1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ከግድያ ሙከራው በኋላ ይበልጥ ድጋፍን ያገኙት ዶናልድ ትራምፕ

ረቡዕ፣ ሐምሌ 10 2016

የአሜሪካው የደህንነት ቢሮ፣ ኢራን በዶናልድ ትራምፕ ላይ የግድያ ሙከራ ለማድረግ እያሴረች መሆኑን የሚገልጹ መረጃወች እንደደረሱትም ተገልጿል። በዚህም ምክንያት በዶናልድ ትራምፕ ጥበቃ ላይ የበለጠ የማጠናከሪያ እርምጃ መውሰዱ ተጠቁሟል።

USA Butler Trump nach Schüssen Faust
ምስል Evan Vucci/AP Photo/picture alliance

የናልድ ትራምፕ ድጋፍ እየጨመረ ነው መባሉን

This browser does not support the audio element.

ኢራን ዶናልድ ትራምፕን ለመግደል እያሴረች መሆኑን የሚገልጽ መረጃ የደረሰው የአሜሪካ የደህንነት ቢሮ ጥበቃውን የበለጠ ማጠናከሩ ተገለጸ። ዶናልድ ትራምፕን የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ አድርጎ የመረጠው የሪፐብሊካን ጉባኤም ከፍተኛ ጥበቃ እየተደረገለት በመካሄድ ላይ ይገኛል። በዚሁ ጉባኤም ላይ የኦሃዮውን እንደራሴ ጄ ዲ ቫንስን በእጩ ም/ል ፕሬዝዳንትነት መምረጣቸውን ይፋ አድርገዋል። ዶናልድ ትራምፕ በፖለቲካውም ሆነ በፍርድ ቤት ክርክሩ እየቀናቸው ይገኛል። 
ዶናልድ ትራምፕ በከፍተኛ ጥበቃ ታጅበው፣ ጆሯቸውን በፕላስተር ታሽገው የታደሙበት፣ የሪፐብሊካን ጉባኤ ከወትሮው የበለጠ የደመቀ፣ የተለየ ድጋፍም ያገኙበት ሆኖ ቀጥሏል። ጉባኤው የሪፐብሊካን ፓርቲ ዶናልድ ትራምፕ የፕሬዝዳንት እጩው መሆናቸውን ያሳወቀበት ነው። 
ይሄንኑ ተከትሎም ዶናልድ ትራምፕ የኦሃዮውን እንደራሴ ጄ ዲ ቫንስን በም/ል ፕሬዝዳንት እጩነት መርጠዋል። የም/ል ፕሬዝዳንት እጩው ትራምፕን ይቃወሙ ከነበሩ ወግ አጥባቂ ሪፐብሊካኖች አንዱ ነበሩ። በሂደት የትራምፕ ቀንደኛ ደጋፊ የሆኑት ጄ ዲ ቫንስ ፤ ‘ከምንም በፊት አሜሪካ’ የሚለው እሳቤ አቀንቃኝ ከመሆናቸው ሌላ የትራምፕ አጀንዳወች ዋና ደጋፊ ናቸው።
በዚሁ ጉባኤ ላይ ዶናልድ ትራምፕን ጨምሮ ሁሉም ተናጋሪወች ንግግራቸውን ከግድያ ሙከራ በኋላ ቀይረው እንደገና መጻፋቸው ተነግሯል። አሁን ሁሉም፤ አሜሪካ ልዩነትን ያከበረ፣ መከባበርና አንድነትን እንድታሰፍን የሚጠይቅ መልክትን ማስተላለፍን መርጠዋል።

ምስል Gene J. Puskar/AP Photo/picture alliance


የአሜሪካው የደህንነት ቢሮ፣ ኢራን በዶናልድ ትራምፕ ላይየግድያ ሙከራ ለማድረግ እያሴረች መሆኑን የሚገልጹ መረጃወች እንደደረሱትም ተገልጿል። በዚህም ምክንያት በዶናልድ ትራምፕ ጥበቃ ላይ የበለጠ የማጠናከሪያ እርምጃ መውሰዱ ተጠቁሟል። ባለፈው ቅዳሜ የተደረገው የግዳይ ሙከራ ከኢራን እቅድ ጋር የሚያገናኘው ነገር መኖር አለመኖሩ የታወቀ ነገር የለም። ይሄ ሁሉ የጥበቃ ለውጥ ተደርጎ እንዴት የቅዳሜውን ሙከራ አስቀድሞ ማስቆም አልተቻለም የሚለው የሁሉም ጥያቄ ሆኗል። እናም የአሜሪካ ፈደራላዊ የምርመራ ቢሮ( ኤፍ ቢ አይ) በፕሬዝዳንታዊው የጥበቃ ሃይል  ላይ ምርመራ ጀምሯል። ኤፍ ቢ ይ አያይዞም የግድያ ሙከራውን ተከትሎ የበቀል ጥቃት ሊወስዱና ብጥብጦች ሊፈጥሩ የሚችሉ ግለሰቦችና ቡድኖች ሊኖሩ እንደሚችሉ ስጋቱን ገልጿል።
ከግድያ ሙከራው በኋላ ዶናልድ ትራምፕ የበለጠ ስኬትን ነው ያገኙት።  የፕሬዝዳንታዊው ውድድር መንፈስም ሆነ ትራምፕ ላይ የነበረው የከረረ ሂስም ጋብ ብሏል። ከዚህ ቀደም በይፋ ድጋፋቸውን ያልገለጹት እንደ ኤለን መስክ ያሉ ሰወችም በይፋ ዶናልድ ትራምፕን እንደሚደግፉ አስታውቀዋል። 
የኦናልድ ትራምፕ መንገድ የበለጠ እየቀና የመጣው በፖለቲካው ግብግባቸው ብቻ አይደለም፤ በፍ/ቤት ክሶቻቸው ላይ ጭምር እንጂ። ለወትሮውም በተለያዩ ምክንያቶች ሲጓተት የነበረው፣ ፕሬዝዳንቱ የአሜሪካ ከፍተኛ ምስጢሮችን ወደ ቤታቸውና ሆቴላቸው በመውሰድ ተገቢውን ጥበቃ አላደረጉጉለም የሚለው ክሳቸው ውድቅ ተደርጎላቸዋል። 
በበርካታ ድጋፍ የታጀቡት የሪፐብሊካን ፓርቲ እጩ ዶናልድ ትራምፕ መትረፋቸውን ‘የእግዛብሄር ጣልቃ ገብነት’ ሲሉ ገልጸውታል። ሰኞ የተጀመረው የሪፐብሊካን ጉባኤ ቀጥሎ፤ ነገ ሃሙስ፣ አሜሪካንን ዳግም ታላቅ እናርግ በሚለው መርህ ታጅቦ፣ ዶናልድ ትራምፕ እጩነታቸውን በይፋ በሚቀበሉበት ንግግር ይጠናቀቃል። 
አበበ ፈለቀ
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW