1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በአማራ ክልል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 21 2017

በአማራ ክልል በተከታታይ እየጣለ ያለው ከባድ ዝናብ በሰብል ላይ ጉዳት እያደረሰ እንደሆን አርሶአደሮች ተናገሩ። አንድ የአየር ትንበያ ባለሙያ «ዝናቡ ለሳምንት ይቀጥላል» ብለዋል።

አማራ ክልል ዝናብ
በአማራ ክልል ከባድ ዝናብ ከዚህ ቀደምም ጉዳት አድርሷል ፎቶ ከማኅደር ምስል Hanna Demisse/DW

በአማራ ክልል ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በሰብል

This browser does not support the audio element.

 

ካለፈው ሳምንት ጀምሮ በአማራ ክልል አንዳንድ አካባቢዎች እየጣለ ያለው ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በደረሱ ስብሎች ላይ ጉዳት እያስከተለ መሆኑን ነው አርሶ አደሮች ለዶይቼ ቬሌ የገለፁት። ዝናቡ ባልደረሱ ሰብሎች ላይ ቢሆንም ከሚፈለገው በላይ እንደበዛበት ነው አርሶስደሮች የሚናገሩት። ከወቅታዊ የክልሉ ፀጥታው ጋር ተዳምሮ ሰብል መሰብሰቡ በአካባቢያቸው ፈተና መሆኑን ነው አንድ የሰሜን ጎጃም አርሶአደር ያመለከቱት።

ዝናብና የፀጥታ ችግር በሰብል አሰባሰብ ላይ ጉዳት እያስከተለ ስለመሆኑ

ወቅቱ በጣም አስቸጋሪ መሆኑን የሚገልፁት አርሶ አደሩ፣ ያልተሰበሰበው ጤፍ እየረገፈ መሆኑና የተሰበሰበውም ቢሆን በዝናቡ ጉዳት እየደረሰበት እንደሆን ተናግረዋል። አልፎ አልፎ በአካባቢው የሚታየው ጦርነትም ለሰብል ስብሰባው ሌላ ፈተና መሆኑን አመልክተዋል።

ባለፈው ዓመት ከፍተኛ ድርቅ በነበረበት ሰሜን ጎንደር አንድ አርሶ አደር ሰሞኑን ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ በመስክ ላይ ያለችውን አነስተኛ ሰብል መሰብሰብ አላስቻለም ብለዋል።

በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳድር ዳህና ወረዳ አርሶአደር በክረምቱ ወራት በጎርፍና በመሬት መንሸራተት በወረዳው ከፍተኛ ጉዳት መድረሱን ጠቁመው፣ አሁን ደግሞ ወቅታዊ ያልሆን ዝናብና ወቅታዊው የክልሉ ሰላም ሁኔታ በሰብል ስብሰባ ላይ ጫና እየፈጠረ እንደሆን ተናግረዋል።

«... ባለፈው ዓመት ዝናብ ከፍተኛ ጉዳት አድርሶብናል፣ የመሬት መንሸራተት፣ ማዕበል፣ ጉዳት ደርሶብናል፣ ከዚያ የተረፈውን ደግሞ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ከጥቅም ውጪ አድርጓቸዋል።» ነው ያሉት። ከነገ ዛሬ ጦርነት ይነሳ ይሆን? በሚል ኅብረተሰቡ በስጋት ላይ እንደሆነም ተናግረዋል።

በተለይ ሜዳ ላይ ለመሰብሰብ የተዘጋጀ ጤፍ ጉዳት እየደረሰበት እንደሆን የባሕር ዳር ዙሪይ አርሶአደር ገልጠዋል።

በአማራ ክልል የኢትዮጵያ ሜቴሬዎሎጂ ቢሮ ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ዝናቡ ከጥቅሙ ጉዳቱ ያመዝናል

በረዶ ጭምር እየጣል እንዳል የነገሩን እኚህ አርሶ አደር የሚወርደው ዝናብ ከጥቅሙ ጉዳቱ እንደሚያመዝን ተናግርዋል። ከከባድ ዝናብ በኋላ ፀሐይ ሲወጣም የጤፉ ፍሬ በከፍተኛ ሁኔታ እየረገፈ መሆኑንም አክለዋል።

በክልሉ ያለው ወቅታዊ የሰላም ሁኔታም ለሰብል መሰብሰብ ሌላው እንቅፋት መሆኑን ነው አርሶ አደሮቹ ያመለከቱት። ያለው ጦርነት በሰብል ስብሰባ ላይ ጫና መፍጠሩንም ገልጥዋል። «ገንዘብ ከፍለው የሚያሳጭዱ ሰዎች የተኩስ ድምፅ ሲሰሙ ከስጋት አኳያ ጥለው ይሄዳሉ» ነው ያሉት።

«ዝናቡ በቀጣዩ ሳምንትም ይቀጥላል» ባለሙያ

የምዕራብ አማራ ሚቲዎሮሎጂ አገልግሎት ማዕከል የትንበያ ባለሙያና ተመራማሪ አቶ መልካሙ በላይ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ሰሞኑን የጨመረበትን ምክንያት ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል።

እሳቸው እንደሚሉት ወቅታዊ ያልሆነ ዝናብ መነሻው በሜዲትራኒያንና በቀይ ባሕር አካባቢ የተፈጠረ የባሕር ወለል ሙቀት መጨመርና ያን ተከትሎ ቻይናና ዙራያው ያሉ አካባቢዎች ወደ ኢትዮጵያ የሚመጣውን ቀዝቃዛ ነፋስ እንዳያልፍ አድርጎታል። በዚህም ምክንያት እርጥበት ያለው ቀዝቃዛ ነፋስ ደግሞ ከኮንጎናከሰሜን ህንድ ውቅያኖስ ወደ አማራና ማዕከላዊ ኢትዮጵያ ስለሚገባ ወቅቱን ላልጠበቀ ዝናብ መፈጠር ምክንያት መሆኑን አመልክተዋል።

ዝናቡ በተለይም በቆላማ አካባቢዎች በደረሱ ሰብሎች ላይ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመው፣ ዝናቡ በቀጣዩ ሳምንትም ሊቀጥል እንደሚችል የትንበያ መረጃዎች እንደሚያሳዩ አስረድተዋል።  

ባለፈው ዓመት በአማራና በሌሎች አንዳንድ  ክልሎችም የነበረው ከፍተኛ ዝናብ በፈጠረው የመሬት መንሸራተት፣ ናዳና ጎርፍ የብዙ ሰዎች ሕይወት ማለፉ፣ ንብረት መውደሙና በዙዎችም መፈናቀላቸው ይታወሳል።

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW