1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

«ብልህ ሰው በገዛ ሀገሩ ጦርነት አይከፍትም» ወርቅነህ ሥዩሜ

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ጥቅምት 15 2017

ወርቅነህ ሥዩሜ በጀርመን ኑርንበርግ ከተማ ነዋሪ ብቻ ሳይሆን መጤዎች ከሀገሪቷ ዜጋ ጋር ተዋሕደው እንዲኖሩ የሚሠራ የከተማዋ ምክር ቤት አባልም ነው። « ለ6 ዓመት የሚቆይ የምክር ቤት አባል ነኝ። እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አፍሪቃን ወክዬ እየሠራሁ ነኝ። » ይላል።

Workineh Siyoume - Integrationsrat Mitglied aus Nürnberg
ምስል Privat

«ብልህ ሰው በገዛ ሀገሩ ጦርነት አይከፍትም» ወርቅነህ ሥዩሜ

This browser does not support the audio element.

የጎርጎሮሲያኑ 2015 ዓ ም ከአንድ ሚሊዮን በላይ ተገን ጠያቂዎች ወደ ጀርመን የተሰደዱበት ዓመት ነበር ። ከነዚህም መካከል 75 000 ያህሉ 18 ዓመት ያልሞላቸው ፣ ብቻቸውን ወደ ጀርመን የተሰደዱ ህፃናት እና ወጣቶች ነበሩ። ምንም እንኳን አብዛኞቹ ስደተኞች ከሶርያ እና ኢራቅ የተሰደዱ የነበረ ቢሆንም ቁጥራቸው ትንሽ የማይባል አፍሪቃውያንም ነበሩ። ከእነዚህ አንዱ ወርቅነህ ሥዩሜ ነው። «እጅግ ብዙ ፈተናዎች አሉት። እኔ ከቤተሰብ ጋር አልመጣሁም ። ብቻዬን ነው ወደዚህ የመጣሁት። በሀገር ቤት ከልጅነቴ አንስቶ ለ 15 ዓመት ትምህርት ቤት ነው የነበርኩት። »

በወቅቱ የ24 ዓመቱ ወጣት ብዙ ነገሮችን ከዜሮ መጀመር ነበረበት። በተለይ ጀርመን በስደተኞች በተጨናነቀችበት ዓመት ወደ ጀርመን በመምጣቱ ፈተናው ብዙ ነበር።
«ከሕግ አንፃር መንገዶቹ ክፍት አልነበሩም። ለአምስት ዓመታት መሥራትም ሆነ እንቅስቃሴዎች የተገደቡ ነበር። ግን ያስፈልገኛል ብዬ ያሰብኩትን፤ ቋንቋ በመማር እና ትምህርት ነክ ነገሮች ላይ አሳለፍኩ። »
በወቅቱ የነበሩት የጀርመን መራሒተ-መንግሥት አንጌላ ሜርክል የሚጎርፈው የስደተኛ ብዛት ቢያስደነግጣቸውም « እንችላለን።» ወይም « እንወጣዋለን» ሲሉ ነበር ሕዝባቸውን ሊያረጋጉ የሞከሩት።  ወርቅነህም ወቅታዊውን ፈተናዎች አልፎ እና በድል ተወጥቶ በአሁኑ ሰዓት በተለያዩ በጎ አድራጎት እና ፖለቲካ ነክ ስራዎች ውስጥ ተሳታፊ ሊሆን ችሏል። «የበጎ ፍቃድ ሥራ ደስ ይለኛል። ኢትዮጵያ እያለሁ ያንን ባላደርግም ያስደስተኝ ነበር። እና  ወደዚህ ሀገር ስመጣ በደስታ ነው ይህንን ሥራ የጀመርኩት።»
ወርቅነህም ጀርመን ሀገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ይጠቅማል ብሎ ባሰበው የበጎ ፍቃድ ሥራ ላይ አተኮረ። ከዚህም ዋንኛ የሚለው የትምህርት ጉዳይ ነው።
«ወደዚህ የሚመጡ ስደተኛ ወጣቶች ለብዙ ችግሮች የተጋለጡ ስለሆኑ እንዴት ወደፊት መጓዝ ይችላሉ በሚለው ላይ መስራት ጀመርኩ። ከዚህ በተጨማሪ እዚህ የተወለዱ ህፃናትን የሚጠቅም ትምህርት ነክ ነገር ጀመርኩ»

በበርሊን አይሮፕላን ማረፊያ ጊዜያዊ የስደተኞች መጠለያምስል Jochen Eckel/picture alliance

ዛሬ የ33 ዓመት ወጣት የሆነው ወርቅነህ  ከኢትዮጵያ ማህበረሰብ አልፎ በሚኖርበት የጀርመን ኑርንበርግ ከተማ መጤዎች ከሀገሪቷ ዜጋ ጋር ተዋሕደው እንዲኖሩ የሚሠራው የኢንቲግሬሽን ወይም የውሕደት ምክር ቤት አባል ነው።  «ምክር ቤቱ ሕዝብ ነክ፤ ሕግ ነክ፤ ፖለቲካ ሐሳቦች ላይ ያተኮረ ምክር ቤት ነው። በ2022 ዓም ምርጫ ነበር። ተመረጥኩ። ለ6 ዓመት የሚቆይ የምክር ቤት አባል ነኝ። እኔም እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ አፍሪቃን ወክዬ እሠራለሁ። »

«እዚህ ስኖር በታላቅ ደስታ ነው»

ወርቅነህ የሚኖርባት ኑርንበርግ ከተማን እጅግ እንደሚወዳት ለሌሎች ከሚያጋራቸው መረጃዎች መረዳት ይቻላል። ከተማዋ ልዩ ናት የሚልበትንም ምክንያት ገልፆልናል።
«እዚህ ስኖር በታላቅ ደስታ ነው። ኑርንበርግ ከተማ በተለያየ ታሪክ ትታወቃለች። ከ1000 ዓመት በፊት የተመሰረተች ከተማ ናት። ከፖለቲካ አንፃር ዋናዎቹ የዓለም ጦርነቶች ከዚህ ከተማ ነው ተነስተው የተስፋፋው። ግን ቢሆንም ሕዝቡ የሥራ ሕዝብ ስለሆነ ይህ ሁሉ ነገር ሲያልፍ ከተማቸውን፣ አካባቢያቸውን የመስራት አቅም እና ጉልበት ስለነበራቸው በደንብ ሰርተው አስቀምጠዋታል። » ወርቅነህ ወደ ጀርመን ከመጣበት ጊዜ አንስቶ በተለያዩ የበጎ ፍቃድ አገልግሎቶች በተለይም በመጤ ማህበረሰብ እና የህፃናት ትምህርት ላይ  መስራቱ  ከተለያዩ ተቋሟት የእውቅና ሽልማቶች እንዲያገኝ ምክንያት ሆኗል። የተለያዩ አጫጭር የትምህርት ኮርሶችንም ወስዷል።

ኑርንበርግ ከተማምስል Norbert Probst/imageBROKER/picture alliance


ወርቅነህ ከ3000 በላይ ተከታዮች ባሉት የፌስቡክ ገፁ «መሣሪያ ገዳይ ነው እንጂ መፍትሔ አይደለም። ጦርነት ይብቃ» የሚል መልዕክት አስፍሯል። መልዕክቱ ለማን ነው? እሱም እንዲህ ሲል ምላሽ ሰጥቷል።« መሣሪያን በየጊዜው እየገዙ፣ እየሸጡ፤ እየገደሉ እንደዚህ አይነት ነገሮችን የሚያደርጉ አካላት በተለያዩ ሀገራት ላይ አሁን ላይ አሉ። የታሪክ ጦርነት አለ። የኃያልነት ጦርነት አለ።እንደዚህ አይነት ጦርነትን የሚፈልጉ ሰዎች ራሳቸውን ከዛ እንዲቆጥቡ ነው። ማንም በዛ ተጠቃሚ እንደማይሆን ግልፅ ነው። ብልህ ሰው በገዛ ሀገሩ ጦርነት አይከፍትም። ለማን ነው ለሚለው? ማንም ቢሆን ይህ ነገር ውስጥ ላሉ አካሎች ነው። »

ጀርመን ሀገር ውስጥ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ደግሞ ወርቅነህ ማድረግ አለባቸው የሚለው ፦«ማንም ሰው በተለያየ መንገድ ወደዚህ ሀገር ሊመጣ ይችላል። እዚህ ሀገር ውስጥ ግን ለመኖር ራሱን መቻል አለበት። ለዛ ራሱን መስጠት፤ ትምህርት መማር ፤መስራት ያለበት መስራት አለበት። ችግር ሲመጣ ብቻ ተፍ ተፍ ከሚሉ ቢዘጋጁ፤ ከዚህ ሌላ ደግሞ ወንጀል ጀርመን ውስጥ ቀይ መስመር ነውና ከወንጀል ቢርቁ የሚል ሀሳብ አለኝ።»

ልደት አበበ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW