1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የኑሮ ውድነት በካማሺ ዞን

ሐሙስ፣ ጥር 16 2016

የካማሺ ዞን ነዋሪዎች በአካባቢው የምርት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ተናገሩ። ባለፉት ሦስት ሳምንታት የፍጆታ ምርት ወደ ካማሺ ከተማ አለመግባቱን ነዋሪዎቹና የከተማው ከንቲባ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ለምርት ዋጋ መጨመር ምክንያት ያሉት በጸጥታ ችግር ምክንያት የተሽከርካሪዎች ሥራ ማቆም እንደሆነ ተናግረዋል።

 Kamashi town in Benishangul Gumuz region Ethiopia
በካማሺ ዞን በጸጥታ ምክንያት የመንገድ መዘገት የኑሮ ውድነቱን ማባባሱ ነው የተገለጸው። ምስል Negassa Dessalegn/DW

የኑሮ ውድነት በካማሺ ዞን

This browser does not support the audio element.

 

የካማሺ ዞን ነዋሪዎች በአካባቢው የምርት ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን ተናገሩ። ባለፉት ሦስት ሳምንታት የፍጆታ ምርት ወደ ካማሺ ከተማ አለመግባቱን ነዋሪዎቹና የከተማው ከንቲባ ለዶቼ ቬለ ገልጸዋል። ለምርት ዋጋ መጨመር ምክንያት ያሉት በጸጥታ ችግር ምክንያት የተሽከርካሪዎች ሥራ ማቆም እንደሆነ ተናግረዋል። ከሦስት ሳምንት በፊት በአጎራባች ቢላ መገንጠያ የሚባል አካባቢ በጸጥታ ኃይሎችና ታጣቂዎች መካከል ግጭት ተፈጥሮ እንደነበር ነዋሪዎቹ ተናግረዋል። የምዕራብ ወለጋ ዞን አስተዳደርና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት በበኩሉ በዞኑ አዋሳኝ አካባቢ ላይ ከሦስት ሳምንት በፊት ጸጥታ ኃይሎች በሌሉበት ስፍራ አንድ ተሽከርካሪ ተቃጥሎ እንደነበር ገልጸዋል። በአሁኑ ወቅት በጸጥታ ኃይሎች እጀባ የመጓጓዣ አገልግሎት መስጠት መጀመሩንም አመልክተዋል።

በካማሺ ዞን መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች ዋጋ ከዕለት ወደ ዕለት እየጨመረ እንደሚገኝና ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኙ ኅብረተሰብ ክፍሎች ላይ ተጽህኖ እያሳደረ እንደሚገኝ ያነጋርናቸው ነዋሪዎች አመልክቷል። አንድ ኪሎ የጤፍ ዋጋ 130 ብር፣ ሽንኩርት በኪሎ ከ180 ብር እስከ 200 ብር እንደሚሸጥ ተናግረዋል። አብዛኛው የፍጆታ ምርቶች በገበያ ላይ እንደማይገኙም ነው ነዋሪዎች የተናገሩት፡፡ አልፎ አልፎ ከሌላ አካባቢ በሚመጡ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ንረት እንደሚስተዋል ነዋሪዎቹ አብራርተዋል።በጸጥታ ችግር ሳቢያ የፍጆታ ምርት እየገባ አይደለም

የካማሺ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አብዴታ ደረሳ የምርት ዋጋ ጭማሪውን አስመልክቶ በሰጡን ማብራሪያ በአካባቢው የኑሮ ውደነት ይዞታው መጨመሩን አረጋግጠዋል። ባለፉት ሦስት ሳምንታትም መሠረታዊ የፍጆታ ምርት ወደ ከተማ አለመግባቱን ጠቁሟል። ከሦስት ሳምንት በፊት ታጣቂዎች አደረሱት ባሉት ትንኮሳ በስጋት ምክንያት በንግድ ሥራ የተሰማሩ ባለሀብቶች ሸቀጥ መጫን አቁመው እንደነበርም ገልጸዋል።

በጉዳዩ ላይ ያነጋገርናቸው የምዕራብ ወለጋ ዞን የአስተዳደር እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኮማንደር ነጋልኝ በቃበል በአዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ከሦስት ሳምንት በፊት «ጠላት» ብሎ የጠሯቸው ኃይሎች አንድ ተሸከርካሪ አቃጥሎ እንደነበር አስታውቀዋል። በዕለቱ ጸጥታ ኃይል ባለመኖሩ ድንገት የተከሰተ መሆኑን ገልጸው ከዛ ወዲህ ለተሽከርካሪ እንቅስቃሴ ስጋት የሆነ የጸጥታ ችግር የለም ብሏል።

«ከሦስት ሳምንት በፊት በተለያዩ ቦታዎች ከነጆ የተነሳ አንድ መኪና ተቃጥሎ ነበር። ወደ ካማሺ ከተቃረበ በኋላ ነው በመኪናው ላይ ጉዳት መድረሱን የሰማነው። በድንገት ጸጥታ ኃይሎች በለሉበት ቦታ የተከሰተ ነው። ከዚያ ወዲህ ተሽከርካሪ ወደዚያ መሄድ አላቆመም እየተንቀሳቀሰ ነው። በእኛ በኩል ከጸጥታ ኃይሎች ጋር በዚሁ መስመር ላይ የሚከሰቱ ችግሮችን በመነጋገር እያስተካከሉ መሄድ ይቻላል»‹ ነው ያሉት። በካማሺ ዞን እና አካባቢው የፍጆታ ምርት ዋጋ መጨመርና የምርት አቅርቦት እጥረት በተደጋጋሚ በነዋሪዎቹ የሚነሱ ቅሬታዎች ናቸው፡፡ በዞኑ ለረጅም ጊዜ የቆየው የጸጥታ ችግር የዛሬ ዓመት ገደማ በተደረጉ ስምምነትና እርቅ በዞኑ ሰላም መስፈኑን  የዞኑ አስተዳደር ገልጸዋል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW