1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከጦርነት ጠባሳዎች በማገገም ላይ ያሉ ወጣቶች

ዓርብ፣ ጥቅምት 23 2016

ከሁለት ዓመት በላይ የዘለቀው እና በትግራይ ክልል የተጀመረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሰላም ስምምነት ከተቋጨ አንድ ዓመት ሆኖታል። ይሁንና ጦርነቱ በተካሄደበት አካባቢ የነበሩ ወጣቶች ፣ጦርነቱ ካስከተለባቸው የስነ ልቦና ችግሮች ለማገገም ገና ብዙ ጊዜ እንደሚሹ ገልጸውልናል።

ባንዲራ የያዙ ሰዎች
ባንዲራ የያዙ ሰዎችምስል Eduardo Soteras/AFP

ከጦርነት ጠባሳዎች በማገገም ላይ ያሉ ወጣቶች

This browser does not support the audio element.

« ጦርነቱ ባይኖር ኖሮ እህቴን አላጣም»

ከዋኒ ዛሬ የ28 ዓመት ወጣት ነው። በአሁኑ ሰዓት መቀሌ ከሚገኙ የስደተኛ መጠለያዎች «70 ካሬ » ተብሎ በሚጠራው ከእናቱ፣ ከእህቱ እና ከአጎቱ ልጆች ጋር ይኖራል። « ከምዕራብ ትግራይ ነው ተፈናቅለን ወደዚህ አካባቢ የመጣነው» የሚለው ከዋኒ ከጦርነቱ በፊት በአዲግራት ዮንቨርስቲ መምህር እንደነበር ነግሮናል። መለስ ብሎ ሲያስታውስ በጦርነቱ ስራውን ብቻ ሳይሆን የቤተሰቡንም አባል አጥቷል። « ብዙ ዋጋ አስከፍሎናል። እህቴን እንዳታ ሆኛለሁ። ጦርነቱ ባይነሳ ኖሮ የመድኃኒት እጥረት አያጋጥምም ነበር። » ይላል አሁንም የተስፋ መቁረጥ ስሜት የሚታይበት ከዋኒ። ወጣቱ የሚቀጥለው ሳምንት ቀድሞ ወደሚያስተምርበት አዲግራት ዮንቨርስቲ የመመለስ እቅድ አለው። ይህን ከማድረጉ በፊት ግን መታከም ይፈልጋል።« ጦርነቱ ብዙ የስነ ልቦና ቁስል ትቶልን አልፏል » የሚለው ከዋኒ የስነ ልቦና ባለሙያ ድጋፍ እንደሚሻ በግልፅ ይናገራል። « ፌስ ቡክ ላይ የስነ ልቦና ድጋፍ ያስፈልገኛል ብዬ በድፍረት ፅፌያለሁ። ምናልባት አብዷል ሊሉ ይችላሉ። እኔ ግን ርዳታ እንደሚያስፈልገኝ አውቄ ጠይቄያለሁ።» እንረዳሀለን ብለው የፃፉሉት ሰዎች ቢኖሩም «በቦታ ርቀት እና ሌሎች ምክንያቶች» እስካሁን ከማንም በነፃ ርዳታ ሳየገኝ መቅረቱን ከዋኒ ገልፆልናል።

በትግራይ ክልል ጦርነት ጉዳት የደረሰባቸው ወጣቶችምስል Million H. Silase/DW

 

የማይካድራው ጠባሳ

ሌላዋ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት  ገፈት ቀማሽ ወጣት ሀገሬ ትባላለች። ሀገሬ  የሶስት ልጆች እናት እና የማይካድራ ከተማ ነዋሪ ናት። ጦርነቱ በእሷ እና በቤተሰቧ ላይ መጥፎ አሻራ ጥሎ ማለፉን ገልፃልናለች። « ባለቤቴ በህይወት የለም። እሱ በሚመታ ሰዓት ለምን ትጮኺያለሽ ብለው መተውኝ ነበር። ግን አሁን ደህና ነኝ። ያው የኑሮው ሁኔታ የሚያግዘን የሚረዳን ስለሌለ ይከብዳል። » ትላለች። ሀገሬ ባለቤቷን ጨምሮ 1700 የሚሆኑ ሰዎች ህይወት ማለፉን እና በቅርቡ ሶስት ዓመት እንደሚሆናቸው ትናገራለች። የእሷም ባለቤት የተገደለው ጥቅምት 30 ቀን በነበረ እና ብሔርን መሰረት ባደረገ የድምላ ግድያ ነው። ምንም እንኳን በትግራይ ተዋጊዎች እና በመከላከያ ሰራዊት መካከል ጦርነት እየተካሄደ የነበረ ቢሆንም ሀገሬ ጦርነቱ እነሱ ጋር ይደርሳል የሚል ስጋት በወቅቱ እንዳልነበራት ነው የነገረችን። « እኛ አብረን የምንኖር ሰዎች ስለሆንን ሰላም ነው ብለን ነበር። ያኔ ሲመጡ ግን የአማራ ቤት የቱ ነው እየተባለ እና አብረውን የነበሩ የትግሬ ነዋሪዎች ናቸው ሲጠቁሙ የነበሩት»

ከማይካድራ የጅምላ ግድያ የተረፉ ቁጥለኞች በጎንደር ዩንቨርስቲ ህክምና ሲደረግላቸውምስል EDUARDO SOTERAS/AFP

በማይካድራ ማንነት ላይ ያተኮረ የጅምላ ጭፍጨፋ መካሄዱን የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን እና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በወቅቱ ዘግበዋል። የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) በወቅቱ ይፋ እንዳደረገው ቢያንስ 600 ሰዎች የዚህ ጥቃት ሰላባ እንደሆኑ እና ቁጥሩም ከዚያ በላይ ሊሆን እንደሚችል አስታውቋል። ዛሬ በማይካድራ ምን የተለወጠ ነገር አለ? የሰላም ስምምነቱ ያመጣው ፋይዳ ምን ይሆን? ማህበረሰቡስ ይቅር ተባብሎ መኖር ችሎ ይሆን?

ማይካድራ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ

« ከግድያው በኋላ ሲገድሉ ያላደሩ ትግሬዎች ዛሬም አብረውን አሉ። ደብቀው ያሳደሩን ፣ እኛን አይዟችሁ ብለው ትግሬ ናቸው ብለው ዋሽተው ያሳደሩን አሉ። እነዛ አረመኔዎች ግን ከኛ ጋር የሉም። አናያቸውም።» ትላለች ሀገሬ። ይህ የግድ በሰላም ስምምነቱ የመጣ እንዳልሆነም ትናገራለች።

በትግራይ ክልልየተጀመረው ጦርነት ወደ አጎራባች የአማራ እና አፋር ክልሎች ዘልቆ የበርካታ ሰዎች ህይወት አጥፍቷል ንብረትም አውድሟል።  በወቅቱ የ16 ዓመት ወጣት የነበረው አሊ በዚህ እድሜው ብዙ ለማየት ተገዷል። ወጣቱ በአፋር ክልል ዞን 1 ውስጥ ካሳጊታ የሚባለው ቀበሌ ነዋሪ ነው። በጦርነት ጊዜ የነበረውን መለስ ብለ ሲያስታውስ  « ዕለቱ ማክሰኞ እና የገበያ ቀን ነበር። እናቴ እዛ ገበያ ላይ ነበረች። ኃላም ተመታ ህይወቷ ሊያልፍ ችሏል።» ይላል።

ይህ ብቻ አይደለም።  «ቤታችን ሁሉ ወድሟል።» ይላል አሊ። በዚህም ምክንያት ተፈናቅለው የነበሩ ሲሆን ጦርነቱ ካበቃ በኋላ ወደ ቀያቸው ተመልሰዋል። ብዙም ሳይቆዩ ሌላ ነገር ተከሰተ። በጦርነት በተቀበሩ ፈንጂዎች  « ከአራት ወር ገደማ በፊት» የእህቱ ልጅ ህይወት አልፏል። አሊ አሁን የሚኖረው እዛው ዞን 1 ውስጥ ከታላቅ እህቱ ጋር ነው። ዛሬ18 ዓመት የሆነው ይህ ወጣት ትልቅ ምኞቱ ከሚመለከተው አካል የመልሶ መቋቋም እንዲደረግላቸው ነው። 

በትግራይ ክልል የተጀመረው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በአጎራባች ክልሎች አፋር እና አማራ ዘልቆ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል። አባላ አፋር ክልል የደረሰ ውድመት እዚህ ላይ ይታያልምስል DW

 

በጦርነት የሥነ ልቦና ቀውስ ለደረሰባቸው የሚደረግ የሥነ ልቦና ድጋፍ

ሳሙኤል ገብረማርያም ለወጣቶች የስብዕና ማጎልበቻ እና የስነ ልቦና ድጋፍ የሚያደርግ ወጣት ነው። ያደገው የሚኖረው እና የሚሰራው መቀሌ ውስጥ ሲሆን 29 ዓመቱ ነው። ላለፉት አምስት ዓመታት ስብዕናን ማጎልበት ላይ ይሰራ የነበረው ወጣት ከጦርነቱ በኋላ የስነ ልቦና ድጋፍ መስጠትን ይበልጥ አጠናክሯል።« ከሰላም ስምምነቱ በኋላ የበለጠ ተደራጅተን ለወጣቶች በየሳምንቱ የሚሰጥ የምክር አገልግሎት አለን።» ይላል። ይህም የስነ ልቦና እና የስብዕና ማጎልበቻው ድጋፋ በተናጥል እና በቡድን የሚሰጥ እንደሆነ ሳሙኤል ገልፆልናል። ከወጣቶች ጋር ሳሙኤል ሲወያይ ብዙውን ጊዜ የታዘበው ተስፋ የመቁረጥ ስሜት፤ ቶሎ የመናደድ እና የተለያዩ የባሀሪ ለውጦች ናቸው። «ብዙ ራሳቸውን ሊያጠፉ ይፈልጉ የነበሩ ወጣቶችም ገጥመውኛል» ይላል። እሱም እንደ ሌሎች ወጣቶች በተመሳሳይ ሁኔታ ውስጥ  በማለፉ ለሌሎች የሥነ ልቦና ድጋፍ ለማድረግ አልከበደውም። « እኔን የረዱኝ እንደዚህ አይነት ችግር ሲፈጠሩ ራሳችንን እንዴት ማብቃት እንደምንችል ያነበብኳቸው መፅሀፎች ናቸው እንጂ እኔም እንደ ሌሎች ወጣቶች የጦርነቱ ተጎጂ ነኝ።» የሚለው ሳሙኤል ከተጎጂዎቹ አንዱ መሆኑም ሌሎች ያለፉበትን ሲናገሩ ይበልጥ ለመረዳት እንደሚቀለው ይናገራል።

በሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት የተፈናቀሉ አሁንም በርካታ ርዳታ የሚሹ ሰዎች አሉምስል Eduardo Soteras/AFP/Getty Images

ሳሙኤል እንደገለጸልን የአንዳንድ ወጣቶች የስነ ልቦና ቀውስ በጣም ከባድ ከመሆኑ የተነሳ መድኃኒት ያሻል። ይሁንና «አሁን ላይ ለዚህ መድኃኒት የማግኘት እድሉ የተሻለ ነው» ይላል። ሳሙኤል የስነ ልቦና ጉዳት ለደረሰባቸው ወጣቶች መልዕክት አለው። « የሥነ ልቦና ችግራችንን ከደበቅነው ቆይቶ ሊጎዳን ስለሚችል በተቻለ መጠን ወደ አቅራቢያችን ያለ የጤና ተቋማት መሄድ ይኖርብናል»  ሲል ሌሎች ተጎጂዎችን ያበረታታል።

 

ልደት አበበ

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW