1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ወሎ፤ መጠለያ ጣብያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ድምፅ ሊሰጡ ነዉ

ኢሳያስ ገላው
ሰኞ፣ ሰኔ 1 2018

በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ድምፅ ያልሰጡ በሰሜንና ደቡብ ወሎ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ነገ ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉበት ሆነው በልዩ ሁኔታ ድምፅ ሊሰጡ ነው። ተፈናቃዮቹ መምረጥ በመቻላቸው መብታቸው መከበሩ ቢያስደስታቸውም፣ ስለሚመርጧቸው እጩዎችና ፓርቲዎች በቂ ግንዛቤ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል።

ፎቶ ከማኅደር - በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች
ፎቶ ከማኅደር - በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

ወሎ፤ መጠለያ ጣብያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ድምፅ ሊሰጡ ነዉ

This browser does not support the audio element.

ወሎ፤ መጠለያ ጣብያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ድምፅ ሊሰጡ ነዉ

በ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ  ድምፅ ያልሰጡ በሰሜንና ደቡብ ወሎ መጠለያ ጣቢያዎች የሚገኙ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች፣ ነገ ሰኔ 2 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉበት ሆነው በልዩ ሁኔታ ድምፅ ሊሰጡ ነው። ተፈናቃዮቹ መምረጥ በመቻላቸው መብታቸው መከበሩ ቢያስደስታቸውም፣ ስለሚመርጧቸው እጩዎችና ፓርቲዎች በቂ ግንዛቤ እንዳልተሰጣቸው ገልጸዋል።

በሰባተኛው ሀገርአቀፍ ምርጫ በልዩ ሁኔታ ድምፅ የሚሰጡ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ሰኔ 2/2018  ዓመተ ምህረት ባሉበት መጠለያ ጣቢያ ድምፅ ይሰጣሉ። በሰሜን እና ደቡብ ወሎ በአምስት የመጠለያ ጣቢያ እና ዘጠኝ የምርጫ ጣቢያዎች ድምፅ ይሰጣል። በስድስተኛው ሀገርአቀፍ ምርጫ በአካባቢው በነበረው የፀጥታ ችግር ምክንያት በምርጫ መሳተፍ ያልቻለው በሰሜን ወሎ ጃራ መጠለያ የሚኖረው አህመድ ሰይድም እንደ ዜጋ መብታችን መከበሩ አስደስቶኛል ይላል።

"ያው ምርጫ መምረጥ በመቻላችን አንደኛ እንደ ኢትዮጵያ ህዝብ ተፈናቃይም ብንሆን ወገኖቻችን ኢትዮጵያዊ ናቸው፤ በኢትዮጵያዊነታቸው በዜግነታቸው መብታቸው መከበር አለበት ብሎ መንግስት ይህንን ስላመቻቸልን ያው ደስ ብሎናል። እኛ ወለጋ እያለንም ከዚህ በፊት ምስራቅ ወለጋ ኪረሙ ነበርኩኝ፤ ምርጫ አልመረጥንም ነበር።  የስድስተኛው ዙር ምርጫ አላካሄድንም ነበረ። አካባቢ በጸጥታው ችግር ምርጫ አልነበረም። አሁን ግን እዚህ ሰባተኛውን ዙር ምርጫ ለመምረጥ በመዘጋጀቴ በጣም ደስተኛ ነኝ።"

ድምፅ በሚሰጥባቸው የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ መካከል በደሴ ዙሪያ ወረዳ ገራዶ የመጠለያ ጣቢያ አንዱ ሲሆን በመጠለያ ጣቢያው ነዋሪ የሆነው ይመራ አሊም ስለምንመርጠው ፓርቲ ሰፊ ግንዛቤ ባይኖረንም መምረጣችን ግን መልካም ነው ሲል ይናገራል። "በመምረጣችን  ምን አወቅን ብለን ግንዛቤ አልተሰጠንም የምንመርጠውን አላወቅነውም፤  ዞሮ ዞሮ ግን በነጻነታችን መታወቁን ብቻ ደስተኛ ነኝ። ያው ቅድም እንደነገርኩህ ቅድም አንተ ስትደውልልኝ ወዲያው ነው የደወለልኝ ለነገ ተብላችኋል ተባል።"

ምርጫ ሂደቱ እስካሁን ባለው አስገዳጅ ነገር የለም የምትለው አለሚቱ በሉሁ፤ ለምን የማንኖርበትን አካባቢ ተወካይ እንመርጣለን የሚል ጥያቄ ቢኖረንም፤ አሁን ላይ ግን መግባባት ላይ ደርሰናል ትላለች። "ያው እንግዲህ እንመርጣለን ልንመርጥ ነው፤  ደስተኛ ነኝ ሁሉም ሰው ተሳታፊ ሊሆን እንዲሆን ንቁ ተሳትፎ እንዳለው ነው እኛ የምናውቀው። መብትና ግዴታችን ያው አውቀን እንመርጣለን። ያው እንግዲህ እኛ የምንመርጠው እገሌ እገሌን ምረጡ እገሌን አልተባልንም። እራሳችን ነው የምንመርጠው ማለት ነው። እንደ ወረፋ ሆነን ነው የምንመርጠው ያው ግንዛቤ ተሰጥቶታል ህዝቡ ለምን የሚል ጥያቄ መጥቶ ነበረ ያው ። ወደ ቀያችን እንኳን ብንመለስ እንኳን በመረጥነው መንግስት መተዳደር አለብን። ባልመረጥነው መንግስት ለምን እንተዳደራለን የሚል ነው ።" 

ፎቶ ከማኅደር - በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች ምስል፦ Alemnew Mekonen/DW

ምርጫ በማይካሄድበት በተውለደሬ ወረዳ ጃሪ ቁጥር አንድ መጠለያ ጣቢያ ነዋሪ የሆነው አስተያየት ሰጪም በምርጫ አለመሳተፋችን እንደተገለልን እራሳችን እንድንቆጥር አድርጎናል ሲል ይገልጻል። "ባለመምረጣችን ገለልተኝነት ነው የሚሰማንም ምንም እኛን ስላገለሉን የሆነ በቃ፤ ኢትዮጵያዊነትህን ትረሳለህ በቃ ለምን ህገ መንግስቱ ላይ አውቆህ ለ IDP ለወታደር ካምፖች ለተለያዩ ህጉን አጽድቆ አውጥቷል። ከላይ እንዳይመረጥ ማድረግ ይሄ በጣም በቃ ህሊናህን ይጎዳሃል፤  እንደ ሀገር አይሰማህም ዜግነት እንደ ዜግነት አይሰማህም። ጥሩም የሚሆን መጥፎም የሚሆን እንደ ሀገር አብረህ ሀገርህ ሲጎዳ አብረህ መጎዳት ሀገርህ ሲጠቀም፤ አብረህ መጠቀም የሀገር ፍቅር የወገን ፍቅር ይጨምራል ግን ይሄ በገለልተኝነት ሲታይ ባይተዋርነት ያሰማሃል።" 

በጃራ የመጠለያ ጣቢያ ምርጫ አስፈጻሚ የሆነው ሀብታሙ አበራም የምርጫ ቁሳቁስ መድረሱንና ለነገው ምርጫ ዝግጁ መሆናቸውን ይናገራል። "ነገ ይካሄዳል ቁሳቁስም ተረክበን ያው ለነገ ምርጫ ዝግጅት እያደረግን ነው። ካርድ አዉጥተዋል። አራት የምርጫ ጣቢያ አለ። ቁሳቁስ ትናንትና ተረክበናል። እስካሁን የተለየ ነገር ያየነው ነገር የለም አካባቢ ሰላም ነው። አይ እዛ የነበሩበትን ነው የወለጋውን ወይም ደግሞ ቅድም ከተፈናቀሉበት የምርጫ ክልል ነው ያንን ነው የሚመርጡት። በብዛት ምስራቅ ወለጋ ከዛ ደግሞ ቤንሻንጉልም አለ ግን ፤ ምስራቅም ምዕራብ ወለጋም አለ። ሆሮ ጉዱሩ ከዛም ያው በቃ ኦልሞስት ምስራቅ ወለጋ አለ ምዕራብ ወለጋ ከዛ ደግሞ ሆሮ ጉዱሩ ማለት ነው ሻምቡ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ።" 

ፎቶ ከማኅደር - በአማራ ክልል የሚገኙ ተፈናቃዮች ምስል፦ Alemnew Mekonnen/DW

ነገ በልዩ ሁኔታ ባሉበት መጠለያ ጣቢያ ድምፅ የሚሰጡት የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ስለሚመርጡት ፓርቲ በቂ ግንዛቤ እንደሌላቸውም ገልጸዋል። "እዚያ ገለጻ አልተደረገልንም እንግዲህ ምንም ያው ወለጋ ያለን እጩ ነው የምትመርጡት ብቻ ነው የተባልን እንጂ ከመጣህበት የምርጫ ክልል ወለጋ ስኩሎ የተዘጋጀውን እጩ ነው የምትመርጥ ነው፤ የተባልነው እንግዲህ የእገሌ የእገሌ ነው ተብሎ እስካሁን የተነገረን ነገር የለም።" በሰሜን እና ደቡብ ወሎ በገራዶ፣ መካነ ኢየሱስ፣ ኩታበር ቻይና ካምፕ፣ ጉባላፍቶ ግብርና ካምፕ፣ ቦረና እና ጃራ የስደተኞች መጠለያ ነገ ምርጫ ይከናወናል።

ኢሳያስ ገላዉ

አዜብ ታደሰ

ፀሐይ ጫኔ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW