ወልቂጤን ጨምሮ በጉራጌ ዞን ከተሞች የሥራ ማቆም አድማ
ሰኞ፣ ጥር 29 2015በደቡብ ክልል በሚገኘው ጉራጌ ዞን ዋና ከተማ ወልቂጤን ጨምሮ በተለያዩ አካባቢዎች በዛሬው እለት ለአንድ ቀን የሚቆይ የስራ ማቆምና ከቤት ያለመውጣት አድማ እየተደረገ መሆኑን ዶቼ ቬሌ ያነጋገራቸው የዞኑ ነዋሪዎች ተናገሩ።
ዛሬ ማለዳ የጀመረው የስራ ማቆም አድማ ለአንድ ቀን ብቻ እንደሚቆይ የተናገሩት የአድማው አስተባባሪ እና የወልቂጤ ከተማ ነዋሪ የሆኑት አቶ አንድነት አንዱሎ የአድማው የተደረገበትን ምክንያት ዛሬ በደቡብ ክልል የሚከናወነው ህዝበ ውሳኔ ዛሬ ወደ ወላይታ ጋሞ ምርጫ እያደረጉ ነው ጉራጌ ግን በሙሉ ድምፁ ያፀደቀው እና በምክር ቤቱ የወሰነው ውሳኔ በግድና በጉልበት ማእከላዊ ኢትዮጵያ ተብለህ ተሰየም በመባላችን ነው ይላሉ ። «ህዝቡ ተቃውሞውን በሰላማዊ መንገድ ቤት ውስጥ በመቀመጥ አድማ እያደረገ ነው» ብለዋል።
ለአራተኛ ግዜ የሚደረገውን የስራ ማቆም እና ቤት ውስጥ የመቀመጥ አድማን አስተባብራችዋል ቅስቀሳ አድርጋችዋል የተባሉ ወጣቶች በመንግስት አካላት ድብደባ እና እስራት እየደረሰብን ያሉት አቶ አንድነት
«ህዝቡን ስለመብቱ ሲያነቁ እና ሲያስተባብሩ የነበሩ ወጣቶችን ትላንት የመንንግስት አካላት አስረዋቸዋል። መንግስት አሁን ላይ ምላሽ እየሰጠን ያለው በእስራት ነው ብለዋል
ሌላኛው ለዶቼ ቬሌ አስተያየታቸውን የሰጡት የጉራጌ ዞን ነዋሪ የሆኑት ሰንብት መስሩ እሳቸው ባሉበት አካባቢ ከጤና ተቋም በስተቀር ሁሉም ዝግ እንደሆኑ ተናግረዋል። ማህበረሰቡ ጋር ተቀባይነት ያላቸውን እንዲሁም ማህበረሰቡን የሚያነቁ ሰዎች በተለይ ወጣቶች ከትላንት ጀምሮ በመንግስት የፀጥታ አካላት እየታሰሩ እንደሆነ ና እሳቸው በሚኖሩበት አካባቢ ከጤና ተቋም ውጪ ሁሉም ነገር ዝግ መሆኑን ተናግረዋል «የመንግስት የፀጥታ አካላት ዛቻና ማስፈራሪያ ከማድረግ ውጪ እስራት እየፈፀመ ነው» ብለዋል
ከዚህ በፊት በጉራጌ ዞን የሚገኙ አምስት የወረዳ ምክር ቤቶች አሁን ያለውን የደቡብ ክልል ለሁለት የሚከፍለው የክላስተር አደረጃጀት «ገቢራዊ ይሁንልን» ሲሉ ለአገሪቱ የፌዴሬሽን ም/ቤት መጠየቃቸው ይታወሳል።
ለጉራጌ ዞን ኮሙኒኬሽን ኃላፊዎች ለአንድ ቀን በሚቆየው የሥራ ማቆም አድማ እና ታሰሩ ስለተባሉት የማህበረሰቡ ክፍሎች ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ስልክ ብንደውልም ስልክ ባለማንሳታቸው ሀሳባቸውን ልናካትት አልቻልንም።
ትላንት ጥር 28 ቀን 2015 ዓ.ም የጉራጌ ዞን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ በሰጠዉ መግለጫ «ጥር 29 ህዝበ ዉሳኔ ከእኛ ዞን ጋር የሚያገናኘው ምንም ነገር የለም» ብሎ ነበር።
የዞኑ የኮሙኒኬሽን መምሪያ በማኅበራዊ ድረ ገጾች ባሰራጨው መግለጫ «ቀኑን ክልል ወይም ዞን እንዲሁም ልዩ ወረዳ የሚመሰረትበት ቀን በማስመሰል ፀረ ሰላም ሀይሎች አመፅ ለመቀስቀስ በማህበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ እያደረጉ ይገኛል» በማለት በስም ያልጠቀሳቸውን ወገኖች ከሷል።
«የዞኑን ህዝብ ሰላም ለማደፍረስ፣የመማር ማስተማር ሂደትን ለማስተጓጎል፣ ህዝቡ የዕለት ኑሮዎን ለማሸነፍ የሚደረጉ የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎች ለማደናቀፍ» ይሞክራሉ ላላቸው አካላት «ነውጠኛ» ካለው ተግባር እንዲታቀቡ ማስጠንቀቂያ ሰጥቶ ነበር።
የዞኑ አስተዳደር «የህዝብን ሰላም ለማደፍረስ የሚንቀሳቀሱ ህገወጥ ቡድኖች ላይ መንግስት ጠንካራ ህጋዊ እርምጃ ለመውሰድ በቂ ዝግጅት» ማድረጉንም የጉራጌ ዞን ኮሙኒኬሽን መምሪያ ገልጿል።
ማህሌት ፋሲል
እሸቴ በቀለ