ኬንያ በታዳሽ የኃይል ምንጭ ብዙ ተጉዛለች
ቅዳሜ፣ ሚያዝያ 14 2015
ኬንያን የጀርመን መራኄ መንግሥት በቅርቡ፦ «የከባቢ አየር ጥበቃ ባለ ስኬት እና ተምሳሌት» ሲሉ አወድሰዋል ። የጀርመን መንግሥት የምሥራቅ አፍሪቃዊቷ ሀገር ኬንያን በተለይ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ላይ ይበልጥ እንድትበረታ ድጋፍ መስጠት ይሻል ። ኬንያ ውስጥ 80 ከመቶ የኃይል አቅርቦቱ ከአረንጓዴ የኃይል ምንጭ የሚገኝ ነው ። ኬንያ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር እስከ 2030 ድረስ አረንጓዴ የኃይል ምንጭ አቅርቦቷን መቶ በመቶ ማድረግ ትሻለች ። እስካሁን ድረስ ኬንያ ለኃይል ምንጭነት የምትጠቀመው ከጥልቅ ከርሰ ምድር ከሚንፎለፎል እንፋሎት የሚመነጨውን ነው ። ከፀሓይ የሚገኝ የኃይል ምንጭም በኬንያ ቦታ አለው ።
ሔዜል ናይሮቢ ውስጥ ያላት መኖሪያ ቤት ጣሪያው ላይ የፀሓይ ኃይል ማመንጪያ ተገጥሞለታል ። ከፀሓይ የምታገኘውን ኃይልም ቤቷን ለማብራት እና ለማሞቅ ትጠቀምበታለች ። ከኤሌክትሪክ የምታገኘውን ኃይል የምትጠቀመው ለምግብ ማብሰያ ምድጃው ብቻ እንደሆነም ትናገራለች ። «ለማሞቅ እና ለማብራት። ኤሌክትሪክ የምጠቀመው ለማብሰል ብቻ ነው ።»
ሔርዜል ከፀሓይ ከሚገኝ የኃይል ምንጭ የምትጠቀመው ከባቢ አየርን ለመጠበቅ በሚል ብቻ አይደለም ። ከፀሓይ የሚገኝ የኃይል ምንጭ ከኬንያ የኃይል ባለሥልጣን ከሚገኘው የኤሌክትሪ ኃይል አንጻር ዋጋው እጅግ ዝቅ ያለ ነውም ትላለች ። «የኬንያ የኃይል ባለሥልጣን ከሚያስከፍለው በጣም ርካሽ ነው ። »
ሔርዜል ከኤሌክትሪክ የሚገኝ የኃይል ምንጭን ቀንሳ ወደ አማራጭ የኃይል ምንጭ በመዞሯ ለመብራት የምትከፍለው ወጪ በሚገባ ቀንሷል ። እስከዛሬ ትከፍል ከነበረውም የኃይል ወጪዋ በሲሦ አንሷል ። በዚያ ላይ ኬንያ ውስጥ ኤሌክትሪክ በተቋረጠ ቁጥር ሰዉ በጭለማ ውስጥ እንደተቀመጠ ነው ። አንዳንዶች በእርግጥ በናፍጣ የሚሠራ ግዙፍ ጄኔሬተር አላቸው ግን ያ ውድ ነው ። እናም ብዙዎች ያን ማግኘት አይችሉም ። እንደገና ደግሞ ኬንያ ውስጥ ብዙ ቦታዎች ከብሔራዊ የኃይል አቅርቦት ባለሥልጣኑ ጋር የተገናኙ አይደሉም ። በርካቶች ከፀሓይ የሚገኝ የኃይል ምንጭ በመጠቀም የኃይል አጠቃቀም ነጻነታቸውን አውጀዋል ።
አኒሳ ዖስማን ሲፒ ሶላር የተሰኘው ኩባንያ ኃላፊ ናቸው ። ኩባንያው ሥራ ከጀመረ ገና አምስት ዓመቱ ነው ። እንዲያም ሆኖ ግን በአሁኑ ወቅት ኬንያ ውስጥከፀሓይ የሚገኝ የኃይል ምንጭ ለነጋዴዎች፤ ኢንዱስትሪዎች እና ግለሰቦች በማቅረብ ዋነኛው ሆኗል ። ከፀሓይ የሚገኝ የኃይል ምንጭን በመጠቀም ኬንያ ብዙ ተጉዛለች ። ከ15 ዓመታት በፊት ይህ የማይታሰብ ነበር ይላሉ አኒሳ።
«ምናልባት የዛሬ 15 ዓመት ሰዉ ከፀሓይ የሚገኝ የኃይል ምንጭን ይጠቀም የነበረው ለሒሳብ ማባዣዎች ብቻ ነበር ። አሁን በየጊዜው በርካታ ሰዎች ከፀሓይ የሚገኝ የኃይል ምንጭ በዕለት ተዕለት ሕይወታቸው መጠቀማቸው እየተለመደ ነው ።»
ኬንያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት 80 ከመቶ የኃይል አቅርቦቱ ከታዳሽ የኃይል ምንጭ የሚገኝ ነው ። በተለይ ደግሞ ከጥልቅ ከርሰ ምድር ከሚንፎለፎል እንፋሎት የሚመነጨው ኃይል ። ኬንያ እንደ ጎርጎሪዮስ አቆጣጠር እስከ 2030 ድረስ የኃይል ምንጭ አቅርቦቷን መቶ በመቶ ወደ ታዳሽ የኃይል ምንጭ ማዞር ትሻለች ። ከንፋስ፤ ከፀሓይ እንዲሁም ከከርሰ ምድር ከሚንፎለፎል እንፋሎት የሚመነጭ ኃይል ወደመጠቀሙ እንደምትዞርም ክላይማን የኃይል ፖሊሲ ማእከል የተባለው የምርምር ተቋም ገምቷል ።
ኬንያ ውስጥ ከፀሓይ የሚገኝ የኃይል ምንጭን ለሀገሪቱ የመንግሥት የኤሌክትሪክ ኃይል የሚመግቡ ተቋማት አሉ ። ከተቋሞቹ ግዙፉ ሰሜን ምሥራቅ ኬንያ ጋሪሳ ውስጥ ይገኛል ። ከፀሓይ ከሚገኝ ኃይል ማመንጪያ ሥፍራ 120 የእግር ኳስ ሜፋዎችን ስፋት ያክላል ። ከዚህ ሥፍራ 55 ሜጋ ዋት ኃይል ይመነጫል ። ይህም ኃይል ለ600.000 ቤቶች ኃይል መስጠት ይችላል ። የኃይል ማመንጪያው የተገነባው በቻይና አንድ ኩባንያ ሲሆን፤ ሥራ ከጀመረ ሦስት ዓመታትን አስቆጥሯል ።
ቻይና ከፀሓይ የሚገኝ ኃይል ማመንጪያ ሥፍራዎችን በመገንባቱ ሚናዋ ላቅ ያለ ነው ። እስካለፉት ጥቂት ዓመታት ድረስ ምእራባውያን ሃገራት የፀሓይ ኃይል ማመንጪያ ሰሌዳዎችን በማምረት አለያም ቁሶቹን በመገንባት ሲሳተፉ ቆይተዋል ። ከፀሓይ የሚገኝ ኃይል ማመንጪዎችን ኬንያ ውስጥ ከማምረት ከምሥራቁ ዓለም ማስመጣቱ ይረክሳል ይላሉ የክሎሪድ ኦክሳይድ ማምረቻ ኩባንያ ዋና ሥራ አስኪያጅ ቻርልስ ንጋሬ ።
«ኬንያ ውስጥ ከምናመርታቸው ከፀሓይ የሚገኝ ኃይል ማመንጪያ ሰሌዳዎች ይልቅ ከምሥራቁ ዓለም የሚመጡት በጣም ርካሽ ሆነው አግኝተናቸዋል ።»
በአሁኑ ወቅት ኬንያ ውስጥ ከፀሓይ የሚገኝ ኃይል ማመንጪያ ሰሌዳዎችን የሚያመርት የለም ። ፉክክሩ ከቻይና በኩል እጅግ ጠንካራ ነው ። አብዛኛዎቹ በእየጣራው ላይ የሚታዩት ከፀሓይ የሚገኝ ኃይል ማመንጪያ ሰሌዳዎች የሚመጡትም ከቻይና ነው ። አዳራሾቹ ውስጥ ከፀሓይ በሚገኝ ኃይል የሚሠሩ የመኪና ባትሪዎች ጭምር ይመረታሉ ። ከፀሓይ የሚገኝ ኃይል ማመንጪያ ሰሌዳዎችን በመጠቀምም የኤሌክትሪክ አቅርቦቱን መደገፍ ይቻላል ። በአጠቃላይ ኬንያ ውስጥ የታዳሽ የኃይል ምንጭ አገልግሎት እያበበ ነው ይላሉ ቻርልስ ንጋሬ ። «ኬንያ ውስጥ ከፀሓይ የሚገኝ ኃይል እየተስፋፋ ነው ። ባለፉት ሁለት ዓመታትም ከፀሓይ የሚገኝ ኃይል ፍላጎቱ እጥፍ ሆኗል ።»
የናይሮቢ ነዋሪዋ ሔርዜል ጣራዋ ላይ በተዘረጉት ከፀሓይ የሚገኝ ኃይል ማመንጪያ ሰሌዳዎች ደስተኛ ናት ። ወደፊትም የኃይል ማመንጪያዎቹ ባሉበት እንዲቆዩ ትሻለች ። «እዚህ ሁሌም ፀሓይ አለ ። ፀሓይ የሌለችበት አንድም ሥፍራ የለም ።»
ምክንያቱም ፀሓይ በምትኖርበት አካባቢ ሁሌም አለችና ።
ማንተጋፍቶት ስለሺ/ካሪን ቤንሽ
እሸቴ በቀለ