«የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየቀነሱ ይሄዳሉ ብየ አምናለሁ»፦ አዲሱ የኢሰመኮ የበላይ ኃላፊ
ማክሰኞ፣ የካቲት 18 2017
ኢትዮጵያ ውስጥ የጋራ የሚያስተሳስሩ እሴቶች እየተሸረሸሩ መምጣት ለሰብአዊ መብት ጥሰቶች ምክንያት ናቸው ሲሉ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ዋና ኮሚሽነር ተናገሩ ። መንግሥት ሕገ መንግሥቱን እና የፈረማቸውን ዓለም አቀፍ ድንጋጌዎች ሊያከብር እና ሊያስከብር ይገባል ያሉት ኮሚሽነር ብርሃኑ አዴሎ፤ በተቋሙ የአመራር ለውጥ መደረጉ የኮሚሽኑን ሥራ በምንም ምክንያት ወደ ኋላ አይመልሰውም ብለዋል ።
በመብት ጥሠት ላይ በሚያደርጉት የምርመራ ሥራ ጣልቃ የመግባት ጫና እንዳልደረሰባቸው የሚገልፁት ኃላፊው፤ የተቋሙን ነፃነት የሚጋፋ መሰል ችግር የሚገጥማቸው ከሆነ ለሕዝብ እንደሚያሳውቁ ተናግረዋል ።
«ኮሚሽኑ አለቀለት የሚሉ ሰዎች አሉ» ዋና ኮሚሽነር ብርሃኑ
ጥር 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብሔራዊውን የኢትዮጵያ የመብቶች ተቋም - ኢሰመኮን እንዲመሩ የተሾሙት አቶ ብርሃኑ አዴሎ፣ ኮሚሽኑ የሚሠራቸውን ሥራዎች የማስቀጠል ጥረት እንደሚወጡ፣ በሰብዓዊ መብት ረገድ ግንዛቤን ማሳደግ ላይ እንደሚያተኩሩ እና ለዚህም መብቶችን በቋሚነት ማስተማር የሚችል ተቋምን የማቋቋም ጥረት እንደሚያደርጉ ተናግረዋል። የአመራር ለውጡን ተከትሎ "ኮሚሽኑ አለቀለት" የሚሉ ሰዎች አሉ ያሉት ኃላፊው "መተሳሰብ፣ አንድነት፣ መከባበር ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሸረሸሩ ሲሄዱ እናያለን" ብለዋል። የመብት ጥሰቶችን ለመቀነስ ደግሞ ሕገ መንግሥት በመንግሥት እንዲከበር የግድ ነው ብለዋል።
"መንግሥትም በተገቢው በሕግና ሥርዓት ብቻ እንዲሠራ የማድረግ ሥራ ነው መሠራት ያለበት። ሕግን ማክበር መቻል አለበት። ሕገ መንግሥቱ መከበር አለበት።"
«መንግሥትን ጫና የሚያደርግ ከሆነ ለሕዝብ እናሳውቃለን፤ ጫናን አንቀበልም»
የኮሚሽኑ በነፃነትና በገለልተኝነት ሥራውን የማከናወኑን ጉዳይ በሚመለከት ለቀረበላቸው ጥይልቄ ምላሽ የሠጡት ኃላፊው ኮሚሽኑ አመሠራረቱ በሕገ መንግሥት ድጋፍ ያለው መሆኑን በመጥቀስ ለአብነትም የበጀት ነፃነት ያለው መሆኑን ገልፀዋል። "የአመራር እንጂ የአሠራር ለውጥ አልተደረገም" በማለት በየትኛውም መሥፈርት ሥራቸው ወደኋላ የሚመለስ እንደማይሆንም አብራርተዋል።
በመንግሥት በኩል እስካሁን የደረሰብኝ ጫና የለም ያሉት የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር አቶ ብርሃኑ አዴሎ፣ መሠል ጉዳዮች ቢመጡ አንቀበልም ብለዋል። "የተቋሙን ነፃነት የሚጋፋ፣ በነፃነት ገብተን እንዳንመረምር ጫና የማድረግ ነገር ካለ ለሕዝብ አናሳውቃለን እንጂ የምንደብቀው ነገር አይኖርም"። ሲሉም ዋስትና ሰጥተዋል።
«እንዳናወጣ የተከለከልነው የምርመራ ውጤት የለም»
ኢሰመኮ ባለፈው ዓመት ባደረገው የሰብዓዊ መብቶች ሁኔታ ዓመታዊ የምርመራ ውጤት በርካታ ሰዎችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳት ተዳርገዋል፤ በሕይወት የመኖር መብት አሳሳቢ ጉዳይ ሆኖ መቀጠሉን፣ የመንቀሳቀስ መብት ፈተና ላይ መውደቁንም አመልክቷል። ከዚያ በፊትም በሰብአዊነት ላይ የተቃጡ እና የጦር ወንጀልን ሊያሟሉ የሚችሉ የመብት ረገጣዎች እና ግዙፍ ወንጀሎች መፈፀማቸውን አስታውቋል ።
እስካሁን የተፈፀሙ የመብት ጥሰቶች በሽግግር ፍትሕ ተጠያቂነት ይሰፍናል የሚል እምነት እንዳላቸው እና አለም አቀፍ ወንጀሎችን የሚዳኙ የሕግ ድንጋጋዎች በሀገሪቱ የሕግ ማእቀፍ ውስጥ እንዲካተት የማድረግ ጥረት መኖሩን ጠቁመዋል። ኮሚሽኑ እንዳያወጣ የታገደበት የምርመራ ውጤት አለመኖሩንም ገልፀዋል።
የታገዱ ሲቪክ ድርጅቶች ጉዳይ እና የምኅዳሩ ነገር
በመንግሥት የታገዱ አራት የሲቪክ ድርጅቶችን በተመለከተ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች አስተዳደራዊ ቦርድ ጉዳዩ መመርመር ነበረበት ያሉት ኃላፊው ቦርዱ አሁን በአግባቡ ሥራውን እየሰራ አይደለም ብለዋል። ስለሆነም ቦርዱ በአስቸኳይ ተቋቁሞ አቤቱታቸውን ሊመለከት ይገባል ብለዋል። በቀጣይ ሀገር አቀፍ ምርጫ ከመኖሩ ጋር ተያይዞም ሲቪክ ድርጅቶች በነፃነት በስፋት መንቀሳቀስ አለባቸው ሲሉ ገልፀዋል።
«የሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየቀነሱ ይሄዳሉ የሚል እምነት አለኝ» የሚል ተስፋ እንዳላቸውም ገልፀዋል ። በሥልጣን ዘመናቸው የዜጎች በነፃነት የመንቀሳቀስ እና አጠቃላይ የሰብአዊ መብቶች መከበር ጉዳይ ሠርተው ሊያሳዩት የሚፈልጉት ውጥን መሆኑንም ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል ።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ዮሐንስ ገብረ እግዚአብሔር