1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

"ካገሬ የወጣሁት ከፍቶኝ ተገፍቼ ነው። ስመለስ ግን ቂም ይዤ አይደለም" ታማኝ በየነ

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 26 2010

በኢትዮጵያ ፖለቲካ ለውጥ እንዲኖር ለረዥም አመታት ይወተውት የነበረው ታማኝ በየነ ከ22 አመታት በኋላ ወደ አገሩ ተመልሷል። ታማኝ "ለእኔ መምጣት ህይወት የከፈሉ አሉ፤ የተገረፉ አሊሉ፤ መከራ የተቀበሉ አሉ" ሲል ተደምጧል።

Äthiopien Rückkehr Menschenrechtsaktivist Tamagn Beyene
ምስል DW/Y. Gebregziabher

ታማኝ በየነ ወደ ኢትዮጵያ ተመለሰ

This browser does not support the audio element.

ታማኝ በየነ ከ22 አመታት በኋላ በዛሬው ዕለት ኢትዮጵያ ገባ። በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ ለውጥ እንዲመጣ ለአመታት አበክሮ ይወተውት የነበረው ታማኝ አዲስ አበባ ሲደርስ ደማቅ አቀባበል ተደርጎለታል። ፖለቲከኞች፣ ድምፃውያን እና በተለያዩ የኪነ-ጥበብ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሙያዎች በአቀባበል መርሐ ግብሩ ላይ ታይተዋል።
ታማኝ በየነን ለመቀበል ቦሌ አለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ከተገኙ መካከል እናቱ አንዷ ነበሩ። ያራመደው አቋም በእሱ ብቻ ሳይሆን በባለቤቱ በድምፃዊት ፋንትሽ በቀለ ላይ ጭምር ተጽዕኖ ማሳረፉን ተናግሯል። "እናቴ እዚህ ድረስ መጥታ ተቀበለችኝ። አባቴን ግን መቅበር አልቻልኩም። እንኳን እኔ ባለቤቴ እናቷን መቅበር አልቻለችም" ያለው ታማኝ ለውጡ ቀደም ብሎ ቢሆን ኖሮ የሚል አስተያየት ሰጥቷል።ታማኝ "ለውጡ ትንሽ ቀደም ብሎ ቢሆን ኖሮ እናቷን መቅበር ትችል ነበር። እኔ በወሰድኩት አቋም፤ እኔ ባመንኩት ነገር እሷም አብራ ተቀጣች። ግን ይኸ ሁሉ ቂም የሚያዝበት አይደለም። ወደ ፊት ሌሎች እናቶች እንዲህ እንዳይሆኑ አገራችን የሰላም የፍቅር አገር እንድትሆን ሁላችንም ድርሻ አለን" ሲል አሳስቧል።
ለ22 አመታት በአሜሪካን አገር የኖረው ታማኝ "ካገሬ ከፍቶኝ ተገፍቼ ነው የወጣሁት። ስመለስ ግን ቂም ይዤ አይደለም የመጣሁት" ሲል ተደምጧል። ቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ ከደረሰ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ "ትኬት ቆርጬ ዝም ብዬ አይደለም የመጣሁት። ለእኔ መምጣት ህይወት የከፈሉ አሉ፤ የተገረፉ አሊሉ፤ መከራ የተቀበሉ አሉ" ሲል ብሏል። "ያጣሁትን አየር አንዴ ስቤ፣ ወገኖቼን አግኝቼ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሁኔታውን ገምግሜ እመለሳለሁ" ያለው ታማኝ ወደ ፊት በዘላቂነት መኖሪያውን በኢትዮጵያ እንደሚያደርግ ጠቁሟል።
ታማኝ አዲስ አበባ ከደረሰ በኋላ በሙያው ከበሬታን ወዳተረፈበት የኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር አቅንቷል። በዚያም የደመቀ አቀባበል ተደርጎለታል።

ምስል DW/Y. Gebregziabher

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW