1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ክላውድ፤መረጃን ከመጥፋት የሚታደገው ቴክኖሎጂ

ረቡዕ፣ ነሐሴ 24 2015

ክላውድ በበይነመረብ አማካኝነት አገልግሎት የሚሰጥ ቴክኖሎጅ ሲሆን ፤ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች በርካታ መረጃዎችን ረዘም ላሉ ጊዚያት ዲጅታል በሆነ መንገድ በማስቀመጥ መረጃው ቢሰረዝ ወይም የተቀመጠበት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ቢጠፋ እንኳ በሌላ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ለማግኘት እድል ፈጥሯል።

የክላውድ ቴክኖሎጅ መረጃን በየትኛውም ቦታ ለማግኘት ያስችላል
የክላውድ ቴክኖሎጅ ሃርድ ዲስኮችን እና የግል የውሂብ ማዕከሎችን ከመጠቀም ይልቅ መረጃን ለማከማቸት በበይነመረብ የርቀት ሰርቨሮችን መጠቀም የሚያስችል ነውምስል YAY Images/IMAGO

በበይነመረብ ውሂብ የሚያከማቸው ቴክኖሎጅ

This browser does not support the audio element.


በየጊዜው የሚደረገው ፈጣን የቴክኖሎጅ ለውጥ የምንሰራበትን፣ የምንማርበትን እና አጠቃላይ የሰዎችን መስተጋብር  በመቀየር ላይ ይገኛል። የበይነመረብ ፍጥነት  በእጅጉ እየጨመረ መምጣት እንዲሁም እንደ ጉግል እና ፌስቡክ ያሉ  ኩባንያዎች የበይነመረብ መዳረሻን  በተለያዩ የዓለም ክፍሎች ይበልጥ እንዲስፋፋ ማድረጋቸው  ፤ አሁን የምንጠቀምባቸው ዲጅታል ቴክኖሎጅዎች ከዓመታት በፊት ከነበሩት በእጅጉ  የተለዩ እንዲሆን አድርጓል።ከዚህ ባሻገር በይነመረብ  ተጽዕኖ የተለመደውን የውሂብ/Data/አቀማመጥ  ዘዴም ቀይሯል።ከነዚህም መካከል የክላውድ ቴክኖሎጅ አንዱ ነው። በግላቸው ለተለያዩ ድርጅቶች የዲጅታል ቴክኖሎጅ የማስፋፊያ  ስራዎችን የሚሰሩት የሶፍትዌር መሀንዲስ ይግረማቸው እሸቴ እንደሚሉት ይህ ቴክኖሎጅ ግለሰቦችም ሆኑ ተቋማት ከየትኛውም ቦታ፣ በማንኛው ጊዜ በየትኛውም ዓይነት ኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ያከማቹትን መረጃ ለማግኘት ያስችላል።የስሙ መነሻም ከዚህ ግብሩ ጋር የተያያዘ ነው።ይላሉ።«ክላውድ የምንለው ያው ቀጥታ ፍቹ ደመና ማለት ነው።የሚገልፀው ደመና የትም ቦታ ወደ ሰማይ ብንመለከት የትም ቦታ ሊገኝ የሚችል ነው።ክላውድም ከዚያ የመጣ ነው።ዳታችንን ወይም መረጃችንን በየትኛውም ቦታ ሆነን በየትኛውን አጋጣሚ ኢንተርኔትን በመጠቀም ማግኘት እንድንችል ነው።ለምሳሌ አንድ ሰው ላፕቶፕ ይጠቀማል ስልክ ይጠቀማል ታብሌት ሊጠቀም ይችላል።ብዙ አይነት የመገናኛ መንገዶችን ሊጠቀም ይችላል።ነገር ግን ዳታውን ያለ ቦታ ገደብ የዕቃው አይነት የተለያዬ ቢሆንም ማግኘት መቻል ነው ዋና ዓላማው። ይጠቀማል » በማለት አብራርተዋል።
ይህ ዲጅታል ቴክኖሎጅ  ከመምጣቱ  በፊት  ድርጅቶች  መረጃ የሚያስቀምጡት በማዕከላዊ የመረጃ ቋት /central database/ በሚገለገሉባቸው ኮምፒዩተሮች ሲሆን፤ ግለሰቦች ደግሞ በስልካቸው ወይም በላፕቶፓቻቸው አልያም በሲዲ እና ፍላሽ ዲስኮችን በመሳሰሉ ሀርድ ዲስኮች ነበር ። ነገር ግን እነዚህ የኤለክትሮኒክ መሳሪያዎች ከተሰበሩ ወይም ከጠፉ ውሂብን መልሶ ለማግኘት አማራጭ መንገድ አልነበረም።በጎርጎሪያኑ 1960ዎቹ  ብቅ ያለው እና በ2006  ዓ/ም ጥቅም ላይ የዋለው የሚሰራው  ክላውድ /Cloud computing / ግን ይህንን ለውጧል።ክላውድ በበይነመረብ አማካኝነት አገልግሎት የሚሰጥ ሲሆን ፤ተቋማትም ሆኑ ግለሰቦች በርካታ መረጃዎችን ረዘም ላሉ ጊዚያት ዲጅታል በሆነ መንገድ በማስቀመጥ  መረጃው ቢሰረዝ ወይም የተቀመጠበት የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ ቢጠፋ እንኳ በሌላ የኤሌክትሮኒክስ መሳሪያ  ለማግኘት እድል ፈጥሯል።
ቴክኖሎጅው ስልክ ብንቀይር እንኳ በቀድሞ ስልካችን የነበሩት ፎቶዎች፣  ቪድዮዎች፣  የጽሑፍ መልዕክቶች እና  የስልክ ቁጥሮችን የመሳሰሉ ጠቃሚ መረጃዎቻችን ወደ አዲሱ ስልካችን እንዲሸጋገር ያደርጋል።ከዚህ በተጨማሪም ባለሙያው እንደሚሉት ክላውድ እንደ መጠቀሚያ መሰረተ ልማትም ያገለግላል።«ከዚያ በተጨማሪ ክላውድ መረጃ ማስቀመጥ ብቻ ሳይሆን የአገልግሎት መጠቀሚያ ሊሆን ይችላል።ለምሳሌ ሶፍትዌር አት ኤ ስርቪስ የሚባል አለ ሶፍትዌርን ማበልፀግ ውድ ዋጋ ይጠይቃል ።በድርጅቶችም የኔትወርክ መሰረተ ልማቶችን መዘርጋት በጣም ውድ ዋጋ ይጠይቃል።»ካሉ በኋላ ይህንን ለመቀነስ ክላውድን እንደመሰረተ ልማት መጠቀም እንደሚቻል ገልፀዋል።በዚህም እንደ ባለሙያው ገለፃ ፌስቡክ እና ጅሜል ያሉ አገልግሎቶችን መጠቀም ያስችላል።

አቶ ይግረማቸው እሸቴ፤ የሶፍትዌር መሀንዲስ ምስል Privat

 

የክላውድ ቴክኖሎጅ የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና የበይነ መረብ አገልግሎት ሰጪዎችም በተሻለ ፍጥነት እንዲሠሩ አስተዋጽኦ አድርጓልምስል Nicolas Economou/NurPhoto/picture alliance


በኢትዮጵያም እንደ ራይድ ያሉ ዲጅታል የመጓጓዣ አገልግሎት ሰጭዎችን በምሳሌነት ያነሳሉ።በአጠቃላይ ክላውድ ሃርድ ዲስኮችን  እና የግል የውሂብ ማዕከሎችን ከመጠቀም ይልቅ  መረጃን ለማከማቸት በበይነመረብ የርቀት ሰርቨሮችን መጠቀም የሚያስችል ሲሆን፤ይህም ሰርቨሮችን፣ማከማዎችን፣የውሂብ ቋትን፣ሶፍትዌርን፣ በኔትወርክ ማስተሳሰርን፣ መተንተንን   እና  አስተውሎትን ያካታትታል።በዚህ ቴክኖሎጅ መረጃ የሚቀመጠው አንድ ቋት ወይም ማዕከል ውስጥ ብቻ ባለመሆኑ እና  በይነመረብ  እስካለ ድረስ፣ በማንኛውም ጊዜ፣ ከአንድ በላይ በሆኑ የኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች  ጭምር ማግኘት ያስችላል።ባለሙያው እንደሚሉት የመረጃ ማከማቻውን  ማስፋፋትም ቀላል እና አጭር  ጊዜ የሚፈልግ ነው።  
ከዚህ በተጨማሪ የክላውድ ቴክኖሎጅ  በየትኛውም ቦታ ሆኖ ስራን ለማከናወን እና በትብብር ለመስራትም  እድል ይፈጥራል።የመረጃ ደህንነትን ለመጠበቅም ያግዛል።የስማርት ስልኮቻችንን ደህንነት እንዴት እንጠብቅ?
ባለሙያው እንደሚሉት እንዲህ አይነቱን የክላውድ አገለግሎት በዋናነት ከአማዞን የድረ ገፅ አገልግሎት/Amazon website /  ከማይክሮሶፍት እና ጉግል  ከመሳሰሉ የቴክኖሎጅ ኩባንያዎች  የሚገኝ ሲሆን፤እንደ ጉግል ድራይቭ እና  ድሮፕቦክስ ያሉት ደግሞ በነፃ  አገልግሎት ከሚሰጡት መካከል ናቸው።በኢትዮጵያም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ኢትዮ ቴሌኮም ይህንን አገልግሎት ጀምሯል።በዚህ ሁኔታ  እነዚህ ኩባንያዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ውሂብን በማከማቸት፤ደህንነቱ ተጠብቆ  ረዘም  ላለ ጊዜ እንዲቀመጥም ያደርጋሉ።
የማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች እና የበይነ መረብ አገልግሎት ሰጪዎችም በተሻለ ፍጥነት እንዲሠሩ ክላውድ አስተዋጽኦ አድርጓል።ለዚህም ዩቲዩብ እና ፌስቡክን መጥቀስ ይቻላል። 
ኩባንያዎችም  ለመሠረተ ልማት ግንባታ ወጭ ሳያወጡ እና በአካል በሚታይ መሠረተ ልማት ላይ ጥገኛ ሳይሆኑ የንግድ እንቅስቃሴን ለማስፋፋት እና ውጤታማ ለማድረግ ያስችላቸዋል። በዚህም  ተቋማቱ የራሳቸውን የክምችት ማዕከል ለማቋቋም  ከሚያስፈልጋቸው  ወጪ  ጋር ሲነፃጸር የክላውድ ዋጋ ርካሽ ነው። 
በዚህ ሁኔታ ምስጋና ለክላውድ ቴክኖሎጅ ይግባው እና ሰዎች ከርቀት ሆነው አገልግሎቱን በማግኘት ኢሜሎችን፣ ሰነዶችን ቪዲዮዎችን፣ ድምጾችን  እና ሌሎች መረጃዎችን በቀላሉ ለማግኘት  አስችሏል።
በዋጋ ደረጃ  ርካሽ መሆኑ፣የመረጃ ደህንነትን የሚጠብቅ መሆኑ፣  በየትኛውም  ጊዜ እና ቦታ ያለገደብ የሚገኝ መሆኑ የዚህ ቴክኖሎጅ ዋናዋና ጥቅሞች  ናቸው።በሌላ በኩል  ያለ ኢንተርኔት የማይሰራ መሆኑ፣ ምንም እንኳ ከፍተኛ ጥበቃ የሚደረግበት ቢሆንም በበይነመረብ ዓለም አይሆንም የሚባል ነገር የለም እና የጥቃት ዒላማ ቢሆን እና ለጥቃት ቢጋለጥ፤ከፍተኛ መረጃ አንድ ቦታ የሚከማችበት ከመሆኑ  ጉዳቱ ከፍተኛ መሆኑ ደካማ ጎኖቹ ናቸው።በስልኮቻችን የሚገኙ ግላዊ መረጃዎቻችን ከመንታፊዎች እንዴት እንከላከል?ስለሆነም መረጃን ከፋፍሎ በተለያዩ ቦታዎች ማስቀመጥ እና እጅግ ጠቃሚ የሆኑ እንደ ገንዘብ ነክ ያሉ መረጃዎችን ክላውድ ውስጥ አለማከማቸት፤ ካስቀመጥንም ማመስጠሪያ ሶፍትዌሮችን መጠቀም እና በጠንካራ የይለፍ ቃል መቆለፍ መፍትሄ መሆኑን የሶፍትዌር መሀንዲሱ ይግረማቸው እሸቴ ጠቁመዋል።

ዘመናዊ የውሂብ ማከማቻ እሳቤ ፤የክላውድ ቴክኖሎጅ  በየትኛውም ቦታ ሆኖ ስራን ለማከናወን እና በትብብር ለመስራትም  እድል ይፈጥራል፤የመረጃ ደህንነትን ለመጠበቅም ያግዛልምስል Channel Partners/Zoonar/picture alliance

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

ፀሀይ ጫኔ
ነጋሽ መሀመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW