1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የ«ፓሲቭ ኢሚዩናይዜሽን» ህክምና

ረቡዕ፣ ሚያዝያ 7 2012

ይህ ህክምና ልክ እንደ ወይዘሮ ስቴፋኒ ከዚህ በፊት በበሽታዉ ተይዘዉ ካገገሙ ሰዎች ላይ «ፕላዝማ» የተባለዉን በደም ዉስጥ የሚገኝ የሰዉነት ንጥረ- ቅመም በመውሰድ ሌሎች በበሽታው ለሚሰቃዩ ሰዎች በክትባት መልክ የሚሰጥ ነው። ይህ ንጥረ ቅመም የታማሚዎቹ ሰዉነት ቫይረሱን የመዋጋት አቅም በጊዜያዊነት እንዲዳብር ለማድረግ የሚረዳ ነዉ።

Blutabnahme und Blutspende
ምስል picture-alliance/Eibner/D. Fleig

የ«ፓሲቭ ኢሚዩናይዜሽን» ህክምና ለኮሮና

This browser does not support the audio element.

ሰዉነትን የሚጎዱ ተዋህሲያንን በመዋጋት ከበሽታ ቶሎ እንድናገግም ለማድረግ ዋነኛ ሚና የሚጫወተዉ የሰውነታችን በሽታ የመከላከል አቅም ነው። የሰዉነት የተፈጥሮ መከላከያ አቅም እንደ አመጋገባችንና እንደ አኗኗር ዘይቤያችን ከሰዎች ሰዎች ይለያያል። በዚህም የተነሳ በአንድ አይነት በሽታ ከተያዙ ሰዎች ዉስጥ አንዳንዶቹ ከበሽታዉ ቶሎ ሲያገግሙ አንዳንዶቹ ደግሞ እስከ ሞት ሊደርሱ ይችላሉ። እንደ ዓለም አቀፉ የጤና ድርጅት መረጃም በኮሮና ተዋህሲ ከተያዙ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች መካከል በመቶ ሺህ የሚቆጠሩት የመሞታቸዉን ያህል በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎች ከበሽታዉ አገግመዋል። የሁለት ልጆች እናት የሆኑት የኒዮርክ ከተማ ነዋሪዋ ወ/ሮ ስቴፋኒ ፒክኒ ከነዚህ መካከል አንዷ ናቸዉ።ወይዘሮዋ ታመዉ አልጋ ላይ የዋሉበትን ወቅት እንዲህ ያስታዉሱታል። 
« አስታዉሳለሁ ፤ከበሽታዉ ጋር በምታገልበት ጊዜ አለቅሳለሁ፣ እፀልያለሁ እናም እባክህ አምላኬ ከዚህ በሽታ መዳን እፈልጋለሁ እያልኩ እማፀንም ነበር።» 
ተመራማሪዎችም የኮቪድ-19ን በሽታ ክትባትና መድሃኒት ለማግኘት ከሚያደርጓቸዉ ምርምሮች ጎን ለጎን የሰዎችን የተፈጥሮ የበሽታ መከላከል አቅምን ለመጨመር የሚያግዝ «ፓሲቭ ኢሚዩናይዜሽን»የተባለ ህክምና በመሞከር ላይ ይገኛሉ። ይህ ህክምና ልክ እንደ ወይዘሮ ስቴፋኒ ከዚህ በፊት በበሽታዉ ተይዘዉ ካገገሙ ሰዎች ላይ «ፕላዝማ» የተባለዉን በደም ዉስጥ የሚገኝ የሰዉነት ንጥረ- ቅመም በመውሰድ ሌሎች በበሽታው ለሚሰቃዩ ሰዎች በክትባት መልክ የሚሰጥ ነው። ይህ ንጥረ ቅመም የታማሚዎቹ ሰዉነት ቫይረሱን የመዋጋት አቅም በጊዜያዊነት እንዲዳብር ለማድረግ የሚረዳ ነዉ።በቦን ዩንቨርሲቲ የማይክሮባዮሎጅ የህክምና ተቋም ዳይሬክተር የሆኑት ዶክተር አሂም ሆርአዉፍ እንደሚሉት ህክምናዉ ቀደምት ነዉ። 
«ፓሲቭ ኢሚዩናይዜሽን በእርግጥ የቆየና ወደ አንድ መቶ አመት ገደማ ያስቆጠረ ፅንሰ ሀሳብ ሲሆን ፤በሽታዉን የመቋቋ አቅም ካላቸዉና ካገገሙ ሰዎች ደም ዉስጥ የመከላከያ ንጥረ ነገር በመዉሰድ ሌሎች ታማሚዎች ከበሽታዉ መዳን እንዲችሉ የሚሰጥ ነዉ።» 
በዚህ መሰረት የኒዮርክ ከተማ ነዋሪዋ ስቴፋኒም በዚህ የህክምና ዘዴ ሌሎች በኮቪድ-19 በሽታ የታመሙ ሰዎችን ለመርዳት በደማቸዉ ውስጥ የሚገኘዉን «ፕላዝማ» የተባለ ንጥረ ነገር ለግሰዋል። 
« በእርግጥ በጣም የሚያስገርም ነው።ከበሽታዉ በመዳኔ በጣም ደስተኛ ነኝ። አዉቃለሁ በእኔ ደም ዉስጥ መልስ ሊኖር ይችላል።» 
ያም ሆኖ የለገሱት የደም ህዋስ ዉጤታማነት መልስ ያለዉ የህክምና ባለሙያዎች እንደሚሉት በእሳቸዉ የደም ህዋስ ውስጥ የሚገኘው «ፕላዝማ» ለየት ያለ ተዋህሲውን የመቋቋም የተፈጥሮ ነጥረ-ነገር የሚያመነጭ ከሆነ ብቻ ነዉ።እንደ ዶክተር አሂም የለጋሹ የደም አይነትም ወሳኝ ነው። 
« ለሌላ ሰዉ ደም ሲለገስ የደም አይነት አለመመሳሰል ችግር ሊኖር እንደሚችል የታወቀ ነዉ። ስለዚህ ከምርመራ በፊት የደም ህዋስ በቀጥታ ስራላይ ይዉላል ተብሎ አይታሰብም።ከዚህ በተጨማሪ በሽታን የሚከላከለዉ ንጥረ ነገር የሚገኘው በደም ህዋስ ወይም በጠቅላላ ሰዉነት ሳይሆን የሚገኘዉ በማዕከላዊው «ፕላዝማ» ዉስጥ ነው።» 
በሌላ በኩል ይህ ጊዜያዊ የበሽታ መከላከያ ህክምና ጥቅም ላይ የሚውለው የታማሚዉ በሽታን የመከላከል አቅም ቀድሞውኑ ቫይረሱን ለመዋጋት ስራ ሲጀምር ብቻ መሆኑን ባለሙያዉ አስረድተዋል። 
ከዋሽንግተን ዩንቨርሲቲ ዶክተር ጀፈሪ ሂንደርሰን እንደሚሉት ደግሞ «ፓሲቭ ኢሙዩናይዜሽን»የረጅም ጊዜ መከላከያ አይደለም። 
«ይህ ፓሲቭ ኢሚዩናይዜሽን ወይም ድንገተኛ ክትባት የአንድን ሰዉ ተዋህሲዉን የመቋቋም አቅም ለአጭር ጊዜ ለማጎልበት የሚያግዝ ዘዴ ነው።ከክትባት በፊትም ጥቅም ላይ መዋል ይችላል።» 
ይህ ህክምና ከክትባት የሚለየዉም ለዚህ ነዉ።«ፓሲቭ ኢሚዩናይዜሽን»የታማሚው ሰውነት በራሱ የበሽታ መከላከያ ስላላመረተ የሚሰጥ ድጋፍ ሲሆን ፤ ክትባት ግን በሽታ አምጪ ተዋህሲያንን ሰውነትን በማይጎዳ መልኩ ለሰዎች በመስጠት በሽታ ተከላካይ ሕዋሳቶች እንዲያወቋቸው ማድረግ ነዉ። ሰውነታችንም እነዚህን ተዋህሲያን እንደ ወራሪ ስለሚያያቸው ወዲያውኑ መዋጋት ይጀምራል።ሰውነታችን ከዚያ በፊት ተጠቅቶ ቢሆን እንኳ ክትባት በሚያገኝበት ወቅት የሰዉነት ህዋሳት እንዴት መዋጋት እንዳለባቸው ስለሚያውቁ ወዲያውኑ ሥራ ይጀምራሉ።ይህ የመከላከል ሂደትም እንደየ ክትባቱ አይነት ከዓመታት እስከ ህይወት ዘመን ሊዘልቅ የሚችል ነው። የ ።«ፓሲቭ ኢሚዩናይዜሽን« ግልጋሎት ግን ለጥቂት ሳምንታት ብቻ የሚያገለግል ነዉ።ያ የሆነበት ምክንያት ደግሞ ከበሽታዉ ባገገሙ ሰዎች የተለገሱት ንጥረ ቅመሞች በተቀባዩ የደም ህዋሳት አማካኝነት ከአንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ዉስጥ ስለሚሰባበሩ መሆኑን ባለሙያዎች ያስረዳሉ። 
ከዚህ የአጭር ጊዜ ግልጋሎቱ በተጨማሪ ይህንን ህክምና የወሰደ ሰዉ ሰውነቱ ዘላቂ የሆነ በሽታን የመከላከል አቅም በራሱ ስላላመረተ በተመሳሳይ በሽታ አምጪ ተዋህሲ እንደገና የመጠቃት ዕድሉ የበለጠ መሆኑም ሌላው አሉታዊ ጎኑ ነዉ። 
ያም ሆኖ ይህ የህክምና ዘዴ በአሁኑ ወቅት ከነ ዉስንነቱም ቢሆን በኮቪድ-19 የተያዙ ፅኑ ህሙማንን ህይወት ለመታደግ ብቸኛ መፍትሄ መሆኑን ዶክተር አሂም ይገልፃሉ። 
«በእርግጥ ክትባት አይደለም።ሚሊዮኖችንና ወይም ቢሊዮኖችን መከላከል አይችልም።ያ ብዙ ጥረት ይጠይቃል።ነገር ግን ፅኑ ህሙማን በጣም የመጎዳት ወይም የመሞት ዕድል እንዳላቸዉ ታይቷል።እነሱን ለመርዳት «ፕላዝማን» ከበሽታዉ ካገገሙ ሰዎች በመዉሰድ የሚሰጠዉ ህክምና ተዋህሲዉ በፍጥነት እንዲቀንስ አድርጓል።ይህ ተዋህሲዉን የሚያደርሰዉን ጉዳት ለመቀነስ በአሁኑ ወቅት ልንሰራዉ የምንችለዉ ብቸኛዉ ዘዴ ነዉ።» 
ስለሆነም በአሁኑ ወቅት ሁነኛ ክትባትም ይሁን መድሃኒት ያልተገኘለትን የኮቪድ-19 በሽታ ለማከም በጥቂቱም ቢሆን ሊረዳ የሚችለዉ ይህ ህክምና ዘዴ በመሆኑ ከበሽታዉ ያገገሙ ሰዎች የደም ህዋስ ልገሳ አስፈላጊ መሆኑን ባለሙያዎቹ ገልፀዋል። ስቴፋኒ ፒኪኒም ሌሎች የሳቸዉን ፈለግ እንዲከተሉ ይመክራሉ ። 
«እኔ በእርግጠኝነት የምመክረዉ ከህመሙ ያገገሙና ተመርምረው ከተዋሲው ነፃ የሆኑ ሰዎች በደማቸዉ የሚገኘውን«ፕላዝማ» እንዲለግሱ ነዉ።ምክንያቱም ይህ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ሰዎችን ህይወት ለመታደግ ይረዳልና» 
«ፓሲቭ ኢሚዩናይዜሽን» ከጎርጎሮሳዉያኑ 1890 ዓ/ም ጀምሮ በጀርመናዊዉ የበሽታ መከላከያ ባለሙያ /ኢሚኖሎሎጅስት/ ኤሚል ፎን ቤሪንግ ስራ ላይ የዋለ ሲሆን በወቅቱም በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ህፃናትን የገደለውን «ዲፍቴሪያ »የተባለ በባክቴሪያ አማካኝነት የሚመመጣ የአፍንጫና የጉሮሮ በሽታን ለማከም አገልግሏል።ህክምናው ቆይቶም በ1918 ተከስቶ ለነበረዉ የስፔን ጉንፋን ወይም «ስፓንሽ ፍሉ» ተብሎ የሚጠራዉን ወረርሽኝ በሽታ ለማከም ውጤታማ እንደነበር ይነገራል።ይህ የህክምና ዘዴ በምዕራብ አፍሪቃ በ2014 ዓ/ም ተከሰቶ የነበረዉን የኢቮላ በሽታ ለማከም ያገለገለ ሲሆን በወቅቱ የሞት መጠንን 30 በመቶ እንዲቀንስ ማድረጉን ዘገባዎች ያሳያሉ። 
የዚህ ህክምና ዘዴ ፈጣሪ ጀርመናዊዉ ኢሚል ፎን ቤሪንግ ለቲታነስና ለዴፍቴሪያ በሽታዎች ከደም ህዋስ የሚወሰዱ ዉጤታማ መድሃኒቶችን በማዘጋጀት በጎርጎሮሳዊዉ 1901 ዓ/ም የመጀመሪያው የህክምና ሳይንስ የኖቤል ተሸላሚም ነበር። 

ምስል picture-alliance/dpa/F. Bungert
ምስል DW/P. Stojanovski
ምስል picture-alliance/dpa/NurPhoto/J. Nacion

ፀሐይ ጫኔ 
ሂሩት መለሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW