1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮሌራን በስምንት ዓመት የማጥፋቱ ዕቅድ ተግዳሮቶች

ዓርብ፣ ታኅሣሥ 21 2015

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር በቀጣይ ስምንት ዓመታት ውስጥ ኮሌራን ከሀገሪቱ የማጥፋት ዕቅዱን ከሰሞኑ ይፋ አድርጓል። እንዲህ ያለው ዕቅድ መኖሩ አዎንታዊ ቢሆንም ተግባራዊነቱን የሚፈታተኑ ዘርፈ ብዙ ጉዳዮች መኖራቸውን ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የህክምና ባለሙያዎች ይናገራሉ።

Symbolbild UNO Entwicklungshilfekonferenz
ምስል dpa/DW

«የንጹሕ ውኃ አቅርቦትና እና የመጸዳጃ አጠቃቀም»

This browser does not support the audio element.

የዓለም የጤና ድርጅት ሃገራት አቅማቸውን አስተባብረው የኮሌራ ወረርሽኝን በጎርጎሪሳዊው 2030 ዓ,ም ለማጥፋት እንዲሠሩ ጥሪ ካቀረበ ሰነባብቷል። ቫይብሪዮ ኮሌራ በተባለ ጀርም አማካኝነት በተለይም ንጹሕ ያልሆነ ውኃን በመጠቀም የሚስፋፋው ይህ ተላላፊ በሽታ መጠነኛ ወይም ምን አይነት የህመም ምልክት ሳያሳይ አፋጣኝ ተቅማጥ፣ ማስመስ እንዲሁም የሆድ ቁርጠትን እንደሚያስከትል መረጃዎች ያመለክታሉ። በበሽታው ምክንያት ከሰውነት በርካታ ፈሳሽ በመውጣቱም የታመመውን ሰው አዳክሞ ሕይወት እስከማሳጣት ያደርሳል። በተለያዩ ጊዜያት የኮሌራ ወረርሽኝ ኢትዮጵያን ጨምሮ በበርካታ መሠረተ ልማት ባልተስፋፋባቸው ሃገራት ይከሰታል። የንጹሕ ውኃ አቅርቦት፣ የተሻለ የንጽሕና መጠበቂያ እና ህክምናን በአግባቡ ለሁሉም ማዳረስ ኮሌራን ከዓለም ለማጥፋት ዋነኛ እንቅፋት እንደሆነ ነው በየጊዜው የሚነገረው። እንዲህ ያለው የመሠረተ ልማት ውሱንነት ካለባቸው ሃገራት በግንባር ቀደምትነት ከሚጠቀሱት አንዷ ደግሞ ኢትዮጵያ ናት። በርካቶች ዛሬም ለንጹሕ ውኃ አቅርቦት እሩቅ ናቸው። መረጃዎች እንደሚያሳዩት በጎርጎሪዮሳዊው 202 ዓ,ም ካለው አጠቃላይ የሕዝብ ብዛት ንጹሕ ውኃ የሚያገነው 12,5 በመቶው ነው። የንጽሕና መጠበቂያ አቅርቦትን በተመለከተም በገጠርም በከተማም ካለው ሕዝብ የተዳረሰው ለ50 በመቶው ነው።

ጽዳት የጎደለው አካባቢ ለኮሌራ መስፋፊያ ምክንያት እንደሚሆን የህክምና ባለሙያዎች ይገልጻሉምስል AP

የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እስከ ጎርጎሪዮሳዊው 2028 ዓ,ም ድረስ የኮሌራ ወረርሽኝን ለማጥፋት እየሠራ መሆኑን ይፋ አድርጓል። በሽታውን ለመከላከል መሠረታዊ የሆነው የውኃም ሆነ የመጸዳጃ አገልግሎት በሌለበት ኢትዮጵያ ውስጥ በአጭር ዓታት ውስጥ የታሰበውን ለማሳካት እንደሚከብድ አስተያየታቸውን የሰጡን የህክምና ባለሙያዎች ያስረዳሉ። ሲስተር ኂሩት ፍሰሀ በደቡብ ኢትዮጵያ፤ ዕቅዱ አስደሳች ቢሆንም ማኅበራዊ እና ኤኮኖሚያዊ መሻሻሎች ሳይኖሩ ለማሳካት እንደሚከብድ ተናግረዋል። የኮሌራ በሽታን ከኢትዮጵያ ለማጥፋት የተያዘው እቅድጀርመን ሀገር ከ30 ዓመታት በላይ በህክምና ሙያቸው ያገለገሉት ዶክተር ውብታየ ዱሬሳም እንዲሁ በድህነት ኑሮውን በሚገፋ ኅብረተሰብ መካከል የተባለውን በአጭር ጊዜ ማሳካት አዳጋች የሚያደርጉትን ጉድለቶች ለማስተካከል ጊዜ እንደሚፈልግ አመልክተዋል። የህክምና ባለሙያዎች አስተያየት የሚጋሩት ከ40 ዓመታት በላይ በማኅበረሰብ ጤና ዘርፍ ያገለገሉት ዶክተር መኮንን አይችሉህም በበኩላቸው ዕቅዱ አዎንታዊ ቢሆንም ከአቅም እና ካለው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር እንደማይገናኝ ነው ያመለከቱት። የታሰበውን ለማሳካትም አስቀድሞ የንጹሕ ውኃ አቅርቦትን እና የመጸዳጃ አገልግሎት ተጠቃሚነትን ማስፋፋትን የመሳሰሉ መሠረተ ልማቶች ላይ ብዙ መሥራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል። የዓለም የጤና ድርጅት ከአንድ ዓመት በፊት በ23 ሃገራት የኮሌራ ወረርሽኝ የመከሰቱ መረጃ እንደደረሰው መዝግቧል። ወረርሽኙም የበርካቶችን ሕይወት የቀጠፈ ሲሆን በሽታው የተከሰተባቸው አብዛኛዎቹ ሃገራት ደግሞ በአፍሪቃ እና በምሥራቃዊ ሜዲትራኒያን አካባቢ የሚገኙ መሆናቸውን አመልክቷል።

 ሸዋዬ ለገሠ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW