ከ370 በላይ የተለያዩ አገራት ዜጎች ከሱዳን ጦርነት ሸሽተው ኩርሙክ ወረዳ ገቡ
ቅዳሜ፣ ግንቦት 5 2015
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (UNOCHA) 440 የሚደርሱ ሰዳናውያን ወደ በአሶሳ ዞን ኩርሙክ ወረዳ መግባታቸውን አስታወቀ። ሌሎች 18 ሺ የሚደርሱ ደግሞ በመተማ በኩል ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን የድርጅቱ ሪፖርት ያስረዳል። የሱዳኑን ግጭት በመሸሽ ወደ ጋምቤላ ክልልም የተሻገሩ እንዳሉ ተገልጿል፡፡ ዶይቼ ቬለ ወደ ኩርሙክ በርካታ ሱዳውያን መግባታቸውን ከክልሉ መንግስት እና ነዋሪዎች ለማጋገጥ ችሏል።
በሱዳን ከ20 ቀን በፊት በተቀሰቀሰው ግጭት ከ7 መቶ ሺ በላይ ሰዎች በሀገሪቱ ውስጥ ሲፈናቀሉ 177 ሺ የሚደርሱት ደግሞ ከሀገሪቱ መሸሻቸውን ዓለም አቀፉ የፍሰተኞች ድርጅት (IOM) አስታውቋል፡፡ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት በርካታ ሱዳናውያን በተለያየ አቅጣጫ ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውን ገልጿል፡፡ ከመተማ አስከ አሶሳ ዞን እና ጋምቤላ 19ሺ የሚደርሱ ሰዱናውያን መመዝገባቸውን ጽህፈት ቤቱ ገልጿል፡፡ ከአሶሳ ከተማ በ96 ኪ.ሜ ርቀት ላይ በምትገኘው ኩርሙክ ወረዳ 440 ሱዳናውያን ተመዝገበው እንደሚገኙ ኦቻ አመልክቷል፡፡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ አንድ የኩርሙክ ወረዳ ነዋሪ ከባለፈው ሳምንት ማክሰኞ ጀምሮ ብዙ ቁጥር ያላቸው ሱዳናውያን ወደ ወረዳው መግባታቸውን ተናግረዋል። በስፍራው ጊዜያዊ መጠለያ መዘጋጀቱንም ገልጸዋል።
የቤኒሻንጉል ጉሙዘ ክልል የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ታሲሳ ለዶቼ ቨለ እንደተናገሩት የሱዳን እና ሌሎች አገራት ዜግነት ያቸውን 378 ሰዎች ወደ ኩርሙክ መግባታቸውን አረጋግጠዋል፡፡ በኩርሙክ በኩል የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ሰዎች መግባት ከጀመሩ 10 ቀናት እንደተቆጠረም አክለዋል፡፡ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የስተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽን (UNHCR) ጊዜያዊ መጠለያ መዘጋጀቱንም አቶ ታረቀኝ አብራተዋል፡፡ ሱዳንን በሚያዋስነው በጉባ በኩል ከዚህ ቀደም ወደ ሱዳን ተፈናቅለው የነበሩ 9ሺ የሚደርሱ ኢትዮጵያውያን መመለሳቸውን ጠቁመዋል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ ጉዳዮች ማስተባበሪያ ጽህፈት ቤት (UNOCHA) ለመጀመሪያ ጊዜ በዚህ ሳምንት ሱዳናውያን በጋምቤላ ክልል በኩል ወደ ኢትዮጵያ መሻገራቸውን አመልክቷል። ሱዳን ውስጥ ተጠልለው የነበሩ 200 የደቡብ ሱዳን ስደተኞች ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ መሸሻቸውን ሀሙስለ ዕለት ይፋ ባደረገው ሪፐርቱ አመልክቷል፡፡
ነጋሳ ደሳለኝ
እሸቴ በቀለ