1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ኪነ ጥበብ

ወንጀል ተፋላሚዎቹ

ማክሰኞ፣ ታኅሣሥ 24 2010

ወንጀል ተፋላሚዎቹ! አዲስ ተከታታይ ድራማ ጽሑፍ በፌስ ቡክ። በፈጣን የሴራ ፍሰት፥ በአጫጭር ትእይንቶች የተገነባው ድራማ በአይነቱ ለየት ያለ ነው። ይኽ የድራማ ጽሑፍ በዶይቸ ቬለ የአማርኛው ክፍል የፌስቡክ ገፅ የሚቀርብ ሲኾን፤ ለሽልማት ያበቃል። ትእይንቶቹ ከታች ይገኛሉ። ስለ ተሳትፎ እና ውድድሩ ደግሞ ፌስቡክ ገጻችን ላይ በዝርዝር ሠፍሯል።

09.2015 Crime Fighters MQ amharisch

የመሬት ቅርምቱ (ገቢር 1 ትዕይንት 1)

ምሬቱ እጅግ አይሏል። ነዋሪዎች በገዛ ሀገራቸው ባይተዋር፤ በመሬታቸው የውጭ ዜጋ ተቀጣሪዎች መሆናቸው አንገሽግሿቸዋል። ከአበባ እርሻው ተቀጣሪዎች መካከል በተለይ ዘሪሁን አንገፍግፎታል።

«ወይኔ ሰውዬው! ስማ አምባዬ፤ እኔ እንደዚህ አይነት ሕይወት ሰልችቶኛል። እዚህቺው የቆምንባት መሬት ላይ የራሳችን እርሻ የምናርስ፤ እሸት ከጓሮ፤ ከብትም ከበረት የነበረን ሰዎች ነበርን።  የራሳችን ጌቶች እንጂ የማንም ተቀጣሪ አልነበርንም። አሁን ግን ይኸው እንደ ባሪያ የሚያየን የአንድ የውጭ ዜጋ ተቀጣሪዎች ሆነን አርፈነዋል።»

«ዘሪሁን፤  አንተ ደግሞ እንዲሁ ያለፈ ነገር ማመንዠክ ትወዳለህ።»

በቢሊዮን ዶላር ገቢ የሚዘወረው «ሮዝስ ኢንተርናሽናል» ጽጌሬዳ አምራች የውጭ ኩባንያ መጠነ-ሰፊ የእርሻ መሬቶችን ከአካባቢው ነዋሪዎች በግዢ መልክ ወስዷል፤ የሀገሬው ነዋሪዎችን አፈናቅሎ መሬታቸውንም ተቀራምቷል ማለቱ ይቀላል። መንግሥት ለንግድ ተግባር በሚል ሰበብ የዚህ አካባቢ ነዋሪዎችን በግዳጅ አፈናቅሏል።

«ኧረ ነቃ በል አምባዬ! እየተፈጸመ ያለው አይታይህም እንዴ? እሺ የአካባቢያችን መሪ አለቃ አውላቸው የታሉ? ታፍነዋል። የደረሱበት ሳይታወቅ ይኸው ሳምንት አለፋቸው። ይሄ ለምን ኾነ?»

«እኔ ምን ዐውቃለሁ!»

«ዐየህ፤ መሬታችን ለ‘ሮዝስ ኢንተርናሽናል‘ መሰጠቱን በመቃወማቸው ነው አፍነው የወሰዷቸው።»

«አንተ ሰው ዛሬ ምን ነካህ? ‘ሮዝስ ኢንተርናሽናል‘ ወዲያው መጥፋታቸው እንደተሰማ አይደል እንዴ መግለጫ ያወጣው። አብደኻል እንዴ?»

«አዎ፤ እብድም፦ ብቻ የፈለግኸውን በለኝ። ምን እየተብላላ እንደኾነ ግን አንድ ቀን ይገለጥልሃል።»

«በል በል አሁን ዝም ብለህ ጽጌሬዳህን ቅጠፍ። ሆ! ደግሞ ጣጣ እንዳታመጣብንና እኛኑ እንዳታስቀጥፈን።»

*** 

የመሬት ቅርምቱ (ገቢር 1 ትዕይንት 2)

የአካባቢው የጎሣ አለቃ ደብዛቸው እንደጠፋ ነው። ከልብ ይሁን የይስሙላ መንግሥትም የአቶ አውላቸው ያለመገኘት ጉዳይ ያሳሰበው ይመስላል። ካፊቴሪያ ውስጥ ዘካሪያስ ቡናውን ፉት እያለ ዘና ለማለት ሲሞክር፤ በእድሜ ጠና ያሉት አቶ ግዛቸው ግን ተጨናንቀዋል።

«ዘካሪያስ፤ ይልቅ ቀበቶህን ጠበቅ አድርገህ አለቃ አውላቸው ያሉበትን ለማጣራት ሞክር። የሀገሪቱ የደህንነት ኃላፊ እንደመሆንህ መጠን ይህን ጉዳይ ቅድሚያ ልትሰጠው ይገባል። በዛ ላይ ፕሬዚዳንቷ የአውላቸው ደብዛ መጥፋት ጉዳይ በአፋጣኝ  እልባት እንዲያገኝ ትፈልጋለች።»

«አቶ ግዛቸው ደግሞ ከመቼ ጀምረው ነው ሴት ልጅን ቁም ነገር ብለው መስማት የጀመሩት?»

«አንተ! መሪያችንን ነው እንዲህ የምትዘረጥጥ?  ወይ ድፍረት! በዛ ላይ ሰው ሊሰማን ይችላል።»

«ስጋት አይግባዎ አቶ ግዛቸው! የሀገሪቱ የስለላ ኃላፊ እኔው ነኝ። ሽማግሌውን ሠማይ ቤትም ቢሆን ካለበት ቦታ አመጣዋለሁ። ብፈልግ ፕሬዚዳንቷ በየትኛው ጎኗ እና ከማን ጋር እንዳደረችም ማወቅ እችላለሁ። ስለዚህ ይረጋጉ።»

«ለመሆኑ ሽማግሌው በሕይወት አለ ብለህ ታምናለህ?»

«እንዴ? ምን አይነት ጥያቄ ነው? አሁን የ80 ዓመት ሽማግሌን ለመግደል የሚያስብ ሰው ይኖራል ብለው ነው?»

«እህ ብለህ ስማኝ አንተ! አለቃ አውላቸው ከቅኝ ገዢዎች ጋር በተደረገ ፍልሚያ  የጀግንነት ክብር የተጎናጸፈ ሰው ነው።  ስለዚህ ይህ ሰው አንድ ነገር ቢሆን ሕዝቡ ምን ሊል እንደሚችል አስብ።»

«አቶ ግዛቸው አይጨነቁ። እኚህን ነፃ አውጪ ጀግና የሚባሉትን ሰው ዱካ፤ ፈልገን እናገኛለን።»

***

የመሬት ቅርምቱ (ገቢር 1 ትዕይንት 3)

መስኩ በተለያዩ የአበባ አይነቶች ተሞልቷል። በአቅራቢያው የተዘረጋው ወንዝ በዝግታ ይንፏለላል። አምባዬና ዘሪሁን በምሳ እቃቸው ቋጥረው የያዙትን ምግብ ለመመገብ የአበባ እርሻው አጠገብ የተዘረጋው አግዳሚ ወንበር ላይ አረፍ ይላሉ።

«እሺ አምባዬ፤ እኔስ ያው ከተለመደው ድንች ቅቅል የተለየ ነገር አልያዝኩም። አንተስ?»

«ስማ ዘሪሁን፤ ምናለ ይኼን ድንች ወደ ስኳር ድንች እድገት እንኳን ቢያሸጋግሩልህ? ሁሌ ድንች! አይሰለችህም?»

«ቀልድ አንተ፤ በል እሺ ምሳ እቃውን ክፈተው።»

አምባዬ የምሳ እቃውን እየከፈተ ያልጎመጉማል። ባዶ የምሳ እቃው ይንኳኳል። ዘሪሁን በምጸት ድምጸት ነው የሚናገረው።

«ምን?! ባዶ የምሳ እቃ ነው ያመጣሁት እንዳትለኝ ብቻ!»

«አንተ ለባዶ ምሳ እቃ ትገረማለህ፤ ባዶ ሆድም ነው እንጂ!»

«በል ና እንግዲህ መቼስ ወደ ስኳር ድንች እድገት አልሸጋገር ያለው ድንች ቅቅሌ አንተንም ነው የሚጠብቀው በለኛ።»

ዘሪሁን የምሳ እቃውን መክፈት ሲጀምር አምባዬ በድንጋጤ ተውጦ አንድ ቦታ ላይ አፍጧል።

«ያንት ያለህ!»

«ኧረ ሰውዬው ግድቡ ጋር እየሰመጠ እኮ ነው!»

ወደ ወንዙ ተሯሩጠው በመሄድ ከግድቡ ውስጥ አንድ ሰው ጎትተው ያወጣሉ። ሁለቱም ትንፋሻቸው ይቆራረጣል።

«ነፍሱ አለች? የሚተነፍስ ግን አይመስልም። አንተ ሆዱ ሁሉ ተነርቷል። እንዴ አምባዬ ምን እያደረግህ ነው? ኧረ ባክህ በጀርባው ገልብጠው!»

«እንዴ! አለቃ አውላቸው?!»

አምባዬ እና ዘሪሁን የሚያከብሯቸውን የአለቃ አውላቸው ሰውነትን እወንዙ ዳር አግኝተዋል። አለቃ በሕይወት ይኖሩ ይሆን? እነአምባዬስ በመቀጠል ምን ያደርጋሉ?

***

የመሬት ቅርምቱ (ገቢር 2 ትዕይንት 1)

አምባዬ እና ዘሪሁን እወንዙ ዳር ቆመው የሚያደርጉት ግራ እንደገባቸው ነው።

«የፈጣሪ ያለህ! ዘሪሁን፤ አለቃ ሞተው ይኾን እንዴ?»

«እኔንጃ አምባዬ!»

«ያም ሆነ ይኽ አለቃ አውላቸውን አግኝተናቸዋል። ያ ማለት ደግሞ መንግሥት አለቃን ላገኘ እከፍላለሁ ያለውን ወሮታ መጠየቅ እንችላለን ማለት ነው።»

አምባዬ በተጎሳቆለች ተተንቀሳቃሽ ስልኩ ለመደወል ይሞክራል። ስልኩ አልሠራ ይለዋል። ዘሪሁን በፍጥነት የራሱን ስልክ ያቀብለዋል። የስልክ ጥሪው ከወዲያኛው ወገን ይነሳል።

«ከፖሊስ ጣቢያ ማዕከል መርማሪ ሙላቱ እባላለሁ። ምን ልታዘዝ?»

«እ… እ… እኛ… ማለቴ… ካልተሳሳትኩ አለቃ አውላቸውን አግኝቻቸዋለሁ።»

«ለማሾፍ ከሆነ የደወሉት ጊዜያችን በከንቱ በማባከን ልንከስዎ እንችላለን። እየቀለዱ ነው…?»

«ኧረ በፍፁም!እየቀለድኩ አይደለም። አምባዬ። አምባዬ እባላለሁ። እውነቱን ለመናገር አለቃ አውላቸው እግሬ ስር ተጋድመዋል።»

«እግሬ ስር ተጋድመዋል? ተጎድተዋል እንዴ? አለቃ ደኽና አይደሉም?»

«ኧኧ፤ እኔንጃ… እኛ… ማለቴ፤ እኔ ከወንዝ ነው ያወጣኋቸው። እና የሚተነፍሱ አይመስለኝም… ሳይሞቱ አልቀሩም። የወሮታውን ገንዘብ…»

«አቶ አምባዬ ፤ እባክዎ አሁን ያሉበትን ይንገሩን እና በፍጥነት ወደ ቦታው እንምጣ። አለቃ መኾናቸውን እንዳረጋገጥን ገንዘቡ ይከፈልዎታል።»

«ቦታው፤ የ 'ሮዝስ ኢንተርናሽናል እርሻ 'ውስጥ፤ እወንዙ አጠገብ ነው። ግድቡ ጋር።»

«ዐወቅኹት። ጥሩ እዛው ይቆዩን። ያው በእጅዎ ምንም ነገር እንዳይነኩ… እና ከማንም ጋርም እንዳይነጋገሩ። ተግባባን?»

«አዎ ግን…»

«ምንም ግን የለም ፤ አሁን ያልኩዎን ያድርጉ!»

የሞባይል ስልኩ ይቋረጣል። አምባዬ እና ዘሪሁን ግራ በመጋባት ይተያያሉ።

 

የፌስቡክ ድራማ ጽሑፉ እስከ ገቢር ስምንት ድረስ ይቀጥላል። እያንዳንዱ ገቢር ሦስት ትእይንቶች አሉት። ትእይንቶቹን ፌስቡክ ገጻችን ላይ ስናወጣ ወደዚህም እናመጣቸዋለን።

 

ከታች የሚገኘው የድራማ ጽሑፍ እላይ ካለው የተለየ ራሱን የቻለ ታሪክ ያለው ሲኾን፤ ለተወዳዳሪዎችም ሽልማት ሰጥተናል። አኹን የምትወዳደሩት ከላይ ባሉት ጽሑፎች ነው።  

______________________________________________________________________________________________________________________

 

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 1 ትዕይንት 1)

አካባቢው በሁከት ተውጧል። ጩኸት በርክቷል። ከርቀት የፖሊስ መኪና ሣይረን እያሰማች ትመጣና ትቆማለች። ሁለት ፖሊሶች ዘለው ይወርዳሉ። በእድሜ ጠና ያሉ ሴትዮ፦ ይርበተበታሉ።

«እዚያ ቤት ሰዎቹ ተራርደውላችኋል። የእንስሳት ሀኪሙ ጎረቤቴ ጳዉሎስን በጩቤ ተከተኩት!»

ሴትዮዋ ለፖሊሶቹ ወደ ሉሲ ይጠቁማሉ። ሉሲ እየሮጠች ነው። አንደኛው መርማሪ ሮጦ ይደርስባትና ሉሲን አፈፍ ያደርጋታል። ሉሲ እጇ በደም ተጨማልቋል። ትንቀጠቀጣለች።

«አላደረኩትም፤ እኔ አይደለሁም፣ እኔ አይደለሁም»

«እሱን ጣቢያ ስንደርስ ትናገሪያለሽ፤ ነይ በይ ቀጥዪ!»

***

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 1 ትዕይንት 2)

ፖሊሶቹ ሉሲን ወደ ጣቢያ ወስደዋታል። መርማሪ ዓለሙ ወንጀሉ በተፈጸመበት ሥፍራ ቆዝሟል። ቀደም ሲል ያየውን ማመን አልቻለም። ሉሲን በደንብ ነው የሚያውቃት። ዕድሜው በሃያዎቹ የሚገመተው ሟች ደግሞ አብሮ አደጉ ነው። ወለሉ ላይ በደም አበላ ተውጦ ተዘርሯል።

«ያንት ያለህ! እንዴት ይዘገንናል!»

መርማሪ ስመኝ እንባ በዐይኖቿ ግጥም ብሏል።

«እንዴት ክፉ ናቸው። ደረቱ ላይ ነው ስለቱን የሻጡበት። »

እንባ ባቆረዘዙ ዐይኖቿ በአካባቢው የምታየውን ነገር በአጠቃላይ እያብራራች በመቅረጸ-ድምጿ ለማስቀረት ትታገላለች።

«ተገቢው መረጃ ከተሰበበ በኋላ አስክሬኑን ወደ አስክሬን ምርመራ ክፍል ልንወስደው ይገባል።»

«ጥሩ! አንቺ ቀጥዪ፡፡ እስከዛው እኔ ደውለው የጠሩንን ጎረቤቶች ላነጋግር፡፡»

***

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 1 ትዕይንት 3)

ፖሊሶቹ የወንጀል ክስተቱን በመመርመር ላይ ባሉበት ወቅት፤ የሟች እህት ሙና ደግሞ በምትሠራበት ሆቴል ውስጥ ነች። የሆቴሉ ሥራ መቀዛቀዝ አበሳጭቷታል። የሥራ ባልደረባዋ ዮዲት አጠገቧ አለች። የእጅ ስልኳ ይጠራል።

«ሄሎ! ሙና ነኝ፤ ማን ልበል ? … ምን? …ጳዉሎስ? …ወይኔ ወንድሜን       

ዮዲት ግራ በመጋባት፦ «ምንድን ነው ሙና

«ወንድሜን ገደሉብኝ! ወንድሜ ተገደለ!»

«ወይኔ እኔ አፈር በበላሁት! እነማን ናቸው?»

ሙና ግንባሯን መዳፎቿ ላይ እንደቀበረች፥ ወለሉ ላይ ተንበርክካ ትንሰቀሰቃለች።

***

ሕገ-ወጥ አዳኞች (ገቢር 1 ትዕይንት 4)

መርማሪ ዓለሙ ወንጀሉን ለፖሊስ የጠቆሙት ወ/ሮ የኔነሽን ፖሊስ ጣቢያ ውስጥ እያናገራቸው ነው። በእድሜ የገፉት የጳዉሎስ ጐረቤት ያዩትን ሁሉ በትክክል እንዲነግሩት ይሻል፡፡

 «እንዴ! የገደለችውማ እሷ እራሷ ነች። ለዚህ አንዳችም ጥርጣሬ የለኝም!»

«በትክክል ስትወጋው ተመልክተዋታል ወይ?» 

«እንግዴህ፤ በመስኮታቸው በኩል አጮልቄ ስመለከት፤ እሱ ወለሉ ላይ የደም ኩሬ ውስጥ ተጋድሟል!  ሚስቲቱ ደግሞ ቢላዋውን እንደያዘች፤ ከበላዩ አንጎንብሳ ትንጎማለላለች!»   

መርማሪ ዓለሙ ወ/ሮ የኔነሽን አሰናብቶ እንዳበቃ ከመርማሪ ስመኝ የስልክ ጥሪ ይደርሰዋል። ጳውሎስ በተገደለበት ቢላዋ ላይ የሉሲ እና የሌሎች ማንነታቸው ያልታወቁ ሰዎች አሻራዎች ተገኝተዋል። ይህ እንዴት ሊኾን ቻለ?  በረዥሙ ተነፈሰ። አኹን በፍጥነት የሉሲን ቃል መቀበል ይኖርበታል።   

***

የድራማውን ቀጣይ ክፍል ማለትም ገቢር 2 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን ቀጣይ ክፍል ማለትም ገቢር 3 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን አራተኛ ክፍል ማለትም ገቢር 4 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን አምስተኛ ክፍል ማለትም ገቢር 5 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም ገቢር 6 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን የመጀመሪያ ክፍል ማለትም ገቢር 7 አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

የድራማውን ቀጣይ ክፍል ማለትም ገቢር 8  አራት ትእይንቶች ይኽን ሲጫኑ ያገኛሉ።

ጀምስ ሙሃንዶ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW