ወልቃይት ጠገዴ አካባቢ ውጊያ ነበር ተባለ
ረቡዕ፣ ነሐሴ 25 2014
ኢትዮጵያ እና ሱዳን በሚዋሰኑበት የወልቃይት ጠገዴ አካባቢ በኢትዮጵያ መንግሥት እና በሕወሓት ታጣቂዎች መካከል ዛሬ ንጋት ላይ ውጊያ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎች ለዶይቸ ቬለ (DW)ተናገሩ። የኢትዮጵያ መንግሥት ኮሙኒኬሽን አገልግሎት ዛሬ በይፋ የትዊተር ገጹ ባወጣው መግለጫ ደግሞ፦ «ያለ ጦርነት መኖር የማይችለው» ያለው ሕወሓት «በዋግ፣ በወልቃይት አቅጣጫና በሱዳን ድንበር አካባቢ ወረራ ከፍቷል» ብሏል። «ይህን የሕወሓት ወረራ ጀግናው የመከላከያ ሠራዊት በተሟላ ዝግጅትና በጽኑ ቁመና እየተከላከለ ይገኛል» ሲልም አክሏል።» የሕወሓት ቃል አቀባይ ጌታቸው ረዳ በበኩላቸው፦ «ዛሬ ጠዋት ሰቆጣ፣ ሐምድያት እና ደደቢትን ጨምሮ በተለያዩ ግንባሮች በኩል» በሕወሓት ታጣቂዎች ተኩስ ተከፍቷል መባሉን በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው አስተባብለዋል። «መንግሥት ከዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዕይታ ውጪ ለመሆን የፈጠራ ታሪክ እየሠራ ነው» ሲሉም አክለዋል። ዶይቸቬለ ዛሬ ከቀትር በኋላ ያነጋገራቸው አንድ የሁመራ ከተማ ነዋሪ ግን ሁመራ ከተማ «ሰላም ነዉ» ብለዋል።
«ሁመራ ከተማ በጣም ሰላም ነው አሁን። ምንም አይነት ችግር የለም። ሰላማዊ እንቅስቃሴው እንደቀጠለ ነው። እነሱ ትንኮሳ ያደረጉት በዚህ በበረከት በኩል በሱዳን በኩል፤ ሱዳንን እና ኢትዮጵያን በሚያዋስነው በኩል ባለው ቦታ ነው። ከተማ ውስጥ ምንም ችግር የለም። ሰላማዊ እንቅስቃሴ እንደቀጠለ ነው፤ ሕዝቡም ደጀንነቱን እንዳስመሰከረ ነው።»
ኢትዩጵያ እና ሱዳን በሚዋስኑባት በወልቃይት ጠገዴ በረከት አካባቢ «ሸረሪና» የሚባል ቦታ ላይ ውጊያው ጠዋት ላይ ሲደረግ እንደነበር እና አሁን ግን ምንም አይነት ድምፅ እንደማይሰማ በግብርና የሚተዳደሩ ሌላ የሁመራ ነዋሪ ለዶይቸ ቬለ ገልጠዋል።
«ሕወሓት በዚህ በረከት የሚባል አካባቢ አለ ወደ ሱዳን ድንበር። እዚያ አካባቢ እና ደግሞ በእዚህ በተከዜ ደግሞ ወደ ሽሬ መስመር ባለው ማታ ጀምረው ማጥቃት እንደጀመሩ እና ወረራ እንደፈጸሙ ነው የሰማሁት።»
የኢትዮጵያ መንግስትና የሕወሓት ኃይላት ለአምስት ወራት ግድም የቆየውን ተኩስ አቁም አፍርሰዉ አማራ ክልል ቆቦ አካባቢ አዲስ ውጊያ ከጀመሩ ዛሬ ሳምንት ሆኗቸዋል።
ማንተጋፍቶት ስለሺ
ነጋሽ መሐመድ