1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ከፍቅርና ጥላቻ ጀርባ ያሉ ሳይንሳዊ ዕውነታዎች

ረቡዕ፣ የካቲት 9 2014

ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሰዎች ፍቅር ውስጥ ሲሆኑ፤ከአመከንዮ፣ከፍርድ እና ከማመዛዘን ጋር የተያያዘው «ሴሬብራል ኮርቴክስ» የተባለው የአንጎል ክፍል አብዛኛው የማይነቃቃ ሲሆን፤ በጥላቻ ጊዜ ግን እነዚህ ክፍሎች በከፍተኛ ሁኔታ ይነቃቃሉ። በዚሀ ጊዜ ሰዎች ሌላኛውን ወገን ለመረዳት ከመሞከር ይልቅ ወደ ትችት እና ወደ ፍርድ ያመዝናሉ።

Symbolbild Liebe
ምስል፦ Colourbox

«ፍቅር ተፈጥሯዊ ሲሆን፤ ጥላቻን ግን ከማህበራዊ መስተጋብር የምንማረው ነው።»

This browser does not support the audio element.


በያዝነው ሳምንት መጀመሪያ በጎርጎሮሳዉያኑ የካቲት 14 ቀን የፍቅረኞች ቀን ወይም «ቫለንታይን  ዴይ »ተከብሯል።በዓሉ ብዙውን ጊዜ ግብዣ እና ስጦታ የፍቅር መግለጫ  ሆኖ  የሚከበር  ቢሆንም፤ የዚህ ቀን መነሻ ለድሆች እና ለምስኪኖች ባለው ልግስና፤ የርህራሄ እና የፍቅር ተምሳሌት ተደርጎ ይታይ የነበረውን ቅዱስ ቫለንታይን የተባለ  ቄስ ህልፈተ ህይወት  ለመዘከር  ነው። በዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅትም ይህንን ቀን መነሻ በማድረግ ከፍቅር ከርህራሄ እና ከጥላቻ ጀርባ ያሉ ሳይንሳዊ ዕውነታዎችን ምን ይመስላሉ የሚለውን  እንዳስሳለን። 
ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ፍቅር፣ ርህራሄ፣  ደግነት እንዲሁም  ጥላቻ  ከሰው ልጅ ታላላቅ መሰረታዊ ስሜቶች መካከል ዋናዋናዎቹ ናቸው።እነዚህ ስሜቶች ሰዎች እንዲከፉና እንዲደሰቱ የማድረግ አቅም አላቸው።
በናይጄሪያ ኢባዳ ዩኒቨርሲቲ የሥነ ልቡና ፕሮፌሰር  የሆኑት ሮቲሚ አኒማሻሁን ለDW  እንደተናገሩት በእነዚህ ስሜቶችና እና በስነ ልቡና ደህንነት መካከል የጠበቀ ግኙነት አለ። በተለይ ፍቅር ለሰው ልጆች ለህልውና ጠንካራ ምክንያት ነው የሚሉት አኒማሻሁን፤ በፍቅር ውስጥ ያሉ ሰዎች ከሌሎቹ ጋር ሲነፃፀሩ በመንፈስ ጭንቀት የመጠቃት ዕድላቸው አነስተኛ  መሆኑንም ተናግረዋል።የስነ አእምሮ  ባለሙያው ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ እንደሚሉት ሰሜታዊነት የአንድ ሰው የአእመሮ ጤንነት ከሚወሰነባቸው ተፈጥራዊ እና መሰረታዊ አቅሞቸ መካከለ  አነዱ ሲሆን፤ ፍቅር ደግሞ ከሰዎች ጋር ላለን መሰተጋብርም ወሳኝ ነው።
እንደ ፕሮፌሰር አኒማሻሁን ገለጻ  ስንወድ ወይም እንደምንወደድ ሲሰማን ሰውነታችን ጥሩ ስሜት ያላቸው እንደ «ኢንዶርፊን» እና «ኦክሲቶሲን» ያሉ አእምሮን የሚመግቡ እና  ጤንነታችንን የሚያጎለብቱ ንጥረ ቅመሞችን ያመነጫል።በሌላ  አነጋገር፣ በፍቅር ውስጥ ያለ አንድ ሰው «ዶፓሚን» (የደስታ ንጥረ ቅመም) እና  «ኦክሲቶሲን » (የፍቅር ንጥረ ቅመም) የተባሉ ንጥረ ቅመሞች አንጎልን ይቆጣጠሩታል ። በዚህ ወቅት አንጎላችን  «ቫሶፕሬሲን» እና «አድሬናሊን» የተባሉ  ንጥረቅመሞችን ወደ ነርቭ ህዋሳቶቻችን በመልልቀቅ የደስታ ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል።
ይህንን በተመለከት በተደረጉ  ጥናቶችም የሚዋደዱ ጥንዶች  ለሥነ ልቦና ህመም የመጋለጥ እድላቸው በጣም አናሳ መሆኑን ገልፀዋል። ፐሮፌሰሩ ። በጥናቱ መሰረት እንደዚህ አይነት ሰዎች ጤናማ እና ደስተኛ ህይወት ያላቸው እንዲሁም ረጅም ዕድሜ የሚኖሩ ሆነው ተገኝተዋል።ይህንን ስሜት ይዞ ለመቆየት ግን  የማህበራዊ ሳይንስ ሊቃውንት እንደሚሉት መተማመን፣መቻቻል፣ አንዱ የአንዱን ስሜት መረዳትን እና ፅናትን ይጠይቃል።የሥነ አእምሮ  ባለሙያው ዶክተር ዳዊት ወንድማገኝ እንደሚሉት ደግሞ ፍቅር  ከአካላዊ ደህንነት በተጨማሪ በማህበራዊና በመንፈሳዊ ህይወታችን ውስጥ በዙ በረከቶቸ አሉት።
ሳይንሳዊ መረጃዎች እንደሚያሳዩት ሰዎች በፍቅር ላይ በሚሆኑበት ወቅት  ከፍርድ እና ከማመዛዘን ጋር የተያያዘው «ሴሬብራል ኮርቴክስ» የተባለው የአንጎል  ክፍል  አብዛኛው የማይነቃቃ ሲሆን፤ በጥላቻ ጊዜ ግን የዚህ አካል አብዛኛው ክፍሎች በከፍተኛ ሁኔታ ይነቃቃሉ።ያ በመሆኑ ስዎች በጥላቻ  ውስጥ ሲሆኑ ሌላኛውን ወገን ለመረዳት ከመሞከር ይልቅ ወደ ትችት እና ወደ ፍርድ ያመዝናሉ።ይህም ላለመግባባት መንሰኤ ይሆናል።እንደ ዶክተር ዳዊት ጥላቻ እንደ ፍቅር ተፈጥሯዊ ሳይሆን፤ ከማህበራዊ መስተጋብር የምንማረው ነው። 
ስለ ፍቅር ሲነሳ ከፍቅረኛና ከትዳር አጋር ከሚገኝ ፆታዊ ፍቅር ባሻገር የቤተሰብና የጓደኛ ፍቅርም በአንድ ሰው ህይወት ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው።ተራማሪዎቹ እንደሚሉት ሰዎች  ከሚወዷቸው ጋር ጊዜ ማሳለፍን ጨምሮ ለራሳቸው ጥሩ ስሜት እንዲሰማቸው የሚያደርጉ በጎ ተግባራትን ሲያከናውኑ፤ «ሃይፖታላመስ»በተባለው የአንጎላችን ክፍል  የሚመረተው እና «ዶፓሚን» የተባለው የደስታ ስሜት የሚፈጥር ንጥረ ቅመም እንዲመረት ያደርጋል። በዚህ የተነሳ ሰፊ የጓደንነት ህይወት  ያላቸው ሰዎች ዝቅተኛ ውጥረት እና የበሽታ መከላከያ ስርአታቸው ጠንካራ ሲሆን፤ ጠንካራ ማህበራዊ ትስስር እና የአእምሮ ጤናንም ያሻሽላል ። ከጓደኞች፣ ቤተሰቦች እና አጋሮች ጋር የተረጋጋ ግንኙነት በተለይ ለወጣቶች በአካላዊ ጤንነት ላይ ከሚያሳድሩት ተፅዕኖ ባሻገር፣ ለራስ ክብር መስጠትን፣ ችግሮችን የመፍታት ዘዴን እና የማህበራዊ ግንኙነት ክህሎቶችን ለማዳበር ስለሚረዱ በጣም አስፈላጊ ናቸው።በአንፃሩ ያለ መወደድና ያለ መፈለግ ስሜት በተለይ በልጆች የወደፊት ህይወት ላይ የሚያሳድረው ተጽዕኖ ከፍተኛ ነው።
በአጠቃላይ ለሌሎች የምናደርገው ደግነት፣ ቅንነት፣ ርህራሄ እና ፍቅር ስለራሳችን ጥሩ ስሜት እንዲሰማን ያደርጋል ። መወደድ ብቻ ሳይሆን የሚወዱትና የሚያስቡለት ሌላ ሰው  ሲኖር፤  ለህይወት የሚሰጥ ዋጋ እንዲሁም የመኖር ፍላጎት እንዲጨምር ያደርጋል። በሌላ በኩል ፍቅር የነገሰበት ቤተሰብ እና ማህበረሰብ ጤናማ እና ሰላማዊ ሀገርን ለመገንባት መሰረት ይሆናል።ነገር ግን "ፍቅር ከስብከት ባለፈ  ልምምድ ይፈልጋል"።ይላሉ ዶክተር ዳዊት ።

ምስል፦ Nikolai Sorokin-Fotolia
ምስል፦ Romy Arroyo Fernandez/NurPhoto/imago images
ምስል፦ Simon Maina/AFP/Getty Images
ምስል፦ Tayfun Coskun/AA/picture alliance


ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው እንዲያደምጡ እንጋብዛለን።


ፀሀይ ጫኔ
ሽዋየ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW