ወባ በሽታን በደረቅ አካባቢ ሳይቀር የምታሰራጨው ትንኝ
ማክሰኞ፣ ጥቅምት 29 2015
የወባ በሽታን በደረቅ እና ሞቃት አካባቢዎች ሳይቀር የምታሰራጨው ትንኝ በሽታው የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ የሚደረገውን ጥረት ሊያደናቅፈው እንደሚችል እየተነገረ ነው። ከሰሞኑ የወጣ አንድ ጥናት ከዚህ በፊት አፍሪቃ ውስጥ ትኖራለች ተብላ የማትገመት የወባ አይነት ጅቡቲ ላይ መገነቷን አመልክቷል። ሕንድ እና ኢራን አካባቢ በብዛት የምትገኘው ወባ አስተላላፊ ትንኝ በከተሞችም ሳይቀር ወባን ልታስፋፋ እንደምትችል ተጠቁሟል።
ድሬደዋ አንድ ወቅት የወባ ስርጭትን መቆጣጠር መቻሏ ሲነገርላት ነበር። ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን ያንን የስኬት ታሪኳን የምትጋፋ ወባ አስተላላፊ ትንኝ በጅቡቲ በኩል ሳይመጣባት እንዳልቀረ ነው በወባ ምርምር በርከት ላሉ ዓመታት የሠሩት ዶክተር ፍፁም ግርማ ያስረዱን። በጤና ጥበቃ ሥር የሚገኘው እና የተለያዩ ምርምሮች የሚያካሂደው የአርማወር ሀንሰን የምርምር ተቋም ውስጥ ወባን የተመለከተውን ጥናት የሚያከናውነው ዶክተር ፍፁም የሚመሩት ቡድን የደረሰበትን አዲስ መረጃ ባሳለፍነው ሳምንት ሲያትል ዩናይትድ ስቴትስ ላይ ተገኝተው ለዓለም ይፋ አድርገዋል። ጥናሩ አፍሪቃ ውስጥ ወትሮ መኖሯ ያልታወቀው የወባ ትንኝ ከጅቡቲ አልፋ፣ ቀብሪደሀር ብሎም ድሬደዋ መገኘቷን አመላክቷል።
ይህ የወባ ትንኝ ድሬደዋ ውስጥ ለታየው የወባ ታማሚ ቁጥር መጨመረ ምክንያት መሆኑን በተግባር መረጋገጡንም ነው በዘርፉ ምርምር ለሚያደርጉ አካላት ያሳወቁት። የሚገኝበትን በተመለከም ወትሮ ከሚታወቀው የወባ ትንኝ ይለያል ነው የሚሉት ዶክተር ፍፁም። «ወትሮ የሚታወቀው የወባ ትንኝ በእርጥበት ወቅት የሚከሰት ሲሆን አዲሱ በደረቅ ወራትም በከተሞች ሳይቀር ይከሰታል።» አንፊነስ ስቴፈንሳይ የሚል ስያሜ ነው የተሰጠው ለአፍሪቃ እንግዳ የተባለው የወባ ትንኝ። ሕንድ እና ኢራን አካባቢ በብዛት መኖሩ የሚታወቀው ይህ የወባ ትንኝ አይነት ጅቡቲ ብቻ ሳይሆን ሌሎች የአፍሪቃው ቀንድ ሃገራት ውስጥም ተገኝቷል። ይህም የወባ ታማሚዎች ቁጥር እንጨምር ምክንያት መሆኑ ታይቷል። እነ ዶክተር ፍፁም ባካሄዱት ጥናትም ይኽ ተረጋግጧል።
ኢትዮጵያ ውስጥ የወባ ጊዜ ተብለው የሚታወቁት ወራት የዝናቡን ወቅት ተከትለው የሚመጡት ጥቅምት ኅዳር ወራት ናቸው። አሁንም በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የወባ ታማሚዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑ ይነገራል። አንፊነስ ስቴፈንሳይ የተባለችውን የወባ ትንኝ ለየት የሚያደርጋት በደረቅ ወቅትም መከሰቷ ነው።
የወባ ትንኝ እንዳይስፋፋ ይደረግ የነበረው ጥረት ውኃ የሚይዙ አካባቢዎችን ማድረቅ ነበር። በደረቅ ወቅትም በከተማ ሳይቀር የምትራባዋን እንግዳዋን የወባ ትንኝ ለመከላከል ምን ይደረግ? ዶክተር ፍፁም እንደሚሉት በከተሞች አካባቢ ሳይቀr በትንሽም ሆነ በትልቅ ውኃ ማጠራቀሚያ ላይ ክትትል ማድረግ ያስፈልጋል። ክዳን የሚያስፈልገው ክዳን ሊደረግለት ግድ ነው፤ ትናንሽ የሆነውም ሆነ ጥቅም ላይ ውሎ ክፍቱን የሚቀመጥ ውኃ ማጠራቀሚያ ሊወገድ እንደሚገባም ነው ያሉት። ቀደም ብለው የዚህን የወባ ትንኝ የተለየ ባህሪ እንደገለጹት መኖሪያው የከብቶች ማደሪያ ስፍራ በመሆኑ አጎበር ለመኝታ መጠቀምም ሆነ በቤት ውስጥ የሚደረገው የመድኃኒት ርጭት ተጨማሪ ጥንቃቄ እና ክትትል እንደሚያስፈልገውም አጽንኦት ሰጥተዋል።
ኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት ቅርብ ዓመታት የወባ ታማሚዎች ቁጥር እየቀነሰ በተወሰኑ አካባቢዎች ላይም የተጠናከረ የቁጥጥሩ ሥራ እንደሚከናወን ነበር የዘርፉ ባለሙያዎች የሚናገሩት። በያዝነው ዓመት ግን ከወዲሁ የወባ ታማሚዎች ቁጥር በርከት ማለቱን መረጃዎች ያመለክታሉ። በእርግጥ ዶክተር ፍፁም ግርማ ድሬዳዋ ላይ የታየው ለውጥ እና የአዲሱ የወባ ትንኝ ጉዳይ በሌሎች የኢትዮጵያ ክፍሎችም ይሠራል ብሎ ለመናገር ገና ጥናት መደረግ እንዳለበት አጽንኦት ሰጥተዋል። ወባ በበርካታ የአፍሪቃ ሃገራት ዋነኛ የጤና ችግር ነው። በመላው ዓለም በየዓመቱ ከ600 ሺህ ሰው በላይ በወባ ምክንያት እንደሚሞቱ መረጃዎች ያመለክታሉ። ከተጠቀሰው ቁጥር አብዛኛው የሚከሰተው አፍሪቃ ውስጥ ነው። በአዲሱ የወባ ትንኝ ምክንያት የሚጎዱት ሰዎች ቁጥር እንዳይጨምር ሕንድ የምትከተለውን የወባ መከላከያ ስልት መከተሉ እንደሚያዋጣ ነው የተመከረው። ለሰጡን ማብራሪያ ዶክተር ፍፁም ግርማ ታደሰ እናመሰግናለን።
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ