1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ከ9ሺህ በላይ ፈተናውን አልወሰዱም

ቅዳሜ፣ ሐምሌ 13 2016

የኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ ትናንት የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክተው ለብዙሐን መገናኛ በሰጡት መግለጫ ለፈተና ከተመዘገቡ ተማሪዎች መካከል ከ9ሺህ በላይ የአማራ ክልል ተማሪዎች ፈተናውን አልወሰዱም ብለዋል፡፡

Logo I Bildungsministerium von Äthiopien

ከ9ሺህ በላይ ፈተናውን አልወሰዱም

This browser does not support the audio element.

የዘንድረውን የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ፈተና ለመውሰድ ከተመዘገቡ የአማራ ክልል ተማሪዎች መካከል ከ9ሺህ በላይ የሚሆኑት ፈተናውንእንዳልወሰዱ ትምህርት ሚኒስቴር አስታወቀ። በሰሜን ሸዋ ዞን ካራቆሬ ከተማ የህዳሴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ለፈተናው ቢመዘገብም ፈተናውን እንዳልወሰደ ተናግሯል፡፡
በዚህ ዓመት በአማራ ክልል 200 ሺህየ12ኛ ክፍል ተማሪዎችን ለማስፈተን እቅድ የተያዘ ቢሆንም በክልሉ ከተፈጠረው የፀጥታ ችግር ጋር በተያያዘ 96ሺህ ያክሉ ለፈተና መመዝገባቸውን ቀደም ሲል የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ማሳወቁ ይታወሳል፡፡ ፈተናውን ካልወሰዱ ተማሪዎች መካከል በሰሜን ሸዋ ዞን የካራ ቆሬ ከተማ ነዋሪና የህዳሴ 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተማሪ ኑሩ ደሊል ለመፈተን ምዝገባ አካሂዶ የነበረ ቢሆንም በአካባቢው በነበረው ጦርነት ምክንያት የዓመቱን ትምህርት ማጠናቀቅ ባለመቻሉ ፈተናውን በሌላ ጊዜ ለመውሰድ መገደዱን ተናግሯል፡፡

አንድ የአጣየ ከተማ ነዋሪ በበኩላቸው ተማሪዎች በአለው የፀጥታ ችግር ምክንያት በአጣየ ከተማ የሚገኙ የ12ኛ ክፍል ተማሪዎች ፈተናውን አልወሰዱም ብለዋል፣ ተማሪዎቹ በትምህርት ገበታ ላይ የቆዩ ቢሆንም አልፎ አልፎ በሚከሰት የፀጥታ ችግር ምክንት የዓመቱን ትምህርት መሸፈን እንዳልቻሉ አስረድተዋል፡፡

ሌላ የከተማዋ ነዋሪም ተማሪዎቹ አብዛኛውን የትምህርት ክፍል ያልሸፈኑ በመሆናቸው ፈተናውን በመስከረም 2017 ዓ ም እንዲወሰዱ እንደሚደረግ መስማታቸውን አስረድተዋል፡፡
የኢፌድሪ ትምህርት ሚኒስቴር ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሐኑ ነጋ ትናንት የፈተናውን መጠናቀቅ አስመልክተው ለብዙሐን መገናኛ በሰጡት መግለጫ ለፈተና ከተመዘገቡ ተማሪዎች መካከል ከ9ሺህ በላይ የአማራ ክልል ተማሪዎች ፈተናውን አልወሰዱም ብለዋል፡፡
“በአገር አቀፍ ደረጃ ለፈተናው የተቀመጡት 684 ሺህ 372 ተማሪዎች ናቸው፣ ከቀሩት፣ ወደ ፈታናው ካልመጡት 17ሺህ 377 ተማሪዎች መካከል 9ሺህ 152 በአማራ ክልል ከፀትታ ጋር ሳፈተኑ የቀሩ ናቸው፡፡” ብለዋል፡፡
ከፀጥታ አኳያ ሐምሌ 3/2016 ዓ ም በክልሉ ማዕከላዊ ጎንደር ዞን ተማሪዎችንና ሌለሎች ሰዎችን ይዞ ወደ ፈተና ጣቢያ በሚሄድ  ተሸከርካሪ ላይ ታጣቂዎች በወሰዱት ጥቃት አንድ ተማሪ መሞቱንና ሌሎች ሁለት መቁሰላቸውን አመልክተዋል፣ ተማሪ ያልሆኑ ሌሎች ሁለት ሰዎች በዚሁ ጥቃት ህይወታቸው ሲያልፍ ሌሎች ስድስት ተሳፋሪዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ሚኒስትሩ በመግለጫቸው ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰር ብርሀኑ በዋቻሞ ዩኒቨርሲቲ ደግሞ አንድ የግል ተፈታኝ ተማሪ በደረሰበት የልብ ህመም ወደ ሆስፒታል ቢላክም ህይወቱ ማለፉን አመልክተዋል፡፡
የአማራ ክልል ትምህርት ቢሮ ቀደም ሲል በሰጠው መግለጫ፣ በተፈጠረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በክልሉ በዋናነት በጎጃም ቀጠና የሚገኙ ትምህርት ቤቶች ወደ ስራ አልተመለሱም፣ በዚህም 3 ሚሊዮን የሚጠጉ ተማሪዎች ከትምህርት ውጪ እንደሆኑ ተመልክቷል፡፡
ዓለምነው መኮንን
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW