ከጽንፈኛ ኃይሎች ጋር የተፋጠጠችው ማሊ
ቅዳሜ፣ ታኅሣሥ 16 2014
የፈረንሳይ ወታደሮች ከጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓ,ም ጀምሮ በሰሜናዊ ማሊ ውስጥ ጽንፈኛ ኃይሎችን በመከላከሉ ተግባር ላይ ቆይተዋል። ፈረንሳይ ብቻ ሳትሆን ጀርመንም ማሊ ውስጥ ለተመሳሳይ ተግባር ወታደሮቿን አሰማርታለች። ምንም እንኳን የውጭ ወታደሮቹ በተጠቀሰው አካባቢ ቢሰማሩም ጀሃዲስቶቹ በሳህል አካባቢ ማሊ፣ ኒዠርም ሆነ ቡርኪናፋሶ ውስጥ የሚያደርሱት ጥቃት አልተገታም። በዚህ መሀል ፈረንሳይ ወታደሮቿን ከማሊ ለማውጣት ወሰነች። የማሊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አብዱላይ ዲፖ ሀገራቸው በውጭ ሃገራት የጸጥታ ኃይሎች ድጋፍ ላይ ለዘለዓለም ተደግፋ መኖር የለብትም ባይ ናቸው። የፈረንሳይ ወታደሮች ለማሊ ለከፈሉት መስዋዕትነት እውቅና እንደሚሰጡ በማመልከትም ከውጭ የሚገኝ ማንኛውም ርዳታ በአንድም ሆነ በሌላ ምክንያት ላይ ያነጣጠረ መሆኑን መረዳት ግድ እንደሆነም ያመለክታሉ። ፈረንሳይ በሳህል አካባቢ የምታካሂደውን ዘመቻ በመጪው ሐምሌ ወር እንደምታበቃ ፕሬዝደንት ኢማኑዌል ማክሮ የገለጹ ሲሆን፤ ሀገራቸው ማሊ ውስጥ ያላትን ወታደራዊ የጦር ሰፈር ሁሉ እንደምትዘጋም አመልክተዋል። ከሰሜናዊ ማሊ የፈረንሳይ ወታደሮች መውጣት መጀመራቸውም በሳህል አካባቢ ከጽንፈኞች ጋር የሚደረገው ውጊያ ፓሪስ ማቆሟን አመላካች ነው ተብሏል። ከኪዳል እና ተሳሊት ጦር ሰፈሮችም ለቀዋል። ዶቼ ቬለ ከአክራ ጋና በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የጸረ ሽብር ትግል ተንታኙ ሙታሩ ሙሙኒ እንደሚሉት የፈረንሳይ ወታደሮች በአካባቢው መገኘት ያልተመቻቸው የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት በመውጣታቸው ደስተኞች ናቸው።
«የፈረንሳይ ከዚህ መልቀቅ በአብዛኛው ጸረ ፈረንሳይ ስሜት ያስከተለው ግፊት መገለጫ ነው። በበርካታ የምዕራብ አፍሪቃ ሃገራት የፈረንሳይ ወታደሮች ከበባ ውስጥ የሚገቡበት ጊዜ አለ፤ በጽንፈኛ ቡድኖች ሳይሆን የፈረንሳይ ወታደሮች በአካባቢው መገኘት ሁኔታውን ከሚያሻሽለው ይልቅ ያባብሰዋል ብለው በሚያስቡ የአካባቢ ሰዎች ማለት ነው።»
እሳቸው እንደሚሉትም የፈረንሳይ ወታደሮች ማሊ ውስጥ በቆዩባቸው ዘጠኝ ዓመታት የጸጥታ መደፍረስ ስጋቱን በማባባስ እንደውም በአስጊ ሁኔታ ላይ ጥሎታል። በአሁኑ ወቅትም የማሊ የጦር ኃይል ራሳቸውን መልሰው በቡድን ያደራጁትን እና ከጎርጎሪዮሳዊው 2013 ዓ,ም ወዲህ ወደ ደቡባዊ ማሊ የተንሰራፉትን ጽንፈኛ ኃይሎች የመከላከል እና የማስወገድ አቅም ይኖረው ይሆን የሚል ስጋት አለ። ፕሬዝደንት ማክሮ ትናንት ሰኞ ወደ ማሊ ሊያደርጉ ያቀዱትን ጉዞ አውሮጳ ውስጥ በተባባሰው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ ይዞታ ምክንያት ሰርዘዋል። የማክሮ ጉዞ ቢሳካ ኖሮ በዴሞክራሲያዊ መንገድ የተመረጡትን የማሊን ፕሬዝደንት በመፈንቅለ መንግሥት ካስወገዱት እና የሽግግር መንግሥቱ መሪ ኮሎኔል አሲሚ ጎይታ ጋር ይወያዩ ነበር። ከመፈንቅለ መንግሥቱ ወዲህ የማሊ እና ፈረንሳይ ግንኙነት ውጥረት ሰፍኖበታል። የፈረንሳይ ወታደሮች ከማሊ መውጣት ለሩሲያ መንገድ ከፍቷል የሚለውም ሌላ ስጋት ነው። ዋግነር የተባለው የሩሲያ የግል ወታደራዊ አገልግሎት ቡድን ታጣቂዎቹን ማሊ ውስጥ የማሰማራቱ ርምጃ ፈረንሳይን ብቻ ሳይሆን ዋሽንግተንንም ሃሳብ ውስጥ ከቷታል። የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ እንዳደረገው ቡድኑ ወታደሮቹን ካሰማራ በወር 10 ሚሊየን የአሜሪካን ዶላር ይከፈለዋል። አንቶኒ ብሊንከን፤ በአዋኪ እንቅስቃሴያቸው እና በሰብዓዊ መብት ረገጣቸው የሚታወቁት የዋግነር ወታደሮች ማሊ ውስጥ ሰላም ከማምጣት ይልቅ ሀገሪቱን እንደውም ወደባሰ አለመረጋጋት ይከቷታል ማለታቸውም ተጠቅሷል። የማሊ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲፖ ግን ሀገራቸው ከተባለው አካል ጋር ምን አይነት ውል አልፈጸመችም ነው ያሉት። ይልቁንም ማሊን አሁን የሚያሳስባት ጸጥታዋን እንዴት ታረጋግጣለች የሚለው መሆኑንም ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። የፈረንሳይ ወታደሮች መውጣትን ተከትሎ የሚፈጠረው ክፍተት አሳሳቢ በመሆኑም አወጣጣቸው በዝግታ ቢሆን ባይ ናቸው። የምዕራብ አፍሪቃ እና ሳህል አካባቢ የተመድ ልዩ መልእክተኛ አናዲፍ ካቲር መህማት ሳልህ በአንጻሩ የመንግሥታቱ ድርጅት በሃገራት የውስጥ ጉዳይም ሆነ በሚመሰርቱት ግንኙነት ጣልቃ መግባት እንደማይችል በማመልከት፤ በተጠቀሰው አካባቢ ያለውን ሁኔታ ለማስተካከል የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድጋፍ ያስፈልጋል ባይ ናቸው። በዚህ መሀልም ቻድ ወደማሊ አንድ ሺህ ሰላም አስከባሪ ወታደሮችን ለመላክ መዘጋጀቷን አስታውቃለች። የቻድ ወታደሮች ሲጨመሩ በሰሜናዊ እና ማዕከላዊ ማሊ የተሰማሩ የመንግሥታቱ ድርጅት የሰላም አስከባሪ ኃይሎች ቁጥር 13 ሺህ ይሆናል።
አይዛክ ካሌድዚ/ ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ