ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት ያስከተለ የጎርፍ አደጋ በአውሮጳ
ማክሰኞ፣ ሐምሌ 13 2013ጀርመንን ጨምሮ በምዕራብ አውሮጳ የተለያዩ ሀገራት ባለፈው ሳምንት ከሰኞ እስከ ረቡዕ በዘለቀው የጎርፍ አደጋ ከፍተኛ ሰብዓዊና ቁሳዊ ጉዳት መድረሱ ሲጠቀስ ቢያንስ 184 ያህል ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ በሺዎች የሚቆጠሩም እስካሁን የደረሱበት እንደማይታወቅ እየተገለፀ ነው:: የሟቾቹ አሃዝ ከዚህ ከፍ ሊል እንደሚችልም የነፍስ አድን ባለሙያዎች አሳስበዋል:: የጎርፍ መጥለቅለቅ ክስተቱ እንደ ጀርመኑ ታላቁ የራየን ወንዝ ያሉ ድንበር ተሻጋሪ የተፋሰሱ ሀገራትንም ያጠቃ ሲሆን በቤልጅየም ኔዘርላንድስ ከፊል ሉክሰምበርግ ብሪታንያ ጣሊያን በኦስትሪያና ስዊትዘርላንድም አደጋው ለበርካቶች ሞትና ከመኖሪያ ቤታቸው መፈናቀል መንስኤ ሆኗል:: በመንገዶች በድልድዮች በተሽከርካሪዎች በኤሌክትሪክና የስልክ መስመሮች በተጨማሪም በውሃና ፍሳሽ ማስተላለፊያ መስመሮችም ላይ ከባድ ጉዳትን አስከትሏል::
ከምሥራቃዊ የፈረንሳይ ግዛት ተነስቶ የምዕራብ ጀርመን ክፍለ ሃገሮችን እንዲሁም እንደ ኖርድ ራየን ቬስት ፋለንና ራየንላንድ ፋልስ የመሳሰሉ አካባቢዎችን ባጠቃው ኃይለኛ የዝናብ ጎርፍ በ 24 ሰዓታት ከ 100-150 በተለይም በራየንፋልስ ከ 207 ሚሊ ሜትር በላይ ከፍታ እንደነበረው የተመዘገበ ሲሆን ይህም በሀገሪቱ ታሪክ ላለፉት መቶ ዓመታት ተከስቶ የማያውቅ ነው ተብሏል:: የዚሁ የጎርፍ ጉዳት ሰለባ ከሆኑት መካከል በኢትዮጵያውያን የተቋቋመው "ሃውስ ሰላም" የተሰኘው የአረጋውያንና አካል ጉዳተኞች እንክብካቤ መስጫ ማዕከል የነርሲንግ ማኔጅመንት ሃላፊ የሆኑት ኢትዮጵያዊው አቶ ቴዎድሮስ ሽመልስ አንዱ ናቸው:: ኤፉርትሽታት ውስጥ በምትገኘው ትንሿ የብሌሰም ከተማ ከአስር አመት በፊት ገዝተው የሚኖሩበት ቤታቸው በጎርፍ መጥለቅለቅ አደጋው ጉዳት ደርሶበት ዛሬ ተፈናቃይ ሆነዋል:: በከተማዋ የሚኖሩ ከ 1800 በላይ ነዋሪዎችም ተመሳሳይ ዕጣ እንደገጠማቸው ለዶይቼ ቨለ ገልፀዋል::በከተማዋ የሚገኘው የውሃ መቀነሻ ግድብ ጎርፉን መቋቋም ተስኖት መሰበሩና በአካባቢው በአንድ የግል የልማት ድርጅት የተቆፈረና 20 ሜትር ያህል ጥልቀት ያለው የአሸዋ ማጣሪያ ጉድጓድ ሞልቶ ውሃው በመፍሰሱ በሁለት አቅጣጫ ከተማዋን ሰብሮ የገባው ጎርፍ በርካታ ቤቶች ተቋማትንና ንብረት ሊያወድም እንደቻለም ነው አቶ ቴዎድሮስ ጨምረው ያብራሩት:: 1600 ያህል የከተማዋ ነዋሪዎች በአንድ ትምህርት ቤት ውስጥ አሁን ላይ ተጠልለው የሚገኙ ሲሆን ከከተማው ከንቲባ ጋር ባደረጉት ውይይትም ነዋሪዎቹን ወደ መኖሪያቸው የመመለሱ እንቅስቃሴ ከመከናወኑ አስቀድሞ የቤቶቹን ደህንነት እንዲሁም መሬቱ ውሃና ጎርፍን የመቋቋም ብቃቱን በፍጥነት በባለሙያዎች የማስጠናቱ ጉዳይ ትኩረት ተሰጥቶት እየተሰራ እንደሆነ አስረድተውናል ሲሉ ገልፀዋል::
በጀርመን ነዋሪ የሆኑ ሌሎች የጉዳቱ ሰለባዎችም ኃይለኛ ዝናብ በቀላቀለው በዚሁ የጎርፍ አደጋ የሚያውቋቸውን ሰዎች በሞት መነጠቃቸው እንዲሁም ለረጅም ዘመን የኖሩበት ቤትና ንብረታቸው በድንገት በመውደሙ ከባድ ድንጋጤና ሃዘን እንደገጠማቸው በእንባ ጭምር ገልፀዋል::"ይህ ቦታ ቀድሞ ወደነበረበት ቦታ የሚመለስ አይመስለኝም:: ለዘመናት የኖርኩበት መኖሪያ ቤቴም ወድሞ ጠፍቷል:: በጣም ልብ ይሰብራል ያሳዝናል:: "
የጀርመኗ መራሄተ መንግሥት አንግላ መርኬልና የሀገሪቱ ከፍተኛ ባለስልጣናት በምዕራብ ጀርመን የተለያዩ አካባቢዎች ባቬሪያና ዛክሰን እንዲሁም ኖርድ ራየን ቬስት ፋለን ክፍለግዛት በሙንስተር አይፍል ጭምር ተዘዋውረው በጎርፉ ጉዳት የደረሰውን ውድመት በጎበኙበት ወቅት በአደጋው ክፉኛ መደንገጣቸውን በመግለጽ ከመኖሪያቸው የተፈናቀሉ ነዋሪዎችን አጽናንተዋል:: መንግሥት ችግሩ በዘላቂነት የሚፈታበትን መንገድ በባለሙያዎች እንደሚያጠናና የጉዳቱ ሰለባዎች መልሰው የሚቋቋሙበትን መንገድ በፍጥነት እንደሚሰራም መርኬል ቃል ገብተዋል::
"የደረሰው ውድመት በቃላት ለመግለጽ የሚከብድ በጣም አስደንጋጭ ነው:: የችግሩን ተጎጂዎች መልሶ ለማቋቋምና ወደ ቀደመው ሕይወታቸው ለመመለስ ሁላችንም እጅ ለእጅ ተያይዘንና ተደጋግፈን መንቀሳቀስ ይኖርብናል::"
በአሁኑ ወቅት የአደጋ ጊዜ ሰራተኞችና በጀርመን የተለያዩ ግዛቶች ነዋሪ የሆኑ በጎ አድራጊ ግለሰቦች በጎርፍ አደጋው የተጎዱ አካባቢዎችን መልሶ ለመቋቋም የውሃ መተላለፊያ ቱቦዎችን የፈራረሱ አካባቢዎችንና ጎርፍ ያመጥውን የቆሻሻ ክምር በማጽዳት ስራ የሚገኙ ሲሆን በተለያዩ መጠለያ ጣቢያዎች ለሚገኙ ተፈናቃዮችም አስፈላጊውን ድጋፍና እንክብካቤ እያደረጉ መሆናቸው ታውቋል:: ወቅቱን ያልጠበቀና ከፍተኛ የዝናብ መጠን የፈጠረው የጎርፍ አደጋ መንስኤ ከሰው ሰራሽ አልያም ከአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያያዥነት ይኖረው ወይም አይኖረው እንደሆነ ለማወቅ በባለሙያዎች እየተጠና ነው::
እንዳልካቸው ፈቃደ
ኂሩት መለሰ