1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ወሎ "የደረሰበትን ልቁጠር ብል በአገሬ ሰው የቀለድኩ ይመስለኛል" ከመርሳ የተፈናቀሉ ነጋዴ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 11 2014

ከትግራይ ኃይሎች ውጊያ በሚደረግባቸው የአማራ ክልል አካባቢዎች ነጋዴዎች ሥራቸው ተስተጓጉሎ በሥጋት ውስጥ ይገኛሉ። መሠረታዊ የአገልግሎት ተቋማት በቅጡ እየሰሩ አይደለም። የወሎ ገበሬ እና ማሳ የገባበት ቅርቃርም ለብዙዎች ሥጋት ሆኗል። ወሎ "የደረሰበትን ልቁጠር ብል በአገሬ ሰው የቀለድኩ ይመስለኛል" ሲሉ ከመርሳ የተፈናቀሉ ነጋዴ ተናግረዋል

Karte Äthiopien Amhara ETH

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ወሎ እና የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ዳፋ

This browser does not support the audio element.

በሐይቅ ከተማ የሚገኙት የሸቀጣ ሸቀጥ ነጋዴ ቤተሰቦቻቸውን "ከሥጋት ቀጠና ለማራቅ" ወደ ደሴ ልከው፤ መደብራቸውን ዘግተው የሚመጣውን ይጠባበቃሉ። "ቢመጡም ሮጬ ማምለጥ እችላለሁ" የሚል እምነት ያላቸው ነጋዴ ለደሕንነታቸው በመስጋት ማንነታቸውን መግለፅ አይፈልጉም። "እኔ ከዛሬ [ማክሰኞ] ጀምሮ ዘግቺያለሁ። ቤቴ ነው ያለሁት። ግርግር ስለሚኖር ቢመጡብኝ የሚል ሥጋት አለ። ያ ስላለ ዘግቼ አሁን ቤቴ ነው ያለሁት" ሲሉ የሐይቁ ነጋዴ የንግድ ሥራቸውን እንዳቆሙ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል።

ከአዲስ አበባ 430 ኪሎ ሜትር ገደማ ርቃ በደቡብ ወሎ ዞን ተሑለደሬ ወረዳ የምትገኘው ትንሺቱ የሐይቅ ከተማ በአቅራቢያዋ የሚካሔደው ውጊያ ትኩሳት ይሰማት ከያዘ ሰነባብቷል። የሐይቁ ነጋዴ "በመድፍ፣ በዲሽቃ ኃይለኛ ውጊያ አለ። ድምጹ ራሱ በጣም ይሰማል። ከዚህ ከሐይቅም ይተኮሳል። ይኸው አሁንም እየተተኮሰ ነው" ሲሉ የጦርነቱን ድባብ ያስረዳሉ።

ነጋዴዎች እና የመንግሥት ሰራተኞችን ጨምሮ ወደ ደሴ እና በአካባቢው ወደሚገኙ ከተሞች የሸሹ የሐይቅ ነዋሪዎች ጥቂት አይደሉም። የከተማዋ ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት ትናንት ማክሰኞ በሐይቅ ከተማ ባንኮች አገልግሎት አልሰጡም። ምግብ ቤቶች ተዘግተዋል። የአካባቢው ነዋሪዎች ሎጎ እያሉ ከሚጠሩት እና 23 ኪሎ ሜትር ስኩዌር ከሚሸፍነው ሐይቅ አጠገብ የምትገኘው ከተማ እንቅስቃሴዋ እንደወትሮው አይደለም።  

የሐይቁ ነጋዴ "አሁን ባለው ጊዜ ያለውን ሽጠን ብሩን መያዝ ነው እንጂ ዕቃ መልሰን አናመጣም። ከመጡ ይዘርፉናል በሚል ሥጋት እንዲያውም ከሱቅ ዕቃዎችን ወደ ሌላ ቦታ አሽሽተናል" ሲሉ የንግድ ሥራቸው የሚገኝበትን ሁኔታ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ፌድራል መንግሥት እና የአማራ ክልል የጸጥታ አስከባሪዎች ከትግራይ ኃይሎች የሚያደርጉት እና ከሰሜን ወደ ደቡብ የሚንደረደረው ውጊያ ተጽዕኖ ያሳደረው ግን በንግድ ሥራዎች ላይ ብቻ አይደለም። በከተማው የመድሐኒት መደብሮች ዝግ ናቸው። የጤና ተቋማትም በቅጡ ግልጋሎት እየሰጡ አይደሉም።

"ትናንትና የአጎቴ ሚስት እርጉዝ ሆና ጤና ጣቢያ ሔደው `አይ እኛ ሥጋት ስላለብን አንሰራም´ ብለው መልሰውታል። ከዚያ ሚስቱ ደሴ ሔዳ ነው የወለደችው" በማለት በቅርብ ቤተሰባቸው ላይ የደረሰ ያሉትን በሐይቅ የሚገኙት እና ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁት ነጋዴ አስረድተዋል።  

ከአዲስ አበባ እስከ መቐለ የተዘረጋው አውራጎዳና ከሚያቋርጣቸው ከተሞች አንዷ በሆነችው መርሳ ነዋሪ የነበሩት አቶ ሰይድ ሙሐመድ ወደ ደሴ ከመሸሻቸው በፊት የሕፃናት ልብስ በከተማዋ ይነግዱ ነበር። የከተማው ወጣቶች የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ እና የጀርመን ቡንደስሊጋ የመሳሰሉ የእግር ኳስ ጨዋታዎችን የሚመለከቱበት፤ ፑል የሚጫወቱበት መዝናኛ በዚያው በመርሳ አቶ ሰይድ ነበራቸው።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ውጊያ አንድ አመት ሊሞላው ሁለት ሳምንታት  ገደማ ቀርቶታል።ምስል Stringer/File/REUTERS

ከሶስት ወራት ገደማ በፊት የመርሳ ከተማ በትግራይ ኃይሎች እጅ ለመውደቅ ስትቃረብ ልጆቻቸውን ይዘው ወደ ደሴ የሸሹት አቶ ሰይድ "የሕጻናት ልብስ መሸጫ እና ቡቲክ፤ ኳስ ቤት ነበረ። ቴሌቭዥን እና ፕሮጀክተር ነበረ። ጄኔሬተር እና ስፒከር ነበር። እንደተዘረፈ ነው የተነገረኝ። እዚያው [መርሳ] የቀሩ ሰዎች ነበሩ፤ አሁን በቅርብ የመጡ። እነሱ ታጣቂዎቹ በተለይ ሱቁን ቤታቸው እንዳደረጉት ነው የተነገረኝ" ብለዋል።

ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም. የተቀሰቀሰው ውጊያ አንድ አመት ሊሞላው ሁለት ሳምንታት  ገደማ ቀርቶታል። ጦርነቱ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ብርቱ ሰብዓዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ቀውስ ፈጥሯል። እስካሁን ተዋጊዎቹ መቋጫ ሊያበጁለት፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚያደርገው ጫናም ማስቆም ተስኖት ሕይወታቸውን የሚያጡ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ከለት ወደ ዕለት እየጨመረ፣ ሰብዓዊ ቀውሱ እየበረታ ሲሔድ ይታያል። ከመርሳ የተፈናቀሉት አቶ ሰይድ ጦርነቱ "በአጭር ጊዜ ካልተቀጨ" የወሎ መጻኢ እጣ ፈንታ "የጨለመ" ሆኖ ይታያቸዋል።

አቶ መሐመድ ሰይድ የተባሉ ሌላ የመርሳ ነዋሪ ከተማዋ በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ በተሰማቸው የደሕንነት ሥጋት ወደ ደሴ መሸሻቸውን ለዶይቼ ቬለተናግረዋል።  

"እዚያ ባለንበት ሰዓት አንዳንድ ጋጠወጦች ቢኖሩም ደህና ነበረ። ኮማንዶ ገብቶ ከወጣ በኋላ ነው ትንሽ አስቸጋሪ የሆነው። አንዳንድ ወጣቶችም የተገደሉት ከዚያ በኋላ ነው" የሚሉት አቶ መሐመድ በመርሳ "ከተማ አሁን ምንም አይነት ሱቅ፤ ምንም አይነት [አገልግሎት] የለም። ተዘርፏል፣ የተቃጠለም አለ" ሲሉ ይናገራሉ።  

"ከተማዋ ወድማለች። ለምሳሌ አልፎ አልፎ የተቃጠሉ ቤቶች አሉ። ከባድ መሳሪያ ያረፈባቸውም ቤቶች አሉ። ከባድ መሳሪያ አረፈባቸው ማለት ፈራርሰዋል ማለት ነው። በንግድ ደረጃ ሱቅም በለው ምንም በለው ሁሉም እንዳለ ተጭኗል፤ የህብረተሰቡ ንብረት የለም። የጤና ጣቢያው እና የሆስፒታሉ ማሽኖች በገቡ በሁለተኛው ቀን ነው የተጫነው። ጁንታው የወሰደው። መድሐኒትም ምንም የለም" ሲሉ አቶ መሐመድ የትግራይ ኃይሎችን ፈጸሙት ያሉትን እየጠቀሱ ይከሳሉ።

በመርሳ ከተማ የጦር "መሳሪያ አለ፤ ወይም ይኸ የካቢኔ ቤት ነው" በሚል ጥርጣሬ የትግራይ ኃይሎች ዘረፋ መፈጸማቸውን አቶ ሰይድም ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በሐይቅ እና በውርጌሳ መካከል በምትገኘው ውጫሌ የተባለች አነስተኛ ከተማ ሰላማዊ ሰዎች በትግራይ ኃይሎች ተገድለዋል የሚል መረጃ ዶይቼ ቬለ ከአራት የተለያዩ ሰዎች አግኝቷል።

ላሊበላ እና ወልድያን የመሳሰሉ የአማራ ክልል ከተሞች በአሁኑ ወቅት በትግራይ ኃይሎች ቁጥጥር ሥር ይገኛሉ። በትግራይ የተጀመረው ጦርነት ወደ አማራ ክልል ከተስፋፋበት ካለፈው ሐምሌ ወዲህ የትግራይ ኃይሎች በተቆጣጠሯቸው አካባቢዎች ግድያዎች፣ ዘረፋዎች እና የንብረት ውድመት መፈጸሙን ከከተሞቹ የሸሹ ነዋሪዎች ይናገራሉ። ዶይቼ ቬለ ተፈጸሙ የተባሉ ግድያዎች እና ዘረፋዎችን በራሱ ለማረጋገጥ አልቻለም። የህወሓት ቃል አቀባይ የሆኑት አቶ ጌታቸው ረዳን በጉዳዩ ላይ ለማነጋገር ያደረገው ጥረትም አልተሳካም።

ማብቂያ ያጣው ውጊያ ግን አቶ መሐመድ ሰይድ እንደሚሉት የመርሳ እና የአካባቢውን ሕዝብ ሕይወት ወደ ኋላ መልሷል። በከተማው መብራት የለም፣ ውኃም የለም። በመርሳ የሚገኙ ሰዎች የሚያስፈልጓቸውን መድሐኒቶች ለማግኘት የሚችሉበትም ዕድል እጅግ ጠቧል።

አቶ መሐመድ ሰይድ "ውጫሌ የምትባል መከላከያ የነበረባት ከተማ አለች። እስከዚያ ትሔድና ከዚያ ከውጫሌ መርሳ ርቀቱ 30 ኪሎ ሜትር ነው። ያንን 30 ኪሎ ሜትር ወጣቱ በእግር ነው የሚወስደው። ቤተሰብ እዚያ ካለህ መድሐኒቱን ገዝተህ በእግር ይዘህ ትሔዳለህ። ከጊዜ በኋላ ግን ይኸም ነገር ቆመ፤ ታገደ። አሁን እዚያ ያለው ሕዝብ መድሐኒት ይጠቀም የነበረው መድሐኒት ተቋርጦበታል። በቃ [ያለው ምርጫ] የመሞቺያውን ጊዜ መጠበቅ ነው ማለት ነው" በማለት የተፈጠረውን ገልጸዋል።

ጦርነቱ በትግራይ፣ አማራ እና አፋር ክልሎች ብርቱ ሰብዓዊ እና ምጣኔ ሐብታዊ ቀውስ ፈጥሯል። እስካሁን ተዋጊዎቹ መቋጫ ሊያበጁለት፤ ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በሚያደርገው ጫናም ማስቆም ተስኖታል።ምስል Ben Curtis/AP/picture alliance

ከመርሳ ተፈናቅለው በሐይቅ ከተማ የሚገኙት አቶ ከድር አሰፋ ለመኖሪያ ቤት ግንባታ የሚያገለግሉ የኤሌክትሪክ እና የኮርኒስ ግብዓቶች ነጋዴ ነበሩ። ለጊዜው ከትውልድ ቀያቸው መርሳ በቅርብ ርቀት ላይ የሚገኙ ቢሆንም "ይኸ ጦርነት አልቆ" አገራቸው የሚገቡበትን ቀን ይናፍቃቸዋል። የንግድ ሥራቸው ቆሟል፤ ሰራተኞቻቸው ተበትነዋል። የደረሰው "ጉዳት አንድ ሁለት ብለህ የምትዘረዝረው አይደለም" የሚሉት አቶ ከድር የወሎ ገበሬ የገጠመው ፈተና ያንገበግባቸዋል፤ የሚመጣው ያሰጋቸዋል። መልስ ማግኘት ያለመቻላቸው ተስፋ ያስቆርጣቸዋል።

"ከተማ ላይ ያለውን ማህበረሰብ ተወው። የገጠሩ ማህበረሰብ ለአመት ይበቃኛል ያለውን እህል አጥቶ የሁለተኛ አመት የመኸር ስብሰባው ሊወድም ጫፍ የደረሰበት ማህበረሰብ ነው። ይኸን ለማን አቤት ትለዋለህ? የእከሌ ጥፋት ነው እከሌ በደለኝ…ማንም ላይ ጣት ልትጠቁምበት የምትችለው ነገር አይደለም። ለዚህ ነገር ኃላፊነት ሊወስድ የሚገባው ሰው መጥቶ ሊያነጋግርህ የሚችልበትም ሰዓት አይደለም። የገጠሩ ሕዝብ በጣም ያሳዝናል። አርሶ ሌሎች ማህበረሰቦችን ይመግባል የሚባል ማህበረሰብ ትንሽ እርዳታ ሰጥተኸው [ልታኖረው] አትችልም። አታኖረውምም" ሲሉ ሥጋታቸውን ለዶይቼ ቬለ አጋርተዋል።

በተለይ የወሎ ገበሬ እና ማሳ የገባበት ቅርቃር ዶይቼ ቬለ ያነጋገራቸውን የአካባቢው ሰዎች በኃይል ያሰጋ ጉዳይ ነው። ገበሬ በውጊያ ምክንያት በመፈናቀሉ አረም እና ኮትኳቶ የሚሹ ሰብሎች ተመልካች አጥተዋል የሚል ሥጋት በተደጋጋሚ ይደመጣል። ውጊያው መፍትሔ ካጣ ሰብል በጊዜ የመሰብሰቡ ጉዳይም ብዙዎችን የሚያብሰለስል ጉዳይ ነው።

ዶይቼ ቬለ ለዚህ ዘገባ ባነጋገራቸው አስራ አራት ሰዎች ዘንድ የሥጋት እና ተስፋ መቁረጥ ድምጸት ይሰማል። ቁጭት አለ። "የእኛ አገር ጥጋበኛ ፖለቲከኛ በተራገጠ ቁጥር ረሐብተኛ ገበሬ የሚጠቀጠቅበት አገር ነው። ይኸን ስል ለማንም ግድ የለኝም። ምክንያቱም የእኛ አባቶች፣ እኔ፣ የእኔ ወንድሞች የማንንም ወንበር የማንንም ሥልጣን አንፈልግም። የምንፈልገው ቀያችን ሰላም ሆኖ አርሰን፣ ዘርተን መኖር ነው። እዚያ ውስጥ የመግባት አይደለም ያን የማየት እንኳ ፍላጎት የሌለው ማህበረሰብ ነው እየተገረፈ ያለው" የሚሉት አቶ ከድር  "ችግሩን እና የደረሰበትን ልቁጠርልህ ብል በአገሬ ሰው እና በራሴ ላይ የቀለድኩ ስለሚመስለኝ የችግር አይነቶችን ልዘረዝርልህ አልችልም" ሲሉ ተናግረዋል።

እሸቴ በቀለ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW