1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮቪድ 19ና የጤና ባለሙያዎች ግብግብ በኢትዮጵያ

ማክሰኞ፣ ሰኔ 9 2012

ኢትዮጵያ ውስጥ በኮቪድ 19 ተሐዋሲ የተያዘ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ መገኘቱ የተነገረ ሰሞን የታየው ጥንቃቄ የላላ መምሰሉን የሚናገሩ አሉ። በኅብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው ችላ ባይነት በመገናኛ ብዙሃን በየዕለቱ የሚነገረው በሌሎች ሃገራት የደረሰውን ጉዳት ያገናዘበ አይመስልም። የጤና ባለሙያዎች ለተሐዋሲው የመጋለጣቸው ጉዳይ አሳሳቢ ሆኗል።

Deutschland Forschung Coronavirus
ምስል picture-alliance/dpa/C. Gateau

« ድጋፍ የሚያሻቸው የኢትዮጵያ የጤና ባለሙያዎች»

This browser does not support the audio element.

ኢትዮጵያ ውስጥ በኮቪድ 19 ተሐዋሲ የተያዘ ሰው ለመጀመሪያ ጊዜ መገኘቱ የተነገረው የዛሬ ሦስት ወር ገደማ ነው። በወቅቱ በሌላው ዓለም በተለይም የኤኮኖሚ አቅማቸው የዳበረ፤ የጤና ሥርዓትና አገልግሎታቸው የተጠናከረ በሚባሉ ሃገራት ተሐዋሲው በየዕለቱ በመቶዎች የሚቆጠሩትን እየገደለ ሺህዎችን ደግሞ እየበከለ የማደሩ ዜና ሁሉንም አደናግጦ ግራ ማጋባቱ ይታወሳል።  ለዚህም ይመስላል ገና ጥቂቶች የመያዛቸው ዜና ኢትዮጵያ ውስጥ ሲሰማ ከመደናገጥ የመነጨው የጥንቃቄ ዝግጅት በየቦታው የታየው። ሕዝብ ያዘወትራቸዋል ይሰበሰብባቸዋል የሚባሉት ቤተ እምነቶችን እስከመዝጋት ምህላና ዱአውን በቴሌቪዥን እስከማድረስ ተሄዶ፣ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው፤ አንዳንድ መሥሪያ ቤቶችም ሠራተኞቻቸውን ከቤታቸው እንዲሠሩ አደረጉ። እንዲያም ሆኖ ስለኮሮና መዝፈኑ ሁሉ እንዳለ ሆኖ ሰዎች በየጎዳናው እጃቸው እንዲታጠቡ የሚያግባቡ አልፈውም የሚያስገድዱ እንቅስቃሴዎች የአንድ ሰሞን ታይታ መምሰሉን በቅርብ የሚያስተውሉ ይገልጹታል። ዋል አደር ብሎ በተሐዋሲው የተያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ሕይወትም እየቀጠፈ ሲመጣ ጭራሽ ተሐዋሲው በመገናኛ ብዙሃን ብቻ የሚነገር፤ የሚጠራው የታማሚና ሟች ቁጥርም እንደው ቁጥር ይመስል መዘናጋቱ ሲታይ ነገ በጭንቅ እንዲታሰብ ግድ እንደሚሆንም ይናገራሉ። አሁን የሚታየው የታማሚዎች መበርከትም ላልጠናው የሀገሪቱ የጤና ስርዓት ፈተናነቱ የማይቀር ነው። በዚያህ ላይ የህክምና ባለሙያዎች ለተሐዋሲው መጋለጥ ሲታከልበት ስጋቱ ያይላል። ዶክተር ሄኖክ ሰይፈ በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል የጉበትና ቆሽት ቀዶ ጥገና ህክምና ከፍተኛ ባለሙያና ረዳት ፕሮፌሰር ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት በኮቪድ 19 ተሐዋሲ የተያዙ ሕሙማን የሚታከሙባቸው ሃኪም ቤቶች ተለይተው ለዚሁ አገልግሎት ተዘጋጅተዋል። ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ቀዶ ህክምናዎችን ጨምሮ  የተለያዩ የጤና ችግር ላይ የሚገኙ ወገኖችን የማከም ተግባሩን አላስታጎለም። በዚህ መሀል በተሐዋሲው የተያዘ ታማሚ በአጋጣሚ ቢኖር እንኳ ሳይጠረጠርና ምርመራም ሳይደረግለት እዚያ የሚቆይበት አጋጣሚ ስለሚኖር በየደረጃው ያሉ ባለሙያዎች ለተሐዋሲው የመጋለጥ ዕድላቸው እንደሚሰፋና ይህም አሳሳቢ እንደሆነ አመልክተዋል። ክሊኒካል ነርስ የሆኑት ሲስተር መዓዛ ኃይሉ በዚህ ረገድ እንዳስተዋሉት በጤና ተቋማት የመመርመሪያ መሣሪያም ሆነ ባለሙያው ራሱን የሚከላከልበት የለውም። ኢትዮጵያ ከ100 ሚሊየን ለሚበልጥ ህዝቧ ያሏት የህክምና ባለሙያዎች ከመቶ ሺህ እንደማይበልጡ መረጃዎች ያመለክታሉ። እነዚህ የህክምና ባለሙያዎች እንደጌጥ በየቦታው ተበትነው የሚያገለግሉ እንደመሆናቸው በያሉበት የአገልግሎት ስፍራ ተገቢው ራሳቸውን ከተሐዋሲው የመከላከያ ቁሳቁሶች በበቂ ደረጃ ከሌሏቸው ለበሽታ ተጋልጠው የቅርብ ሰዎቻቸውም ሰለባዎች መሆናቸው የማይቀር ነው። እነሱ ሌሎችን በሙያቸው እንዲረዱ ቢያንስ በዚህ ወቅት እንኳን ከጎናቸው ለመቆም በተለይ በውጭ ሀገር ከሚገኘው ወገን ብዙ ይጠበቃል። አንዳንዶች ይህን ለማስተባበር እየሞከሩ መሆኑ ይሰማል። ጥሪው ግን ለሁሉም ነው።

ምስል AFP/M. Tewelde

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW