1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ኮንጎ እና አከራካሪው የፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት

ቅዳሜ፣ ጥር 11 2011

በዴሞክራሲያዊት ኮንጎ ሬፓብሊክ ባለፈው ጎርጎሪዮሳዊው ታህሳስ 30፣ 2018 ዓም በተካሄደው ፕሬዚደንታዊ ምርጫ የተቃዋሚው እጩ ፌሊክስ ቺሴኬዲ ማሸነፋቸውን የሀገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን ከጥቂት ቀናት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል። ይህ ውጤት በሀገሪቱ ጠንካራ ንትርክ አስከትሏል።

DR Kongo Verfassungsgericht befasst sich mit Klage von Fayulu
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

ኮንጎ

This browser does not support the audio element.

በዴሞክራሲያዊት ኮንጎ ሬፓብሊክ አስመራጭ ኮሚሽን ዘገባ መሰረት፣ ቺሴኬዲ 38.5 ከመቶ፣ ሌላው የተቃዋሚ እጩ ማርቲን ፋዩሉ 34.8 ከመቶ፣ የገዢው ፓርቲ እና የተሰናባቹ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ ታማን የሆኑት  ኤማኔዌል ራማሳኒ ሻድሪ ደግሞ 23,8 ከመቶ ድምፅ ማግኘታቸው ተገልጿል። ይሁንና፣ ይፋ በሆነው የኮንጎ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ በቺሴኬዲ የተሸነፉት እና ራሳቸውን የምርጫው አሸናፊ አድርገው የተመለከቱት  ፋዩሉ ውጤቱ ተጭበርብሯል በሚልተቃውሟቸውን አሰምተው ፣ የመራጭ ድምፅ እንደገና እንዲቆጠር  ሕገ መንግሥታዊውን ፍርድ ቤት ጠይቀዋል።  ሕገ መንግሥታዊ ፍርድ ቤት በፕሬዚደንታዊው ምርጫ ውጤት ሰበብ የተፈጠረውን ንትርክ  ውሳኔውን ትናንት ይፋ ያደርጋል ተብሎ ነበር። 
ቀደም ሲል በፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት እና በፍርድ ቤቱ ገለልተኝነት ላይ ጥርጣሬ እንዳለው የገለጸው የአፍሪቃ ህብረት በኮንጎ ፕሬዚደንታዊ ምርጫ ውጤት ሰበብ የተፈጠረውን ንትርክ አስመልክቶ በአዲስ አበባ ባለፈው ሀሙስ ባካሄደው ስብሰባ ፍርድ ቤቱ ውሳኔውን ወሌላ ጊዜ እንዲገፋው የህብረቱ ሰላም እና ፀጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሀማት  ጠይቀዋል።
« ምንም እንኳን በኮንጎ ባጠቃላይ ጥሩነቱ የተረጋጋ ሁኔታ ቢታይም፣ አሁንም እጅግ በጣም አሳሳቢ እንደሆነ ነው የሚገኘው። እውነት ለመናገር፣ አስመራጩ ኮሚሽን ይፋ ባደረገው ውጤት ላይ የተፈጠረው ጠንካራ ጥርጣሬ አሁንም አልጠፋም፣ ይህም የኮንጎ ዜጎችን እና በመላ ዓለም የሚገኙ ወንድሞቻቸውን እና ወዳጆቻቸውን ማሳሰቡን ቀጥሏል። »  
ይሁንና፣ የኮንጎ መንግሥት ቃል አቀባይ ላምበርት ሜንዴ  ፍርድ ቤቱ በገለልተኛነት የሚሰራ ነው በሚል ጥያቄውን ውድቅ አድርገውታል።  የአፍሪቃ ህብረት የፊታችን ሰኞ በወቅታዊው የህብረቱ ፕሬዚደንት የርዋንዳ ፕሬዚደንት ፖል ካጋሜ የሚመራ አንድ የልዑካን ቡድን ወደ ኮንጎ መዲና ኪንሻሳ ለመላክ ወስኗል።  ፋኪ ማሀማት የኮንጎ ሁኔታ ውስብስብ መሆኑን በመግለጽ፣ ሰላም ለማስጠበቅ አስፈላጊው ጥረት እንዲደረግ ጥሪ አሰምተዋል።

ምስል Getty Images/AFP/S. Maina
ምስል Getty Images/AFP/T. Karumba

 « ችግሮቹን ለመፍታት  እንዲቻል ውይይት እንዲካሄድ እና ከኃይል ተግባር የራቀ የውጭ ጣልቃ ገብነት ያልታከለበት መንገድ እንዲፈለግ ተማፅኖ አሰምተናል። »
በኮንጎ ሰፊ ተሰሚነት ያለው የካቶሊክ ቤተክርስትያን እንዳስታወቀው፣ ይፋ የወጣው የምርጫ ውጤት ሀቀኛውን ውጤት አያንጸባርቅም፣ ቤልጅየም እና ፈረንሳይን የመሳሰሉ ሀገራት ደግሞ በምርጫው ውጤት ቅር መሰኘታቸውን ገልጸዋል። ይሁንና፣ የኮንጎ ምርጫ አሸናፊን የመለየቱ የመጨረሻ ውሳኔ የሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ተግባር መሆኑን  ስብሰባው ግልጽ ማድረጉን የደቡብ አፍሪቃ የዓለም አቀፍ ጉዳዮች ሚንስትር ሊንዲዌ ሱሱሉ ተናግረዋል። «  ማን አሸነፈ፣ ማን አላሸነፈም አይደለም ጥያቄው። ወሳኙ የምርጫው ሂደት ነው፣ ስለዚህ ጉዳዩን  እና ሁሉም፣ በተለይ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጉዳዩን ለለሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት እንዲተወው እናሳስባለን። »

ይህ የአፍሪቃ ህብረት የሰነዘረው ግልጽ ትችት ብዙዎችን አስገርሟል። የደቡባዊ አፍሪቃ እና የትልቆቹ ወንዞች አካባቢ ሀገራት መሪዎች ባካሄዱት የህብረቱ ስብሰባ የተካፈሉት የኮንጎ ውጭ ጉዳይ ሚንስትር እና ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር ሌዎናር ሸ ኦኪቲንዱ ከአስር ቀናት ገደማ በፊት ይፋ ስለሆነው የምርጫ ውጤት አስተማማኝነት የስብሰባውን ተሳታፊዎች ለማሳመን ሳይችሉ ቀርተዋል። ተሰናባቹ  የሀገሪቱ ፕሬዚደንት ጆሴፍ ካቢላ ያን ያህል ጠንካራ ተቺ አድርገው የማይመለከቷቸው የተቃዋሚ እጩ ፌሊክስ ቺሴኬዲ እንዲያሸንፉ ለማስደረግ ሲሉ የምርጫው ውጤት እንዲጭበረበር አድርገዋል በሚል ይነቀፋሉ።
ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት ለመንግሥት ያደላ እንደሆነ ነው የሚነገረው።  ከአራት ዓመት በፊት አዲሶቹ የፍ/ቤቱ ዳኞች የተሾሙበት ሂደት ገለልተኛ እንዳልሆነ የተቃዋሚው ቡድን፣ ፋዩሉ ጭምር  ማስታወቃቸውን ያኖሽ ኩልንበርግ አስታውሰዋል።
« በ2014 የፍርድ ቤቱ አባላት በፕሬዚደንቱ እና  መንግሥታቸው ነበር የተመረጡት።   በ2018 አንዱ ዳኛ በሞቱበት እና ሌሎች ሁለት ዳኞች ስራቸውን በለቀቁበት ጊዜም   .መንግሥት ተተኪዎቻቸውን ሶስት ዳኞች ሰይሟል። ስለዚህ ይህ ፍርድ ቤት ገለልተኛ ውሳኔ ይደርሳል ተብሎ አይጠበቅም። በአንጻሩ፣ ውሳኔው  ለካቢላ የሚበጅ ፖለቲካዊ ውሳኔ እንደሚሆን ነው የሚገመተው። »

ምስል picture-alliance/AP Photo/P Photo/J. Bompengo

ፋዩሉየ ራሳቸው የሕገ መንግሥታዊውን ፍርድ ቤት ገለልተኝነት ቢጠራጠሩትም፣   በውጤቱ አንጻር በሀገሪቱ ባለው ሕጋዊ መንገድ በመጠቀም ክስ ከማቅረብ ሌላ አማራጭ እንደሌላቸው ነው ያኖሽ ኩልንበርግ የገለጹት። ሕገ መንግሥታዊው ፍርድ ቤት  የፋዩሉን ክስ ውድቅ ካደረገ፣ ኩልንበርግ እንደሚገምቱት፣ በሀገሪቱ ላይ ግፊት ሊያርፍ የሚቻልበትን መንገድ ማፈላለጋቸው አይይቀርም።
« የፋዩሉ ደጋፊዎች  ሞይሴ ካቱምቢ እና ዦን ፒየር ቤምባ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ እነሱ ትክክለኛ አይደለም በሚሉት የፍርድ ቤት ውሳኔ አንጻር በኮንጎ  መንግሥት ላይ ጫና እንዲያሳርፍ መጣራቸው እንደማይቀር የታወቀ ነው። ይሁንና፣ አሁን ባለው ሁኔታ፣ በአውሮጳ ህብረትም ውስጥ ሆነ፣ በአፍሪቃ ህብረት ወይም በደቡባዊ አፍሪቃ መንግሥታት የልማት ድርጅት፣ ሳዴክ ውስጥ በኮንጎ መንግሥት ላይ አስፈላጊውን ጫና ማሳረፍ የሚያስችል አብላጫ ድምፅ መገኘቱ አጠራጣሪ ነው። » 
 በዚህም የተነሳ ለኮንጎ ውዝግብ በቅርቡ መፍትሔ መገኘቱ የማይጠበቅ ነው ብለው እንደሚያስቡ ኩልንበርግ ገልጸዋል።
« ካቢላ በወቅቱ የሚፈልጉትን ማስደረግ የሚሳካላቸው ይመስለኛል። በርግጥ፣ ግልጽ ዓላማ አላቸው። ይሁንና፣ ይህን ዓላማቸውን እንዴት ከግብ እንደሚያደርሱት ተጨባጭ ስልት የላቸውም። »

ምስል Reuters/B. Ratner

አርያም ተክሌ

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW