1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

ደቡብ አፍሪቃ፦ ወታደራዊ የጋራ ትብብር

ቅዳሜ፣ የካቲት 11 2015

ደቡብ አፍሪቃ፤ ሩስያ እና ቻይና ሕንድ ውቅያኖስ ላይ ከትናንት ዓርብ ጀምሮ ለዐሥር ቀን የሚቆይ የጋራ ጦር ልምምድ ለማድረግ ተስማምተዋል። ሁኔታው በምዕራባውያን ዘንድ አልተወደደም። በእርግጥ ደቡብ አፍሪቃ የቆመችው የት ጋር ነው የሚል ጥያቄም በምዕራባውያኑ ዘንድ መነሳት ጀምሯል።

Südafrika | Gemeinsames Marinemanöver mit China und Russland
ምስል፦ Chen Cheng/Photoshot/picture alliance

የደቡብ አፍሪቃ፤ ሩስያና ቻይና ጦር ልምምድ

This browser does not support the audio element.

ደቡብ አፍሪቃ፤ ሩስያ እና ቻይና ሕንድ ውቅያኖስ ላይ ከትናንት ዓርብ ጀምሮ ለዐሥር ቀን የሚቆይ የጋራ ጦር ልምምድ ለማድረግ ተስማምተዋል። ሁኔታው በምዕራባውያን ዘንድ አልተወደደም። በእርግጥ ደቡብ አፍሪቃ የቆመችው የት ጋር ነው የሚል ጥያቄም በምዕራባውያኑ ዘንድ መነሳት ጀምሯል።

የሩስያው «አድሚራል ጎርሽኮቭ» የጦር መርከብ ደቡብ አፍሪቃ ኬፕ ታውን ወደብ ደርሶ መልኅቁን ከጣለ ቀናት ተቆጥረዋል። የጦር መርከቡ ላይ ሁለት ፊደላት በጉልኅ ይነበባሉ። የላቲኑ «ዜድ» እና «ቪ» ኆኄያት። እነዚህ ፊደላት የሩስያ ጦር በዩክሬን ግንባር ያሰማራቸው የጦር መሣሪያዎች ላይም የተጻፉ ናቸው። ፊደላቱ የሩስያ «የአርበኝነት» ተምሳሌት ሆነው የሚያገለግሎ ናቸው ሲል አሶሺየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

ሩስያ ዩክሬንን የወረረችበት ቀን ደግሞ ድፍን አንድ ዓመቱን ሊሞላ ከአንድ ሳምንት በታች ቀርቶታል። በዚህ ወሳኝ ጊዜም ነው ሦስቱ ሃገራት በደቡብ አፍሪቃ የሕንድ ውቅያኖስ የባሕር ጠረፍ ላይ በጦር ልምምድ ተፍ ተፍ ማለት የተያያዙት። የጦር ልምምዱ ተሳታፊ ሃገራት ራሷ ደቡብ አፍሪቃ፤ ሩስያ እና ቻይና ናቸው።

የሩስያ «አድሚራል ጎርሽኮቭ» የጦር መርከብ ከኬፕታውን ከተማ ወደ ደርባን ስታቀናምስል፦ AFP/Getty Images

«ዳግማይ ሞሲ» (Mosi II) በሚል የተሰየመው የጋራ የጦር ልምምዱ ከትናንት ዓርብ ጀምሮ ለዐሥር ቀናት እንደሚቆይም ተዘግቧል። የጋራ የጦር ልምምዱ የሚደረግበት ጊዜ ሩስያ ዩክሬንን የወረረችበት አንደኛ ዓመት በሚሞላበት ጊዜ መሆኑ ለምዕራባውያን መልእክት አለው። ምንም እንኳን ስለቀኑ መገጣጠም የደቡብ አፍሪቃ መንግሥት ያለው ባይኖርም ለዓለም አቀፉ ግጭት ጥናት ተቋም (Crisis Group) የመርኃ ግብር ምክትል ኃላፊዋ ፖሊን ባክስ ግን ሁኔታው «አሳፋሪ» ነው።

«ልክ በዩክሬን ጦርነት አንድ ዓመት ላይ መሆኑ እጅግ አሳፋሪ ነው። ምዕራባውያን ዲፕሎማቶችን አስቆጣ አልልም፤ ይልቁንስ በጣም እንዳሳሰባቸው ነው የገለጡት። እናም ደቡብ አፍሪቃ የት እንደቆመች ማወቅ ይፈልጋሉ።»

በርካታ የምዕራባውያን ዲፕሎማቶች ደቡብ አፍሪቃ ከሩስያ እና ከቻይና ጋር የምታደርገው የጋራ የጦር ልምምድ የደቡብ አፍሪቃን ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚያስገባ ነው ይላሉ።

በእርግጥ የደቡብ አፍሪቃ የውጭ ጉዳይ ሚንስትሯ ናሌዲ ፓንዶር የሩስያ የዩክሬን ወረራን አውግዘው ነበር። የደቡብ አፍሪቃ ፕሬዚደንት ሲሪል ራማፎዛ ግን የውጭ ጉዳይ ሚንስትራቸው ከውግዘት ተግባራቸው እንዲቆጠቡ አስገድደዋል። ያም ብቻ አይደለም የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሠርጌይ ላቭሮቭን ጥር ወር ውስጥ ተቀብለው እንዲያነጋግሩም አስደርገዋል።

የሩስያ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሠርጌይ ላቭሮቭ እና የደቡብ አፍሪቃ የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ናሌዲ ፓንዶርምስል፦ Siphiwe Sibeko/REUTERS

በእርግጥ ደቡብ አፍሪቃ ከሩስያ ጋር ግንኙነቷን እንዲህ የማጠናከሯ ምሥጢር ታሪካዊ ዳራም አለው። ሞስኮው የደቡብ አፍሪቃው የነጻነት ታጋይ ቡድን (ANC)ጸረ አፓርታይድ ትንቅንቅ በሚያደርግበት ዘመን ከነበረው ድጋፍም ጋር የተገናኘ ነው። ሁለቱም መንግሥታት የዓለም አቀፉ ሥርዓት አሁን ያለንበትን እውነታ የሚያንጸባርቅ አይደለም በሚለው ይስማማሉ። እናም መንግሥታቱ «ይበልጥ የኃይል ክፍፍል ሊኖር ይገባል» ብለው እንደሚያምኑ በደቡብ አፍሪቃ የፕሪቶሪያ ዩኒቨርሲቲ የዓለም አቀፍ ፖለቲካ መምህር ፕሮፌሰር ጆ-አንሲ ፋን ቪይክ ተናግረዋል።  ደቡብ አፍሪቃ የፀጥታው ምክር ቤት ቋሚ አባል ከሆኑት ሩስያ እና ቻይና ጋር ወዳጅነቷን ከማጠናከርም በላይ ሌሎች ሃገራትን ጨምሮ ሦስቱ በሚገኙበት ቡድን ውስጥም አባል ናት።

«የመጨረሻው ነጥብ ምንድን ነው፤ ሩስያ፤ ሕንድ፤ ቻይና እና ብራዚል ያሉበት BRICS ምሥረታ ላይ ነን። እነዚህ ደቡባዊ የዓለም ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሃገራት የምእራባውያን ተገዳዳሪ ኃይል ለመመሥረት እየሞከሩ ነው።»

ይህ በእንግሊዝኛ ምኅጻሩ ብሪክስ የተሰኘው ቡድን ሲመሰረት የጋራ የንግድ ትስስርን ለማጠናከር ያለመ መድረክ ነበር። እነዚህ በዓለማችን የኃይል አሰላለፍ ሚዛን ብቅ ብቅ ያሉ ሃገራት የዓለም የኃይል አሰላለፍ የበላይነትን መገዳደርም ጀምሯል። የክራይሲስ ግሩፗ ፖሊን ባክስ ምዕራባውያን ሌላ እውነታ መኖሩን አፍሪቃውያንም አማራጭ እንዳላቸው መገንዘብ ተስኗቸዋል ባይ ናቸው።

«በርካታ የአፍሪቃ ሃገራት የተለያዩ አጋሮች እንዳላቸው ሊሰማቸው ይችላል። የግድ አንዱን ወገን መምረጥ አይገባቸውም። የዩክሬን ጦርነት የፈጠረው ችግር ምእራባውያን ሃገራት አፍሪቃውያን አንድ ወገን ይመርጣሉ በሚል አስበው አለመሆኑ ነው።»

ለኔልሰን ማንዴላ የደቡብ አፍሪቃ የውጭ ፖሊሲ የሰብአዊ መብቶች ፖሊሲ ነበር ምስል፦ Getty Images/AFP/A. Joe

እናም «የአፍሪቃ መንግሥታት እና የአፍሪቃ ሃገራት የራሳቸውን ውሳኔ ማስተላለፍ እንደሚችሉ ምዕራባውያን ሊገነነዘቡ ይገባል» ሲሉም አጥኚዋ አክለዋል። በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የድምፅ አሰጣጥ ወቅትም ይህንኑ በተደጋጋሚ ሲያንጸባርቁ ይስተዋላሉ። የደቡብ አፍሪቃ በድምፅ አሰጣጡ ወቅት ለምዕራባውያኑ ትብብር መንፈጓን ፕሮፌሰር ጆ-አንሲ ፋን ቪይክ «ዕድል እንዳመለጣት» አድርገው ነው የሚያዩት።

«በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ድምፅ ተሰጥቷቸው የጸደቁ በርካታ ውሳኔዎች ብንመለከት በወረራ ወቅት እና በሉዓላዊ ሃገራት ላይ በሚፈጸሙ ዓለም አቀፋዊ የሰላም ስጋቶች ላይ ዓለም አቀፉን ሕግ በግልፅ የሚደግፉ ናቸው። እናም በእኔ እይታ ደቡብ አፍሪቃ ቀድሞ የነበራትን የሞራል አቅጣጫ የማስጠበቁ እድል አምልጧታል።»

ደቡብ አፍሪቃ ከሩስያ እና ቻይና ጋር የምታደርገው ትብብር እንደ ፕሮፌሰር ጆ-አንሲ ፋን ቪይክ ከሆነ ከምዕራባውያን ዘንድ ዋጋ የሚያስከፍል ነው።  «ደቡብ አፍሪቃ የጓሮ ፖለቲካ ስለምትከተል»ም አሉ ፕሮፌሰሯ፦ «ከምዕራባውያን ዘንድ ርዳታ ይቀንስባታል።» ደቡብ አፍሪቃ አንድ ቀን ምናልባት ዩናይትድ ስቴትስ በዋናነት ከምትዘውረው የዓለም ባንክ ድጋፍ ብትፈልግ እጅ ሊያጥራት ይችላል ሲሉም ፕሮፌሰሯ ስጋታቸውን ገልጠዋል።

በእርግጥ በዓለም ባንክ የተቀፈደዱ በርካታ ሃገራት ነጻ ነን ቢሉም ነጻነታቸው ግን በብዙ መልኩ የተገፈፈ መሆኑ በየጊዜው የሚታይ ሐቅ ነው። የሆነ ሆኖ ለዘመናት ወደ አንድ ወገን አጋድሎ የነበረው የዓለም የኃይል አሰላለፍን ለመገዳደር በጋራ የተሰለፉ ሃገራት ተጽዕኗቸው ብርቱ በመሆን ላይ ነው።

ማንተጋፍቶት ስለሺ/ክርስቲና ክሪፓል

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW