1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከ2 ከመቶ ያልበለጠው የኮቪድ ክትባት በአፍሪቃ

ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 30 2013

እንደ ዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ አፍሪቃ ውስጥ እስካሁን የተከተበው ሰው ቁጥር ከሁለት ከመቶ ያነሰ ነው። አኅጉሪቱ በቀጣይ ስድስት ወራት 20 ከመቶ ለመከተብ ብታቅድም የእስካሁኑ ግን እጅግ የተንቀረፈፈ ነው።

Uganda  Kampala | Technikindustrie sucht man kreativen Mitteln Corona zu behandeln
ምስል Prof. Vincent Sembetya

ክትባቱ በአኅጉሪቱ እጅግ ጥቂት ነው የተዳረሰው

This browser does not support the audio element.

እንደ ዓለም የጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ አፍሪቃ ውስጥ እስካሁን የተከተበው ሰው ቁጥር ከሁለት ከመቶ ያነሰ ነው። አኅጉሪቱ በቀጣይ ስድስት ወራት 20 ከመቶ ለመከተብ ብታቅድም የእስካሁኑ ግን እጅግ የተንቀረፈፈ ነው። ለአብነት ያህል ኬንያ 50 ሚሊዮን ግድም ነዋሪ ቢኖርም እስካሁን ድረስ 800,000 ነዋሪዎቿ ብቻ ነው የተከተቡት። በተለይ ሕንድ ውስጥ የኮሮና ተሐዋሲ ከፍተኛ ቀውስ በመፍጠሩ የኮሮና ክትባት ወደ ሌሎች ሃገራት መላኩ ተቋርጧል። የዶይቸ ቬለዋ አንቲየ ዲካንስ ባቀረበችው ዘገባ ከናይሮቢ ጎዳናዎች እስከ ኮንጎ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ እያመላለሰች ክትባቱን ለመስጠት ስለተጋረጡ ተግዳሮቶች ታስቃኘናለች።  

የናይሮቢ ጎዳናዎች እንደወትሮ በሰዎች ተጨናንቀው ደመቅ አላሉም። ኬንያ ከአንዱ የእንቅስቃሴ ገደብ ወጣች ሲባል ወደ አንዱ እየገባች ተቸግራለች። በእርግጥ በኮሮና ተሐዋሲ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ኬንያ ውስጥ መቀነስ ያሳያል።  በዚህ መልኩ ይቀንስ እንደሆነ ግን የሚታወቅ ነገር የለም። የክትባቱም ነገር የለም ማለት ይቀላል።   

«በዘመድ ካልሆነ አይገኝም» 

«አስጨንቆናል። አንዴ የተከተቡት ራሱ ሁለተኛ ይከተቡ እንደሆን የሚል ጥያቄም አለን።»

ኬኒያ አንድ ሚሊዮን ክትባት ከኮቫክስ ዓለም አቀፍ የክትባት ማእከል አግንታለች። ኮቫክስ በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ድሃ ሀገራትም ክትባቱን እንዲያገኙ ጥረት ያደርጋል። ሁለተኛ ዙር የክትባት እደላው መጀመሩ ተነግሯል። ሆኖም ሕንድ ውስጥ የኮሮና ተሐዋሲ ሥርጭት እጅግ በከፍተኛ ፍጥነት በመጨመሩ የክትባቱ ዕደላ ተቋርጧል። ኬንያ ውስጥ ከውጭ የሚገባ ክትባት የለም። በሌሎች የአፍሪቃ ሃገራትም ተመሳሳይ ነው። አፍሪቃ ውስጥ እስካሁን የተከተበው ሰው ቁጥር ከመላው ዓለም ሲነጻጸር ከሁለት ከመቶ ያነሰ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት ዐስታውቋል። የድርጅቱ የአፍሪቃ ኃላፊ ማትሺድሶ ሞይቲ ሁኔታው ያስጨንቃቸዋል። 

ምስል John Muchucha/AP Photo/picture-alliance

«ሌሎች አቅርቦቶች የሚገኙበትን መንገድ መመልከት መቻል አለብን። በዚያም ሃገራቱ ሁለተኛ ዙር የክትባት ብልቃጦችን ማግኘት ይችላሉ። በተመሳሳይ መልኩ አሁን ክትባት ለሃገራት የመላኩ ሒደት በተቋረጠበት ወቅት ሃገራቱ አጋጣሚውን ተጠቅመው ይበልጥ ውጤታማ የሆነውን ማንኛውንም ክትባት ለሁለተኛ ዙር እንዲሰጡ አጥብቀን እንመክራለን።» 

በዓለም የጤና ድርጅቱም በኩል በከፊል ድክመት ይታያል። ለአብነት ያህል ኮንጎ ከኮቫክስ ያገኘችው ክትባት ጊዜው ያለፈበት በመሆኑ ባስቸኳይ እንድትመልስ ተገድዳለች። በዓለም ዙሪያ ክትባቶችን ፍትኃዊ በሆነ መልኩ የማከፋፈሉ ጉዳይ ዐቢይ ተግዳሮት ይመስላል። የአፍሪቃ ኅብረት የጤና ድርጅቶች ኃላፊ  ጆን ንኬንጋሶንግ በተገኘው ቀዳዳ ክትባቶቹን ለማዳረስ ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። 

«ይኼ በፍጹም ዲፕሎማሲያዊ ንግግርር አይደለም። ማንኛውም ክትባት ካለው ጋር እንደራደራለን። ከባዮንቴክ፣ ከሲኖፋርም እና ሲኖቫክ እንዲሁም ሽፑትኒክን ካመረቱት ጋርም እንነጋገራለን።»

የአፍሪቃ ኅብረት እስካሁን የተሳካለት ከዩናይትድ ስቴትሱ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ከተባለው መድሃኒት አምራች ድርጅት ነው። ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ በርካታ ሰዎች ክትባቱን ከወሰዱ በኋላ ለችግር እንደተጋለጡ ከዚህ ቀደም ተዘግቧል። 

የዩናይትድ ስቴትሱ የበሽታዎች ቊጥጥር እና መከላከል ተቋም (CDC) ከጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ክትባት በኋላ ስለተመዘገቡ የሞት ክስተቶች ሰበብ ምርመራ አካኺዷል። ዕድሜያቸው በ50ዎቹ ውስጥ የሚገኙ አንዲት የኦሬጋን ነዋሪ ከክትባቱ በኋላ ባልተለመደ መልኩ የደም መርጋት ተከስቶባቸው ሕይወታቸው አልፏል። በተመሳሳይ መልኩ ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን ዩናይትድ ስቴትስ ውስጥ ከመታገዱ ቀደም ብሎ ሌላ አንዲት ሴት ክትባቱን ወስደው ተመሳሳይ የደም መርጋት ተከስቶባቸው ሐኪም ቤት ውስጥ ለመግባት ተገደዋል። መጀመሪያ አካባቢ ይኼ ችግር የተከሰተባቸው ሰዎች በቊጥር ስድስት ነበሩ። እናም ከ7 ሚሊዮን ሰዎች መካከል ስድስቱ ላይ የደም መርጋቱ ችግር መከሰቱ እጅግ ከስንት አንዴ የሚፈጠር ነው ሲሉ አንዳንድ ባለሞያዎች ነገሩን ቀለል ለማድረግ ሞክረዋል። 

ምስል Jerome Delay/AP/picture alliance

አንዳንዶች የኮቪድ ተሐዋሲ ከሚያስከትለው ከፍተኛ ችግር አንጻር ከስንት አንድ የሚከሰቱ የደም መርጋቶች ቢኖሩም መከተቡ ይሻላል ሲሉም ይሞግታሉ። በአጠቃላይ ከ7,8 ሚሊዮን ክትባቱን ከወሰዱ ሰዎች መካከል የሞቱት 88 ሰዎች አብዛኞቹ ከክትባቱ ጋር ባልተገናኘ መንገድ ሕይወታቸው ያለፈ መሆኑን ከሰሞኑ የወጣ የፎርቤስ ጽሑፍ ይጠቊማል።  በዚህም አለ በዚያ እስከ ታኅሣስ ወር መጨረሺያ ድረስ የአኅጉሪቱ 20 ከመቶ ነዋሪን ለመክተብ የአፍሪቃ ኅብረት የያዘው ዕቅድ ዋዣቂ ይመስላል። የዓለም ጤና ድርጅት ባልደረባው ንሴንጋ ንጎይ አፍሪቃ እንደምንም ብላ ራሷን መርዳት አለባት ይላሉ። 

«የወደፊት እጣ ፈንታችን እንደ አያያዛችን ይወሰናል። አካላዊ ርቀትን መጠበቃችንን ልንቀጥልበት ይገባል። በሀገሮቻችን የተሐዋሲው ስርጭት መጠን ከፍ እና ዝቅ የሚል ዋዣቂ ነው።»

አሁን በአፍሪቃ አኅጉር ስጋት የደቀነው የተሐዋሲው አዲስ ዝርያ ብቅ ማለቱ ነው። እስካሁን ክትባት የጀመሩ ሃገራት ሳይቀሩ የልዉጡ የኮሮና ተሐዋሲ ተግዳሮትን ለመጋፈጥ ከወዲሁ መዘጋጀት ይኖርባቸዋል። ከምንም በላይ ግን የጤና ባለሞያዎች የሚያስተላልፏቸውን ምክሮች እና የመከላከያ መንገዶች በቸልታ አለማለፍ እጅግ ይመከራል። 

ማንተጋፍቶት ስለሺ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW