1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኪነ-ጥበብ: “የጥበበኞቹ እስር እና መጉላላት አሳስቦናል”

ሐሙስ፣ ግንቦት 22 2016

የቴአትር ባለሞያዎች ማኀበር ሁለት ሰዎች ሲታሰሩበት ቢያንስ "ምነው ምንአጠፉ?" ማለት ይሳነዋል? የማኀበሩ ስራ ታዲያ ምንድነው? መጠየቅ ጠብታ እርዳታ ነው፤ ዝምታ ግን ይበላችሁ እሰይ ከማለት አይተናነስም፤ ያሉት አንድ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ ናቸዉ። በሌላ በኩል በኪነ-ጥበብ ሥራዎችና ባለሙያዎች ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንዲቆሙ ጥሪ ቀርቧል።

ዕብደት በሕብረት
ዕብደት በሕብረትምስል privat

ኪነ-ጥበብ: “የጥበበኞቹ እስር እና መጉላላት አሳስቦናል”

This browser does not support the audio element.

ኪነ-ጥበብ፤ የጥበበኞቹ እስር እና መጉላላት አሳስቦናል 

የቴአትር ባለሞያዎች ማኀበር ሁለት ሰዎች ሲታሰሩበት ቢያንስ "ምነው ምንአጠፉ?" ማለት ይሳነዋል? የማኀበሩ ስራ ታዲያ ምንድነው? መጠየቅ ጠብታ እርዳታ ነው፤ ዝምታ ግን ይበላችሁ እሰይ ከማለት አይተናነስም፤ ያሉት አንድ የማህበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ ናቸዉ። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል በኪነ-ጥበብ ሥራዎችና ባለሙያዎች ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንዲቆሙ ሲል ጥሪዉን አቅርቧል። 

በጥበብ ሃሳብን በመግለፃቸዉ ፤ በብዕር እና በትወና ጥበብን በመራቀቃቸዉ ወጣት የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች ታስረዋል፤ በፍርሃት ቆፈን ዉስጥ እንዲገቡ  ሆንዋል ሲሉ የሚገልፁት በጀርመን የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበባት ማህበር "ኤናክ"   መስራች እና ዋና ተጠሪ አቶ ተፈሪ ፈቃደ ናቸዉ።  

ባለፈዉ ሳምንት መገባደጃ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል በኪነ-ጥበብ ሥራዎች እና ባለሙያዎች ላይ የሚደረጉ ጫናዎች እንዲቆሙ ለመንግሥት ጥሪዉን አቅርቧል። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በኪነ-ጥበብ ባለሙያዎች እና መድረኮች ላይ "ወከባዎች፣ ክልከላዎች፣ እሥር እና ጫናዎች ከእለት እለት እየበረቱ መምጣታቸው" እንዳሳሰበው ያስታወቀዉ ማዕከሉ ዘርፉን ማፈን የሀሳብ ነፃነትን መጋፋት በመሆኑ ጥበቃ ሊደረግለት ይገባል ብሏል። የማዕከሉ ዋና ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም የኪነ ጥበብ ሥራዎችና ባለሙያዎች ጥበቃ ሊደረግላቸው እንጂ ሊገቱ አይገባም ይላሉ። 

አርቲስት አማኑኤል ሀብታሙ ምስል privat

የትያትር ባለሞያዎች ጸህፍት ብሎም ገጣምያን መድረካቸዉ እየተዘጋባቸዉ እየታሰሩ ፤ ብሎም ስለ ታሰሩት ከያንያን ቀርቦ ለመናገር በፍርሃት ዉስጥ የገቡ የዘርፉ ባለሞያዎች ጥቂቶች አይደሉም።  

ኪነ-ጠበብቱ ለምን ታሰሩ?  

መቼም የእኛ ሀገር ጥበብ በየዘመኑ ለገዢ እንዳሸበሸበች ነው የሚሉት አንድ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚ ፤ ለወራሪ እንኳ ቢሆን... በኢትዮጵያ የመጀመሪያው ረጅም ልብወለድ ፀሐፊ እንደሆኑ የሚነገርላቸው አፈወርቅ ገብረየስ የጣሊያን መሀረብ አቀባይ እንደነበሩ በዚያው ተያይዞ እንደሚነገርላቸዉ ጽፈዋል። በእርግጥ ይላሉ በመቀጠል በእርግጥ በዘመናት ቅብብሎሽ ውስጥ ከመጣው መንግስት ጋር ቤተመንግስት ገብተው የሚያሞቁ እንዳሉ ሁሉ ጥበብ አንገታቸው ላይ ቆማ ከዚያው ከቤተመንግስቱ ያስወጣቻቸው ከዚያም ዙፋኑን የፈተኑ የጥበብ ሰማዕታት አሉ ሲሉ ደራሲ በዓሉ ግርማን እንደምሳሌ ይጠቅሳሉ። ያም ሆነ ይህ ግን ይላሉ በመቀጠል፤ በዚህ ዘመን ያለዉ ሁኔታ ይለያል።

አንዳንዴ ሙዚቃ፣ ድራማ፣ ፅሁፍ... ዘውጉን እየደረደራችሁ ስትሸላለሙ ግርም ይለኛል። የት ሀገር ሆነው ይሆን  የፃፉት? እላለሁ... ጥበበኛ ከዘመን መንፈስ መፋታት አይችልማ... ጥበብ ሳትጠመዘዝ፣ ኮረኮንችና ሜዳውን ሳትመርጥ እውነት የወጣችውን እና የወረደችውን እየተከተለች የምታገለግል ታማኝ እመቤት ናት። ታዲያ የትኛው ስራችን በዚህ መንገድ ተገለጠ? ሁሉ ሜዳ ሜዳውን፣ ጥላ ጥላውን ሲዞር ነው የምታዩት... እንዴት አንድ ጥበብ በብርድልብስ ክንብንብ ውስጥ ይወለዳል? ከብርድልብሱ ውጪ ያለው ዓለም እኮ ይሰፋል፤ ሲሉ የመገናኛ ዘዴዎች ተጠቃሚዋ ጽሑፋቸዉን ይቀጥላሉ።

አርቲስት ዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳምስል privat

እንደምናየው ሁሉ የሚበረው ከአደጋ ነፃው ምድር ላይ ነው... ለዚያ ነው ግጥሙ ሁሉ "ጠብቄሽ ነበረ..." የሆነው... የት እንደሚጠብቃት አላውቅም ሀገር እየፈረሰ? ይጠይቃሉ።

በርግጥ በዚህ ዘመንም ይሄን ድንበር ጥቂት ተሻግረው ኮረኮንቹ መንገድ ላይ የተገኙ ጣት የሚቆጥራቸው ሰዎች አሉ። ከ"ጥበበኞቹ" በላይ ተፅዕኖውን የተረዳው መንግስት ጎትቶ እስር ቤት የዶላቸው። የአማኑኤል ሀብታሙ ሲገርመን አዘጋጁ ዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳም እንደታሰረ ሰማን።

ታዲያ ጥበበኝነታችን ለመድፈርና ጥበብን ለማገልገል ባያበቃን እንዴት "እነዚህ ሰዎች ለምን ታሰሩ ?" የሚል የዘወትራዊ ሰው ጥያቄ ለማንሳት አይረዳንም? እንዴት አብረን የበላን የጠጣናቸው ሰዎች ሲታሰሩ በዝምታ እናዋጣለን?

የቴአትር ባለሞያዎች ማኀበር ሁለት ሰዎች ሲታሰሩበት ቢያንስ "ምነው ምንአጠፉ?" ማለት ይሳነዋል? የማኀበሩ ስራ ታዲያ ምንድነው? መጠየቅ ጠብታ እርዳታ ነው፤ ዝምታ ግን ይበላችሁ እሰይ ከማለት አይተናነስም፤ ሲሉ የማኅበራዊ መገናኛ ተጠቃሚ አስተያየታቸዉን በአራት ነጥብ ዘግተዋል።  

ገጣሚ በላይ በቀለ ወያምስል privat

የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበባት ማህበር

በጀርመን የኢትዮጵያ ኪነጥበባት ማህበር በምህጻሩ "ኤናክ" ከምስረታው ከጎርጎረሳዉያኑ 2009 ዓም ጀምሮ በተለያየ የጥበብ ዘርፍ ባለውለታ የሆኑ ኢትዮጵያውያንን ሕይወትና ኑሮ ለማሻሻል እንዲሁም ዘመን ተሻጋሪ ስራዎቻቸውን በማሰባሰብ ለተተኪው ትውልድ ጥናትና ምርምር እንዲውሉ ለማድረግ አያሌ ውጥኖችን ይዞ ጥበበኞችን በመርዳት ወደ 16 ዓመታት ተጉዟል፤ ለጥበቡ ዉለታ ያበረከቱ ባለሞያዎችን ወደ ጀርመን በማምጣት ህክምናን ጨምሮ ድጋፍም በማድረጉም ይታወቃል። ይሁንና ለኢትዮጵያ ኪነጥበብ ዘርፉ ፈንጥቆ የነበረዉ ተስፋ ዛሬም ባልተቀረፉ ተግዳሮቶች የታጀበ መሆኑን በጀርመን የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበባት ማህበር "ኤናክ" መስራች እና ዋና ተጠሪ አቶ ተፈሪ ፈቃደ ገልጸዋል።    

በአሁኑ ወቅት "እብደት በህብረት" የተባለው የመድረክ ትያትር ተዋናይ አማኑኤል ሀብታሙ እና አዘጋጁ ዳግማዊ አመለወርቅ ፈይሳ ታስረዋል። በሥነ ግጥሞቹ የሚታወቀዉ ገጣሚ በላይ በቀለ ወያም - ለረጅም ጊዜ በእሥር ላይ መሆኑ ይታወቃል። ይሁንና የኢትዮጵያ የኪነ-ጥበባት ማህበር ብሎም የኪያንያን እና ቤተሰቦቻቸዉ ወደሚዲያ ቀርበዉ ጉዳዩን ለመናገር በፍርሃት ዉስጥ መሆናቸዉ ሌላዉ አሳሳቢ ጉዳይ ሆንዋል። የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከል ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ይህ ለምን ሆነ ይሆን ስንል ጠይቀናቸዋል።  

በጀርመን የኢትዮጵያ ኪነ-ጥበባት ማህበር ዋና ተጠሪ አቶ ተፈሪ ፈቃደ እንዳሉት ከያንያኑ የታሰሩት ጉዳይ ባለመታወቁ እስካሁን ከመከታተል እና ነገሮችን ከማጣራት ዉጭ የሰራነዉ ነገር የለም፤ ይሁን እና ማህበራችን ኪነ-ጥበቡን ለማሳደግ ብዙ ጥረት አድርጓል። የታሰሩም ፍትህ እንዲያገኙ እንጠይቃለን ብለዋል።  አቶ ተፈሪ የኪነ-ጥበብ አፍቃሪዎች ስለ ከያንያኑ እስር ለመናገር ፍርሃት እንዳለባቸዉም ተናግረዋል። 

በተያየትር ትወና ዝናን ያተረፈችዉ እና በስደቱ ዓለም በጀርመን ስትኖር 11 ዓመታት እንደሆናት የምትናገረዉ አርቲስት አልማዝ ልመንህ ከጀርመናዉያን ጋር በትያትር መድረክ ላይ እየቀረበች ለጥበቡ ያላትን ጥሪና ፍቅር ቀጥላለች። የከያንያኑ መታሰርን በመስማትዋ ማዘንዋንም ተናግራለች። እንደ አርቲስት አልማዝ የኪነ-ጥበብ በረከቶችን ልንጠቀምባቸዉ ይገባል። በሌላ በኩል አርቲስት አልማዝ የከያንያን ገቢ እንደስራቸዉ ተመጣጣኝ አለመሆኑ እና በድህነት እንደሚኖሩ ተናግራለች።

የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች ማዕከልምስል EHRDC

ሰብዓዊ መብቶች ባሕል የሆኑባት ኢትዮጵያን እዉን የማድረግ እቅድ

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ከ2014 ዓ.ም ጀምሮ በየዓመቱ የፊልም ፌስቲቫል በማዘጋጀት፣የሰብዓዊ መብቶች በስፋት በኪነ-ጥበብ ሥራዎች ውስጥ ትኩረት እንዲያገኙ፤  እንዲዳሰሱ ማድረጉ "ሰብዓዊ መብቶች ባሕል የሆኑባት ኢትዮጵያን" ማየት የሚል ራዕዩን ለመሳካት አቅም እንደሚሰጠዉ በማመን እንሚያዘጋጀው አስታውቋል። የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች ላይ የሚደርሰዉ እስር እና መጉላላት እንዲቆም ፣ መንግሥት ሃሳብ በነፃነት የሚገለጽባቸውን መሰል ዘርፎች እንዲጠብቅ እና የታሰሩትንም እንዲፈታ፤ ስህተትም ካለ ከያንያኑ ታርመዉ ሞያቸዉን እንዲቀጥሉ እንዲያደርግ ሲሉ የማዕከሉ ዳይሬክተር አቶ ያሬድ ኃይለማርያም ጠይቀዋል።

የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንን ጨምሮ በርካታ የኪነ-ጥበብ ባለሞያዎች እና አፍቃሪዎች የታሰሩ የጥበብ ባለሞያዎች ስህተታቸዉ ተነግሯቸዉ በጥበብ መድረክ ለጥበብ አፍቃሪዉ ወደ መድረኩ እንደሚመለሱ እምነታቸዉ ነዉ። በዚህ ዝግጅት የኢትዮጵያን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር እንዲሁም የቴአትር ባለሞያዎች ማኀበርን ለማነጋገር ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም። በዚህ ዝግጅት ቃለ ምልልስ የሰጡንን በዶቼ ቬለ DW ስም በማመስገን ሙሉዉን ጥንቅር የድምጽ ማድመጫ ማዕቀፉን በመቻን እንዲከታተሉ እንጋብዛለን።

አዜብ ታደሰ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ
ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW