ከ10 ሺህ ብር በላይ በጥሬ መገበያየትን የሚከለክለው አዲሱ ሕግ
ረቡዕ፣ ሰኔ 11 2017
የምጣኔ ሃብትና ገንዘብ አስተዳደር ባለሙያዎች ግን ነገሩ ላይ ጥያቄ አንስተዋል። እንደ የገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ አዲሱ አዋጅ ተግባራዊ የሚደረገው በጥሬ ገንዘብ የሚፈፀም ግብይትን መገደብን ታሳቢ አድርጎ ነው። እንደ አዲሱ ሕግ በአንድ ግብይት የሚፈፀም የጥሬ ገንዘብ ክፍያ ከአስር ሺህ (10,000 ብር) ከበለጠ፣ ትርፉ ብር ለከፋዩ በወጪነት አይያዝም። ገንዘቡን የተቀበለውም የትርፉን ገንዘብ እጥፍ አስተዳደራዊ ቅጣት እንደሚጣልበት ነው የተገለጸው።
አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የገንዘብ አስተዳደር ባለሙያው አቶ አብዱልመናን መሀመድ በዚህ ላይ በሰጡን አስተያየት በጥሬ ገንዘብ ግብይት እንዲፈፀም ምክንያት የሚሆነው በንግድ ስርዓቱ ውስጥ ያለውን ችግር ለመፍታት የተሻለ አማራጭ ሊሆን እንደሚችልና ለሕጉ አስፈላጊነትም ይህ ምክንያት ሊሆን እንደሚችል በአስተያየታቸው አስቀምጠዋል። «ገንዘብን በባንክ ስርዓት ብቻ ማንቀሳቀስ ለደኅንነትና ባንክ ቅንጅት በጣም ይረዳል» የሚሉት ባለሙያው፤ በተለይም ግብር ለመሰብሰብ እና ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውርን ለመግታት የካሽ ገንዘብ ግብይትን መግታት ይጠቅማል ነው ያሉት።
ሌላው አስተያየት ሰጪ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ ዶ/ር አጥላው ዓለሙ በፊናቸው፤ «እኔ የሚመስለኝ በባንክ ስርዓት ገንዘብ ሲዘዋወር ቫትና ታክሱንም ጭምር በቀላሉ ለመቆጣጠር ነው የሚል ግምት አለኝ» በማለት የሕጉ ዓላማ ሊሆን ይችላል ያሉትን መላምት ጠቁመዋል።
ባለሙያዎቹ እየወጣ ነው የተባለው አዲሱ የጥሬ ገንዘብ ግብይት ደንብ ምናልባትም የሰዎችን ነጻነት የሚገድብና ገቢራዊ ለመሆኑም አስቸጋሪ ሊሆን የሚችል ነው የሚለውን አስተያየታቸውን ከአገሪቱ ነባራዊ ሁኔታ ጋር አያይዘው አንስተዋል።
«በዚህ ተገበያይ በዚህ አትገበያይ የሚለው ሕግ ከሰዎች ነጻነት አኳያ ራሱ ግራ አጋቢ ነው» ያሉት አቶ አብዱልመናን የመንግሥት ሚና መሆንና መተኮር ያለበት የገንዘቡን ምንጭ ማጣራት ላይ ብቻ መሆን ነበረበት ይላሉ። ከ10 ሺህ በላይ ያለጥሬ ገንዘብ ግብይትን አስገዳጅ የሚያደርገው ሕጉ አሁናዊ የአገሪቱን ነባራዊ ሁኔታ ያላገናዘበ ይመስላልም በማለት የኢንተርኔትና ሌሎች የባንኮች ተደራሽነትን በጥያቄ ምልክት በማንሳት ገቢራዊነቱንም ተጠራጥረዋል።
«ከእንስሳት እስከ ጤፍ ገቢያ» ያለውን ግብይት በአብነት በማንሳት የሕጉን አስቸጋሪነት የጠቆሙት የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶ/ር አጥላውም በፊናቸው ሕጉ ነባራዊውን የአገሪቱን ሁኔታ ከግንዛቤ ውስጥ ማስገባቱን በጥርጣሬ ነው የሚመለከቱት።
የገንዘብ ሚኒስቴር ባሰናዳው ረቂቅ አዋጅ መሰረት ከ10,000 ብር በላይ በጥሬ ገንዘብ ግብይት እንዳይፈፀም የሚጣለው ግዴታ፣ በመንግሥት መስሪያ ቤቶች፣ በመንግሥት የልማት ድርጅቶች፣ በባንኮችና በማይክሮ ፋይናንስ ድርጅቶች ላይ ተፈጻሚ እንደማይሆን ግን ተጠቁሟል።
ሥዩም ጌቱ
ሸዋዬ ለገሠ
ታምራት ዲንሳ