይናንስና የኢኮኖሚ አማካሪና መምህር የሆኑት አቶ ዳዊት ታደሰ ተጨማሪ በጀቱ እንዴት የሚደጎም ነው የሚለው መሠረታዊ ጉዳይ መሆኑን አብራርተዋል።"በጣም አደገኛ የሚሆነው ይህንን ተጨማሪ በጀት ለመሸፈን መንግሥት ኢኮኖሚው ከሚፈቅደው በላይ ገንዘብ የሚያትም ከሆነ ወይም ደግሞ ከሀገር ውስጥ ባንኮች ወይም ከብሔራዊ ባንክ የሚበደር ከሆነ የዋጋ ንረቱን ሊያባብስ ይችላል"።

በየ ዓመቱ ጭማሪ እያሳየ የመጣው የፌደራል መንግሥቱ በጀት ዕድገቱ እንዳለ ሆኖ በጀት ለዋጋ ንረትና ላልተረጋጋ ምጣኔ ሐብታዊ ቀውስ ምንጭ እንዳይሆን የሀብት ምንጩ ከምን ቢሆን ይበጃል የሚለውን ሌላኛው የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ቴዎድሮስ መኮንን ለዶቼ ቬለ አስረድተዋል።"ተጨማሪም ሆነ አጠቃላይ በጀት ሲወጣ ከግብር ሰብስቦ ነው መንግሥቱ በጀቱን የሚሸፍነው። ግብር ሳይበቃው ከቀረ ወደ እርዳታ ይሄዳል። እርዳታ ካልበቃው ወደ ውጭ ሀገር ብድር ይሄዳል። ያ ካልበቃው ወደ ሀገር ውስጥ ብድር ይሄዳል። ያ ሳይበቃው ከቀረ ከብሔራዊ ባንክ ይበደራል። ከብሔራዊ ባንክ ከተበደረ ዋጋ ንረት አባባሽ ይሆናል" ።

ከብሔራዊ ባንክ በአዲስ መልክ የሚገባ ብር የለም-መንግሥት ከብሔራዊ ባንክ ተበድሮ በአዲስ መልክ ወደ ገበያው የሚያስገባው ገንዘብ አለመኖሩን የጠቀሱት የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ የቀረበው ተጨማሪ በጀት ብዙ አለመሆኑንና የዋጋ ንረትን ለመቀነስም "ፍቱን መድኃኒት ነው" ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል።"ከብሔራዊ ባንክ አንድም ብር በአዲስ መልክ ወደ ኢኮኖሚው የሚገባ የለም። ስለዚህ 'ፊስካል ፖሊሲ' የዋጋ ንረት እንዳይኖር ተደርጎ ነው አዲሱ ማክሮ ኢኮኖሚ ፖሊሲ የተቀረፀው"።

የፀደቀው ተጨማሪ በጀት የዋጋ ንረት ያስከትላል የሚል ስጋት አሳድሯል ምስል Eshete Bekele/DW

አዳዲስ ፕሮጀክቶች የማይኖሩበት ነው የተባለው በጀት

ዋናው በጀት በቀረበበት ወቅት ሌላው አነጋጋሪ የነበረው ጉዳይ በካፒታል በጀትየሚሰሩ አዳዲስ ፕሮጀክቶች እንደማይኖሩ መገለፁ ነበር። በአንጻሩ የመከላከያ በጀት በብዙ እጥፍ መጨመሩን ታውቋል። በተለይ አዲስ የሚጀመሩ የካፒታል ፕሮጀክቶች አለመኖር ስራ እጥነትንና የኑሮ ውድነትን ከመቋቋም አንጻር መነጋገሪያ ሆኖ የቆየ ሲሆን ይህ ጉዳይ በትናንቱ የምክር ቤቱ ውሎም ዳግም ተነስቷል።"መሠረታዊ የሚባሉ የመስኖ ልማት ላይ፣ ግድቦች ላይ፣ አገር አቋራጭ መንገዶች ላይ፣ የኃይል ተቋማት፣ ሆስፒታሎችን፣ ዩኒቨርሲቲዎችን እንደዚህ አይነት መሠረታዊ የሕዝብ መሠረተ ልማቶች ላይ በጀታችንን ፈሰስ ካላደረግን የማብለጭለጭ አይነት ልማት ነው የሚሆነው" ።ይህንን ጥያቄ የማክሮ ኢኮኖሚ ባለሙያው ዶክተር ቴዎድሮስ መኮንንም ይጋሩታል።"ወጪው ምን ላይ ነው አብዛኛው የሚውለው የሚለው ጠቃሚ ነው። እሴት የሚፈጥሩ የመዋዕለ ንዋይ ፍሰቶች ከሆኑ፣ የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ከሆነ የሰው ኃብት ልማት ላይ ከሆነ፣ ጤና ላይ የሚውል ከሆነ መልሶ የመክፈል አቅምን እየገነባ ነው ይህ አገር"። ብለዋል።

የኢትዮጵያ የ2017 በጀት ካለፉት ዓመታት እጅግ ሰፊ ልዩነት ያመጣው ለምንድን ነው?

ኢትዮጵያ ከገጠማት ውስብስብ የፖለቲካዊ፣ የማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ቀውሶች በተጨማሪ በግጭት ውስጥ እያለፈች መሆኑ፣ ጦርነት ያደቀቀው ከፍተኛ የኢኮኖሚ ኪሳራ የተፈጠረባቸው አካባቢዎች ሰፊ መሆናቸውን ግምት ውስጥ በማስገባት ይህ በጀት በጥቂት ዓመታት ልዩነት ውስጥ ለምን ጉልህ ጭማሪ ሊኖረው ቻለ የሚለውን የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያ የሆኑትን አቶ ዳዊት ታደሰን ጠይቀናል።"አንደኛው ከኢኮኖሚ ዕድገት ጋር የተያያዘ ሊሆን ይችላል። ሁለተኛው የሚሆነውከገንዘብ የመግዛት ዐቅም መዳከም ጋር የሚያያዝ ሊሆን ይችላል፤ እና ከዋጋ ንረት ጋር የሚያያዝ ሊሆን ይችላል"። በማለት መልሰዋል።

የኢትዮጵያ የ2017 በጀት ካለፉት ዓመታት እጅግ ሰፊ ልዩነት አለውምስል Solomon Muchie/DW

መንግሥት ሐምሌ 2016 ላይ ባደረገው አጠቃላይ የውጭ ምንዛሪ ማሻሻያ እርምጃ ሕብረተሰቡ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ መደረጉንና መሰረታዊ ምርቶች ማለትም ነዳጅ፣ ማዳበሪያ፣ የምግብ ዘይት፣ መድኃኒት እንዲሁም የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ እንደሚደጎም የገንዘብ ሚኒስትሩ አሕመድ ሽዴ ትናንት በጀቱ ከመጽደቁ በፊት ለምክር ቤቱ አብራርተዋል።"አሁን ባቀረብነው ተጨማሪ በጀት መንግሥት ዝቅተኛ ገቢ ላለው ማህበረሰብ የሰጠው ትኩረት እጅግ በጣም ከፍተኛ መሆኑን ነው የሚያሳየው" ።

መንግሥት አስቀድሞ በፀደቀለት አንድ ትሪሊዮን ብር ገደማ የ2017 በጀት 451 ቢሊዮን ብሩን ለመደበኛ ወጪ፣ 283.2 ቢሊዮን ብሩን ለካፒታል ወጪ፣ 222.7 ቢሊዮን ብሩን ለክልል መንግሥታት ድጋፍ እንዲሁም 140 ቢሊዮን ብሩን ለዘላቂ የልማት ግቦች ማስፈጸሚያ መመደቡ ይታወቃል።

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።


ሰለሞን ሙጨ
ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW