1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ ከ 50 በላይ ሰዎች ተገደሉ

ሰኞ፣ ኅዳር 12 2015

ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ በተፈጠረ ግጭት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተነገረ። ለግጭቱ በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የክልሉን ልዩ ኃይልና ኦነግ ሸኔ የተባለውን ታጣቂ ተጠያቂ ሲያደርጉ፣ የኦሮሞ ተወላጆች ደግሞ “ፋኖ” የተባለውን ታጣቂ ይከስሳሉ፣ ውጊያ ኪራሙ ዙሪያ ዛሬም መቀጠሉን ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት፡፡

Äthiopien Straße in Nekemt

ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ ከ 50 በላይ ሰዎች ተገደሉ

This browser does not support the audio element.

ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪራሙ ወረዳ በተፈጠረ ግጭት ከ50 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ ። ለግጭቱ በአካባቢው የሚኖሩ የአማራ ተወላጆች የክልሉን ልዩ ኃይልና ኦነግ ሸኔ የተባለውን ታጣቂ ተጠያቂ ሲያደርጉ፣ የኦሮሞ ተወላጆች ደግሞ “ፋኖ” የተባለውን ታጣቂ ይከስሳሉ፣ ውጊያ ኪራሙ ዙሪያ ዛሬም መቀጠሉን ነው ነዋሪዎቹ የሚናገሩት፡፡
ከሦስት ቀን በፊት ምስራቅ ወለጋ ኪራሙ ከተማ ውስጥ ተጀመረ የተባለው ግጭት የተለያየ መነሻ እንዳለው ነዋሪዎቹ ይናገራሉ፣ አንዳንዶቹ ከእንስሳት ሰርቆት ጋር የተያያዘ ነው ሲሉ ሌሎች ደግሞ እስረኛ ለማስፈታት በተፈጠረ ግርግር እንደተነሳ ያመለክታሉ፡፡
ያም ሆነ ይህ በከተማዋ የሚኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች መንግስት ኦነግ ብሎ የሚጠራውና የክልሉ ልዩ ኃይል በንፁሐን ላይ ጥቃት ከፍተው ብዙዎች እንዲሞቱና እንዲፈናቀሉ ምክንያት ሆነዋል ብለዋል፡፡
“ሸኔና ልዩ ኃይል ተቀላቅሎ ንፁሐን ህዝብ እየጨረሰ ነው ያለው፣ ንብረትም እንዳለ ተዘርፎ ወድሟል፣ ምንም የለም ቤትም እያቃጠሉ ነው፣ ህዝቡም በርግጎ ጫካ ገብቷል፣ ንፁሐንም እለቀ፣ እየሞተ ነው ያለው፣ እኛም ተፈናቅለን ነው ያለነው ወደ ጫካ ወደ በረሀ፣ ደካሞች አሉ፣ ህፃናት አሉ እርጉዞች አሉ፡፡ መጀመሪያ ገበሬውና ኦነጉ ጋር ነበር አሁን፣ ልዩ ኃይል አስጠርተው አጋጠሙት፣ ሬሳም አልተነሳ፣ አሁን ግን ህዝቡ ሬሳ ወድቆ አንቀመጥም ብሎ እየገጠመ ነው፡፡”
ሌላ የኦሮሞ ብሔር ተወላጅ የሆኑ እናት በበኩላቸው ባለፈው ማክሰኛ የሶስት ልጆች አባት ወንድማቸው በፋኖና በአማራ ልዩ ኃይል እንደተገደለባቸው አመልክተዋል፡፡ “ያው የቤተሰብ አስተዳዳሪ ነው የሶስት ልጆች አባት ነው፣ ጃርቴ አልቦ ከተማ ነው የሚኖረው፣ ማክሰኞ እለት በተፈጠረ ሁኔታ ፋኖና የአማራ ልዩ ኃይል ነን በሚሉት ነው የተገደለ ነው የተባለው፣ ምክንያቱን አናውቅም ገኙትን ጨፍጭፈው ገድለው ቤት ተቃጥሎ ነው ያለው፣ እዚያ የሚኖር አሁን የለም ተፈናቅሏል፡፡”
የአማራ ልዩ ኃይልና ፋኖ የተባሉ ታጣቂዎች በአካባቢው በእርግጥ በኦሮሞዎች ላይ ጥቃት ያደርሳሉ ወይ? ኦሮሞዎችን የሚያፈናቅልስ ማነው? ተብለው የተጠየቁት አንድ ነዋሪ፣ ለችግሮች ሁሉ መነሻ ኦነግ መሆኑንና ፋኖ የሚባል በአካባቢው አይታወቅም ብለዋል፡፡ “ፋኖ የሚባል ነገር የት አለ? ተደራጅቶ ቦታውን የሚጠብቅ እንጂ አማራ ስለሆነ ፋኖ ይሉታል እንጂ ከየት የመጣ ፋኖ አለ? ቀየውን ለመጠበቅ የተደራጀውን ወጣት የሚፈርጁት፡፡” ካለፈው ሶስት ቀን ጀምሮ በተፈጠረው ግጭት በኪራሙ ከተማ 52 ንፁሐን ሰዎች በእርግጥ በታጣቂዎች መገደላቸውንና ገና ያልተገኙ በየጫካው እንዳሉ አንድ እማኝ ተናግረዋል ፡፡
“ትናንትና ዙሪያውን ከብቦ ከተማ ውስጥ ለ ሰው እንዳይወጣ ሲመታ ዋለ፣ አስከሬን ይውጣ እዛ ያለው ቤተሰብ በህይወት ካለ እናውጣ ብለን በአካባቢው ላለው ልዩ ኃይል አዛዥ ሲደወል ምንም ችግር የለባቸውም፣ አሉ፣ አለን፣ በቁጥጥር ስር ውለዋል የተባሉ ሰዎች ግን ሞተዋል፣ የምትገደለውና የምትመታ ንፁሐን ሴት ወንድ፣ ተንኮለኛ ካለ ተንኮለኛውን እየፈለጉ መሄድ ስፈልጋል፣ ይህ ግን እተደረገ አይደለም፣ በየጫካው ያደረ አሁንም ያልተገኘ ሰው አለ፣ ቁርጡ የታወቀ ወደ 52 ሰው ነው የሞተው፡፡”
አስከሬን ለማውጣት ወደ ኪራሙ በተንቀሳቀሱ ወጣቶችና በኦሮሚያ ልዩ ኃይል መካከል ዛሬም ከፍተኛ ውጊያ እንዳለ አስተያየት ሰጪዎቹ አስረድተዋል፡፡ የአማራ ተወላጆች ወደ አማራ ክልል ለመፈናቀል ሃሳብ ቢኖረንም አካባቢያችን በመከበቡ አባይን መሻገር አልቻልንም ሲሉ ገልጠዋል፡፡ “የአማራ ክልል ባይሆን መንገድ ከፍቶ ቢቀበለን ምን ችግር አለ? ህዝብ እየሞተ እየተጨፈጨፈ ነው ያለው፣ መንገድ ባይዘጋብን ህፃናት፣ ሴቶች ቢወጡ ምን ችግር አለ?”
አብዛኛዎቹ የአማራ ተወላጅ የሆኑ ከ60 ሺህ በላይ ሰዎች ሃሮ ወደተባለ ቦታ ሲፈናቀሉ፣ የኦሮሞ ተወላጆች ደግሞ ጊዳ ወደ ተባለ አካባቢ ተፈናቅለዋል ብለዋል፡፡ ነዋሪዎቹ ችግሩ ተባብሶ ወደ ህዝብ ለህዝብ ግጭት ከመግባቱ በፊት መንግስት የመከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው እንዲሰማራ ጠይቀወዋል፡፡ ስለጉዳዩ አስተያየት ለመጠየቅ የኪራሙ ወረዳ አስተዳደርን፣ የአማራ ብልፅግና ፓርቲንና የአማራ ብሔራዊ ንቅናቂ አመራሮችን ለማግኘት ያደረግሁት ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም፡፡
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በወለጋ ዞኖች የሚኖሩ ሰዎች በታጣቂዎች በሚደርስባቸው ጥቃት ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ለመፈናቀል እየተዳረጉ ነው፡፡


ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ 
ነጋሽ መሐመድ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW