1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ዓርብ፣ ነሐሴ 29 2012

የዛሬው የወጣቶች ዓለም ዝግጅት የወጣቱን የመቆጠብ ልምድ እና ባህል ይቃኛል። የኢኮኖሚ ባለሙያ ምክሮችንም አካተናል።

Äthiopien Währung Birr
ምስል DW/Eshete Bekele Tekle

This browser does not support the audio element.

ኮሮና ወረርሽኝ ይህን ያህል የዓለም ኢኮኖሚን ያናጋል ብሎ የጠበቀ አልነበረም።በኮቪድ 19 የተነሳ 20 ሚሊዮን የሚሆኑ አፍሪቃውያን ስራቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ በሚያዚያ ወር የወጣው የአፍሪቃ ህብረት ቅድመ ትንበያ ያመላክታል። በተለይ በአንዳንድ ሀገራት ለወራት ተጥለው በነበሩ እና ባሉ የእንቅስቃሴ እገዳዎች የተነሳ የብዙዎች የገቢ ምንጭ ሙሉ በሙሉ ተቋርጧል። አንዳንዶች ከዚህ ቀደም በቆጠቡት ገንዘብ ወራቱን ሲገፉ ሌሎች ደግሞ አስቀድመው ባለመቆጠባቸው የተነሳ ወይም ኑሯቸው ከእጅ ወደ አፍ በመሆኑ ለከፍተኛ ችግር ተዳርገዋል። ይሁንና ከዚህ ቀውስ ምን እንማራለን? ልንቀይረው ወይም ልንፈትሸው የምንችለውስ ነገር ምንድን ነው?

የዮንቨርስቲ ተማሪዋ ምህረት ዘሪሁን ቁጠባን እንደ መሠረታዊ እና እንደ ባህል ልንወስደው የሚገባን ነገር ነው ብላ ታምናለች። የ 19 ዓመቷ ወጣት የቁጠባ ደብተር ከባንክ አውጥታ መቆጠብ የጀመረችው ገና የ8ኛ ክፍል ተማሪ ሳለች ነው። በፊት የቆጠበጥው ገንዘብ በዚህ በኮሮና ወቅት ጠቅሟታል። « የራስሽ የሆነ ነገር ነው። የሆነ እርካታ አለው። በዚህ ጊዜ ቤተሰብ መጠየቅ ከባድ ነው።»

ናትናኤል ይድነቃቸው ተወልዶ ያደገው ጅማ ከተማ ነው። ከ 10ኛ ክፍል አንስቶ ትምህርቱን በአዲስ አበባ ከተማ ነው በመከታተል ላይ የሚገኘው። አሁን የዮንቨርስቲ ተማሪ ነው። እሱም ከሚቆጥቡት ተርታ ይመደባል። « ከቤተሰብ የወሰድኩት ልምድ ነው። ከልጅነቴ አንስቶ አባቴ እንድቆጥብ ይገፋፋኝ ነበር።» ከምህረት እና ናትናኤል የተለየ አመለካከት ያላት የ 21 ዓመቷ ፀጋ ጌታቸው ናት። ቁጠባ የሚባል ነገር አታውቅም አትወድምም« ስለነገ መጨነው አልፈልግም፣ ዛሬ ነው መኖር የምፈልገው።» ገንዘቧን ለፀጉር ቤት ፣ ለጥፍር ስራ፣ ከጓደኞች ጋር ሻይ ቡና ለማለት በማውጣት ታጠፋለች። ፀጋ የኮሮና ወረርሽኝ ያስከተለውን ቀውስ ካየች በኋላስ ሀሳቧን ቀይራ ይሆን? አዎ! ግን ሁኔታዎች አስገድደዋት እንጂ የግድ ለመቆጠብ ብላ ያደረገችው አይደለም። « አሁን ከቤት አንወጣም ስለዚህ ምንም የምናወጣው ገንዘብ የለም» ስለዚህ ያለኝንም እንዲቀመጥ አድርጎታል ትላለች።

ምስል DW/C. Mwakideu

ናትናኤል ቁጠባ የጀመረው 10 ብር ከፍሎ በከፈተው የባንክ የቁጠባ ደብተሩ ነው። መቆጠብ ሲጀምር «እዚህ ነገር ላይ አውለዋለው ብዬ የጀመርኩት አይደለም» ይላል። በተፈጥሮዬ በባጀት ነው የምንቀሳቀሰው የሚለው ናትናኤል ካሰበው በላይ ያወጣባቸው አጋጣሚዎችም ነበሩ። ምህረት ደግሞ ለመቆጠብ የገንዘብ ልክ የለውም ስትል ታክላለች።  «ዛሬ አንድ ብር ትርፍ ብትኖረኝ። ነገ ሁለት ብር ባገኝ ከዛሬው ጋር ተደምሮ ሶስት ብር ይሆንልኛል ማለት ነው።»

በመለስ ዜናዊ አመራር አካዳሚ የPHD እና የማስተርስ ተማሪዎች የኢኮኖሚክስ ትምህርት መምህር የሆኑት ዶክተር ወንድአፈራሁ ሙሉጌታ  ግን ከገቢያችን የተወሰነዉን መድበን በቋሚነት መቆጠብ ይኖርብናል ይላሉ። ቁጠባም ከወጣትነት ቢጀመር ጥሩ እንደሚሆን ይመክራሉ። « ወጣቶች በገቢያቸው ላይ መመስረት አለባቸው። ቤዚክ የሚባሉት ወጪያቸውን ካወቁ በኋላ፤ ያልተጠበቁት ከ 5 እስከ 10% ቢሆን ሌላ 10 % መቆጠብ መቻል አለባቸው።»

ዶክተር ወንድአፈራሁ እንደሚሉት ለቁጠባ ሚስጥሩ «ቁጠባን መለማመድ» ነው። የምጣኔ ሀብት መምህሩ ከዚህ ባሻገር ወጣቶች እንደምንም ብለው ሼር ቢገዙ ወይም ጠቃሚ የሆኑ እና ወደፊት ጥሩ ገንዘብ ሊያወጡ የሚችሉ እቃዎችን መግዛት ለክፉ ቀን ጠቃሚ መሆናቸውን እንደ ሌላ የቁጠባ አማራጭ ይጠቅሳሉ።

እሳቸውስ የኮሮና ቀውስ ወጣቱን ለችግር ቀን መቆጠብን አስተምሮት ይሆን ይላሉ?

« ወጣቱ ብቻ ሳይሆን እኛም ምን ያህል ጥሬ ገንዘብ ማስቀመጥ አስፈላጊ እንደሆነ የተማርንበት ነው።» ከዚህም በተጨማሪ  ቀውሱ አንዳንድ ሰዎች የገቢ ምንጫቸውን እንዲፈትሹ አድርጓል ይላሉ።«  ለምሳሌ በአርት ስራ ላይ የተሳተፉ እና ብዙም ዝነኛ ያልሆኑ ሰዎች ይህ ቋሚ የገቢ ማግኛ ነው ወይስ ተጨማሪ የገንዘብ ማግኛ ብለው ራሳቸውን መጠየቅ አለባቸው።»

ግለሰቦችን በቁጠባ ተጠቃሚ በማድረግ ሂደት የብድር እና ቁጠባ ተቋማት ሚና ወሳኝ ነበር። እስካሁን በየክልሉ ከስራ ዕድል ፈጠራ እና ከንግዱ ማህበረሰብ ጋር በቅርበት ይሰሩ የነበሩ የብድር እና ቁጠባ ተቋማት ወደ ባንክ ደረጃ እንዲያድጉ መደረጉ ተቋማቱ እመርታ እያሳዩ ስለመሆናቸው ማሳያ ሊሆን ይችላል ።

ልደት አበበ

ነጋሽ መሀመድ

 

 

 

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW