በአንድ ቤት 14 በቀበሌ 22 ሰዎች የገደለው መሬት መንሸራተት በአርሲ
ማክሰኞ፣ ግንቦት 21 2010በምዕራብ አርሲ ዞን ነንሰቦ ወረዳ ቱሉ ጎላ ቀበሌ ግንቦት 18 ቀን 2010 ዓ.ም. ለአንድ ሰዓት ተኩል ገደማ የጣለ ከባድ ዝናብ ያስከተለው የመሬት መንሸራተት በተራራማ አካባቢ በሰፈሩ ነዋሪዎች ላይ የከፋ ጉዳት አድርሷል። የምዕራብ አርሲ ዞን አስተዳዳሪ አቶ መሐመድ ከማል "ቤቶቹ ሰፍረው ያሉበት ጋራ ስር ነው። በተራራው ላይ የሰፈሩም አሉ። በዘነበው ከባድ ዝናብ ምክንያት ጋራው ተንሸራቶ በስሩ በነበሩ ቤቶች ላይ በመደርመስ ወደ ዘጠኝ ቤት ላይ አደጋውን አድርሷል" ሲሉ አስረድተዋል።
እንደ አቶ መሐመድ ገለፃ በአደጋው 22 ሰዎች ሲሞቱ አስራ አራቱ በአንድ ቤት ውስጥ የነበሩ ናቸው። ከሟቾቹ መካከል አስራ አራቱ ደግሞ ዕድሜያቸው ከ18 አመት በታች ነው። በመሬት መንሸራተቱ ሰባት ሔክታር በሚጠጋ ማሳ ላይ የነበሩ የተለያዩ አዝርዕት ላይ ጉዳት መድረሱን እና 45 የቤት እንስሳትም ማለቃቸውን የገለጹት አቶ መሐመድ በአጠቃላይ ወደ 2.5 ሚሊዮን ብር የሚደርስ ንብረት መውደሙን ገልጸዋል።
አቶ መሐመድ በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ሰባት ሰዎች የሕክምና እገዛ ማግኘታቸውን ተናግረዋል። መረጃው ከወረዳ በማግሥቱ ለዞን አስተዳደር መድረሱን የገለጹት አቶ መሐመድ ግንቦት 19 ቀን 2010 ዓ.ም. የሟቾች የቀብር ሥነ-ሥርዓት መካሔዱን ተናግረዋል። ለተጎጂዎች ድጋፍ ለማድረግ ከአንድ ሰዓት በላይ በአሕያ እና በበቅሎ ጉዞ መደረጉን አስተዳዳሪው ገልጸዋል። በአካባቢው መልክዓ ምድር፤ በሰዎች አሰፋፈር እና የመንገድ እጦት ምክንያት የነፍስ አድን ስራው ፈታኝ እንደነበር አቶ መሐመድ አስረድተዋል።
"መሬቱ እንደተደረመሰ ቤቱን ሙሉ በሙሉ ቀብሮታል። በተለይ ሶስት ቤቶችን ሙሉ በሙሉ ነው የቀበራቸው። ወዲያውኑ ሕይወት ማትረፍ የሚቻልበት ሁኔታ አነስተኛ ነበር። ቦታውም ደን ነው። ለሊት ነው። ለትራንስፖርትም ምቹ አይደለም። የአደጋው አፈጣጠር የሰው ሕይወት ለማትረፍ የሚቻልበት አልነበረም"
ከአረቢያን ባሕር ተነስቶ በአፍሪቃ ቀንድ ስምጥ ሸለቆ የሚጋልብ ሳጋር የተባለ አውሎ ንፋስ በቀጣናው ከፍተኛ ዝናብ እና የመሬት መንሸራተት ሊያስከትል እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታዎች ማስተባበሪያ ቢሮ (OCHA) አስጠንቅቆ ነበር። በማስጠንቀቂያው ከፍተኛ ዝናብ ይጥልባቸዋል ከተባሉ አካቢዎች መካከል አርሲ አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ጥንቃቄ እንዲረግ የሚያሳስብ ደብዳቤ ለሁሉም የክልል እና የፌደራል መስሪያ ቤቶች ማሰራጨቱን የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብዓዊ እርዳታዎች ማስተባበሪያ መስሪያ ቤት ሰነድ ይጠቁማል።
በምዕራብ አርሲ አካባቢ እየጣለ የሚገኘው የበልግ ዝናብ "መደበኛ እና ከመደበኛ በላይ" እንደሆነ የሚገልጹት የብሔራዊ ሚቲዎሮሎጂ ኤጀንሲ ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ዱላ ሻንቆ ጠንከር ያለ ዝናብ በመጪዎቹ የክረምት ወራት ሊቀጥል እንደሚችል ገልጸዋል። ምክትል ዳይሬክተሩ ምዕራብ አርሲን በመሳሰሉ ተጋላጭ አካባቢዎች የሚገኙ ሰዎች "ቤታቸውን ሲሰሩ፤ እርሻቸውን ሲያርሱ የአካባቢውን የአፈር ሁኔታ አውቀው ጥንቃቄ ማድረግ አለባቸው" ብለዋል።
በምዕራብ አርሲ በመሬት እጥረት ሳቢያ ሰዎች ወደ ተራራማ አካባቢዎች በማቅናት መስፈር መጀመራቸውን የሚናገሩት አቶ መሐመድ "አሁንም ሊከሰት ስለሚችል ተመሳሳይ ቦታዎች ላይ የሰፈሩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ከዛ ተራራ ሥር ራቅ ብለው እንዲሰፍሩ እየተሰራ ነው ያለው" ሲሉ ተናግረዋል።
እሸቴ በቀለ
አርያም ተክሌ