1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስ

በዴንጊ የተጠቁ በሽተኞች በመተማ እና ሁመራ ተገኝተዋል

ረቡዕ፣ መስከረም 23 2011

በመላው ዓለም በበርካታ ሀገራት በስፋት የሚታየው የዴንጊ ትኩሳት በኢትዮጵያ እምብዛም ስሙ ሲነሳ አይሰማም። በቅርቡ የተደረገ ጥናት ግን በሽታው በሰሜን ኢትዮጵያ ባሉት በመተማ እና ሁመራ መታየቱን አመልክቷል። በአካባቢው በሽታውን እንደ ወባ የመውሰድ ችግር እንዳለ ጥናቱን በዋነኛነት ያካሄዱት የጎንደር ዩኒቨርስቲ ምሁር ይናገራሉ።

Mosquito Mücke
ምስል picture-alliance/AP Photo/J. Miller

በዴንጊ የተጠቁ በሽተኞች በመተማ እና ሁመራ ተገኝተዋል

This browser does not support the audio element.

ወባ መሰል በሽታ ነው። በርካቶችን ለአልጋ በሚዳርግባቸው በእስያ፣ ደቡብ አሜሪካ እና ምዕራብ ፓስፊክ ባሉ ሀገራት በከፍተኛ የጤና ችግርነት ተመዝግቧል። በመላው ዓለም ደግሞ በዓመት እስከ 390 ሚሊዮን ሰዎች በበሽታው እንደሚለከፉ በጉዳዩ ላይ የተደረገ አንድ ጥናት ጠቁሟል። በበሽታው ተጋላጭነት ላይ የተደረገ ሌላ ጥናት ቁጥሩን ከሚሊዮን ወደ ቢሊዮን ያሻግረዋል። እንደ ጥናቱ ከሆነ  በ128 ሀገራት ለበሽታው የመጋለጥ አደጋ የተደቀነበት ህዝብ 3.9 ቢሊዮን ይሆናል። 
ከዓለም ህዝብ ግማሽ ያህሉን ሊያጠቃ ይችላል የሚባልለት ይህ በሽታ ዴንጊ ፌቨር ይባላል።

በጎንደር ዩኒቨርስቲ በሜዲካል ማይክሮ ባዮሎጂ ትምህርት ክፍል መምህር የሆኑት አቶ ጌታቸው ፈረደ ስለበሽታው ምንነት ያስረዳሉ። “ትኩሳት የሚያመጣ በሽታ ነው። እና ትኩሳቱ በጣም ከፍ ይላል። ምልክቶቹ ከወባ ጋር ተመሳሳይ ናቸው። ትኩሳት በዋናነት ሆኖ ማንቀጥቀጥ፣የመገጣጠሚያ ቦታዎች ህመም፣ ማቅለሽለሽ [ይኖራል]። እነዚህ ደግሞ በወባም በሌሎችም በሽታዎች የሚታዩትን ነው እርሱም የሚያሳየው እና ብዙም በምልክት መለየት ከባድ ነው፤ አይቻልም። ምንድነው የሚለየው? ወባ ሰውየው ተመርምሮ ወባ ከሌለበት፣ ትኩሳት የሚያመጡ ብዙ በሽታዎች አሉ ከእነዚያ ውስጥ ነጻ ከሆነ፣ የራሱ መመርመሪያ መሳሪያ አለ በዚያ መመርመሪያ ፖዘቲቭ ከሆነ እርሱ ሊሆን ይችላል። በምልክት መለየት አይቻልም” ይላሉ አቶ ጌታቸው። 

ምስል DW/A.Bacha

ዴንጊ ፊቨር በመላው ዓለም በፍጥነት እየተስፋፋ የመጣ በሽታ ነው ቢባልም ከጎርጎሮሳዊው 1970 ዓ. ም. በፊት ግን በወረርሽኝ መልኩ የተከሰተባቸው ሀገራት ዘጠኝ ብቻ እንደነበሩ የዓለም ጤና ድርጅት መረጃ ያሳያል። በሽታው በስፋት ይታይባቸዋል በሚባሉት በደቡብ አሜሪካ፣ ደቡብ ምስራቅ እስያ እና ምዕራብ ፓስፊክ ባሉ ሀገራት እንኳ የዛሬ 10 ዓመት የተመዘገበው ይፋዊ የበሽታው ቁጥር 1.2 ሚሊዮን ብቻ ነበር። ከሦስት ዓመት በፊት በተደረገ ጥናት ይህ ቁጥር በሦስት እጥፍ ጨምሮ ተገኝቷል።

የዓለም ጤና ድርጅትን የመሳሰሉ ተቋማትን እያሳሳባቸው ያለው የቁጥሩ እንዲህ በፍጥነት መመደንግ ብቻ ሳይሆን ከዚህ ቀደም በሽታው ወዳልታየባቸው ሀገራት መስፋፋቱ ነው። ከዓመታት በፊት በሽታው አይደለም በኢትዮጵያ በአፍሪካ ደረጃም ይሄን ያህል የሚወራለት አልነበረም። ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን በሽታው በአህጉሪቱ እዚህም እዚያም ይታይ ይዟል። የዛሬ ሁለት ዓመት በቡርኪናፋሶ በተቀሰቀሰ የዴንጊ ወረርሽኝ ከአንድ ሺህ የሚልቁ ሰዎች በበሽታው ተጠቅተዋል ተብሏል። በኢትዮጵያም በተመሳሳይ ወቅት በድሬዳዋ እና ሶማሌ ክልል ወረርሽኞች መከሰታቸውን የናሙና ምርመራ ውጤቶች አመላክተዋል። አቶ ጌታቸው የምርመራ ውጤቶቹ የታተመበትን ጥናት ተመልክተውታል። 

“እኔ እንዳየሁት ወረርሽኝ ተነስቶ በጣም ከፍተኛ ትኩሳት ያለባቸው በሽተኞችን ሪፖርት ተደረጉ። ሪፖርት ሲደረግ እዚያ ከድሬዳዋ ላይ ምክንያታቸው ያልታወቁ ግን ብዙ በሽተኞች ታመዋል። ከዚያ ምንድነው የተደረገው? ለብሔራዊው የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት (EPHI) ናሙናው ተላከ። ናሙናውን ልከው ትኩሳት አምጪ የሆኑ ብዙ ተዋህሲያንን መርምረዋል። ወባን ጨምሮ፣ ታይፎይድ፣ የሎው ፊቨር አይነት ብዙ በሽታዎችን መርምረዋል። መርምረው እዚያ ላይ ያገኙት ምንድነው? ዴንጊ መሆኑን ሰርተው አረጋግጠዋል። ያ ነው እንግዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ ሪፖርት የተደረገው” ሲሉ የጥናቱን ውጤት ያስታውሳሉ። 

በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎች በሽተኞች ከፍተኛ ትኩሳት ኖሯቸው፣ ወባም ሆነ ሌላ በሽታ በምርመራ ሳይገኝባቸው ሲቀር፣ “ምክንያታቸው ያልታወቀ” በሚል መግለጫ ሲቀመጥ አቶ ጌታቸው ታዝበዋል። የጎንደር ዩኒቨርስቲው መምህር በሌሎች በሽታዎችን ላይ ከባልደረቦቻቸው ጋር ጥናቶች ባደረጉባቸው የመተማ እና ሁመራ አካባቢዎችም ተመሳሳዩን አስተውለዋል። የከፍተኛ ትኩሳቱ መንስኤ ዴንጊ ፊቨር ሊሆን እንደሚችል ከቀደምት ንባቦቻቸው የተረዱት አቶ ጌታቸው እና ባልደረቦቻቸው በመተማ እና ሁመራ ሆስፒታሎች በተሰበሰቡ 600 ናሙናዎች ላይ ተመርኩዘው ጥናት ለማድረግ ተነሱ።  

ምስል picture-alliance/dpa/G. Amador

“እኛ ያጠናነው አካባቢ ላይ ስናየው ብዙ ጊዜ በሽታ አምጪ ያልታወቁ ተዋህሲያን ግን ትኩሳት የሚያመጡ በሽታዎች እንዳሉ ከዚህ በፊት ባጠናነው ላይ አወቅን። ከዚያ ወባ ይሆን ብለን ፈተሽን። ወባን አላገኘንም። ግን በሽተኞቹ  ትኩሳት አላቸው። ወባም ከሌለ፣ ከዚህ በፊት ካደረግነው ጥናት እዚያ አካባቢ በብዛት የሚገኙት እንደ ካላዛርም ከሌላቸው፣ ከዚህ ተነስተን ምን ሊሆን ይችላል? ብለን ሀገር አቀፍ ጋርም፣ ዓለም ጋርም አያይዘን ደግሞ ይህ በሽታ ሊሆን ይችላል የሚል ግምት ስለነበረን በዚያው ዲዛይን አድርገን ውጤት አግኝተናል” ይላሉ አጥኚው። 

የእነ አቶ ጌታቸው ጥናት ውጤት እንደሚያመለክተው በመተማ ከተመረመሩት ናሙናዎች መካከል አርባ በመቶው የዴንጊ ፊቨር ተገኝቶባቸዋል። ከሁመራ ናሙናዎች ደግሞ 27.5 በመቶ ለበሽታው መጋለጣቸውን በጥናታቸው ደርሰውበታል። ዘጠኝ አጥኚዎች የተሳተፉበት ይህ ጥናት በግንቦት 2010 ዓ ም በሳይንስ መጽሔቶች (ጆርናሎች) ላይ ታትሟል። አጥኚዎቹ ጥናቱን በሚያካሂዱበት ወቅት ካስተዋሉት ነገር አንዱ ዴንጊ ፊቨር በበሽታነት እንኳ ያለመታወቁ እውነታ ነው።  

“መመርመሪያ ስለሌለ እርሱን ጭራሽ የሚገምተው የለም። ለምንድነው የሚገምተው የሌለው? ከዚህ በፊትም ሪፖርት  ብዙም የለም። በ«National Guideline» ላይም የተካተተ አይደለም። አካባቢው ላይ ቃለ መጠየቅ ስናደርግ፣ ዴንጊ ምናምን ስንል ሙያተኞቹ ጭምር ምንድነው ይሄ በሽታ ሲሉ ነበር። እንደዚህ አይነት በሽታ አለ እንዴ? ሲሉን ነበር። እና ሙሉ ለሙሉ እንደዚህ አይነት case የለም ተብሎ ነበር የሚታወቀው” ሲሉ በአካባቢው የተመለከቱትን ያጋራሉ። 

“የእስያ እና የደቡብ አሜሪካ በሽታ ይባል የነበረው ዴንጊ ፊቨር በአፍሪካ ሊያውም በኢትዮጵያ እንዴት ሊገኝ ቻለ?” በሚል የተጠየቁት አቶ ጌታቸው “ምክንያቱን በትክክል ለማወቅ ተጨማሪ ዝርዝር ጥናቶች ያስፈልጋል” የሚል ምላሽ ይሰጣሉ። በሽታው በጎረቤት ሀገራት ጭምር እንደታየ የሚናገሩት ጥናት አድራጊው ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ ያሏቸውን ያስቀምጣሉ።

“በአሁኑ ጊዜ ከአየር ንብረት ለውጥ  እና ከከተሞች መስፋፋት ጋር ተያይዞ እንደ ወባ ትንኝ አይነት የበሽታ አምጪ ተዋህሲያን በቀላሉ እንዲራቡ ያደርጋል። ለምሳሌ በአሁኑ ጊዜ ያው በኢትዮጵያ ውስጥ ከተሞቹ እየተስፋፉ ነው። ከእነኚህ መስፋፋት ጋር ተያያዞ በቀላሉ እርጥበት፣ ውሃ የመሳሰሉ ለወባ ትንኞች መራቢያ ምቹ ነገሮች ይፈጥራል። ያ ነገር ደግሞ ምን ያደርጋል? እነኚህ ዴንጊ ፊቨር የሚባለው በሽታ አምጪ ተዋህሲያን በቀላሉ እንዲራቡ የሚያስችሉ ምቹ ሁኔታዎችን ይፈጥራል። እና በዚያ በተባሉት ቦታዎች ላይም የአየር ንብረቱም ቆላማ ነው። ለወባ ትንኟ ምቹ ነው። እነኚህ ነገሮች ነው ሊሆኑ የሚችሉት። ለወደፊቱ ደግሞ ምንድነው ምክንያቱ የሚለውን ደግሞ ቀጥለን የምናጠናው ይሆናል” ይላሉ።

ምስል DW/A.Bacha

በዴንጊ ፊቨር ላይ የሚደረገው ቀጣዩ ጥናት አሁን በመካሄድ ላይ እንደሆነ አቶ ጌታቸው ይናገራሉ። በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ይጠናቀቃል ተብሎ የሚጠበቀው ይህ ጥናት ከዚህ ቀደም ከተደረገው ዘርዘር እና ሰፋ ያለ እንደሚሆን ይገልጻሉ። ጥናቱ ከአራቱ የበሽታው አይነቶች የትኞቹ በኢትዮጵያ እንደሚገኙ ለማወቅ እንደሚረዳ እና በሽታውን ለመከላከል ወደፊት ለሚደረገው ጥረት አንድ መነሻ ሊሆን እንደሚችል ያስረዳሉ።

እስከ ሞት ሊያደርስ ለሚችለው ዴንጊ ፊቨር ፍቱን መድኃኒት እስካሁን ባይገኝም ተመራማሪዎች ግን የመከላከያ ክትባት መስራታቸውን አስታውቀዋል። ክትባቱን ያመረተው ዓለም አቀፍ ኩባንያ መድኃኒቱ ተጠቃሚዎች ዘንድ እንዲደርስ ለገበያ ያወጣው የዛሬ ሁለት ዓመት ግድም ነው። የዓለም ጤና ድርጅትም በሽታው አዘውትሮ በሚከስትባቸው ሀገራት መድኃኒቱ ጥቅም ላይ መዋል እንደሚችል አዎንታዊ አስተያየቱን ሰጥቷል። በ20 ሀገራት እውቅና እና ፍቃድ የተሰጠው ይህ ክትባት ከዘጠኝ እስከ 45 ዓመት ላሉ ሰዎች የሚሰጥ እንደሆነ ተገልጿል።

ለመሆኑ ዴንጊ ፊቨር እስከ ሞት ሊያደርስ የሚችለው ምን ሲፈጠር ነው? “አራት serotype አሉት። ከአራቱ serotype በአንዱ ከተያዘ በራሱ የመዳን ዕድል አለው። አንዳንዶች ላይ ምልክት ሙሉ ለሙሉ ላያሳይ ይችላል። ሌሎች ላይ ደግሞ ምልክት ያሳያል። አራት serotype አሉ። serotype 1፣ serotype 2፣ serotype 3፣ serotype 4 የሚባሉ አሉ። እና በሽታውን አደገኛ የሚደርገው ምንድነው? አንድ ሰው በመጀመሪያ serotype የተያዘ ሰው ደግሞ በሁለተኛው ጊዜ በሌላ serotype በሚያዝበት ጊዜ በሽታው ወደ ከፍተኛ ደረጃ ወደ ሞት ሊያደርስ ይችላል” ይላሉ አቶ ጌታቸው። 

ተስፋለም ወልደየስ 

አዜብ ታደሰ 
  
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW