ወደየቀያቸዉ የተመለሱ የትግራይ ክልል ነዋሪዎች የገጠማቸዉ ፈተና
ዓርብ፣ ሚያዝያ 3 2017
ወደቀዬአቸው እንዲመለሱ የተደረጉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የድህንነት ስጋት እየደረሰባቸው መሆኑ የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብት ኮምሽን ገለፀ። ኮምሽኑ ባወጣው የክትትል ሪፖርት እንዳለው ወደ የትግራይ ሰሜን ምዕራብ እና ደቡባዊ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኝ ቀዬአቸው ባለፈው ዓመት መጨረሻ የተመለሱ ዜጎች የድህንነት ስጋት ጨምሮ የተለያዩ ማሕበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ችግሮች እየደረሱባቸው መሆኑ አመልክቷል። ያነጋገርናቸው ተመላሾች በበኩላቸው እስካሁንም የድህንነት ስጋቱ አልተፈታም ብለዋል።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶችኮምሽን የትግራዩ ጦርነት ተከትሎ የተፈናቀሉ ዜጎች ሁኔታ ሲከታተል መቆየቱ የሚገልፅ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ ወደ ቀድሞ ቀዬአቸው እንዲመለሱ የተደረጉ የሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች የሰብአዊ መብት አያያዝ ሁኔታ በትግራይ ሰሜን ምዕራብ እና ደቡባዊ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች የሸፈነ ክትትል ማድረጉ አመልክቷል። ኢሰመኮ ከነሐሴ 19 ቀን እስከ ጳጉሜ 1 ቀን 2016 ዓመተምህረት ድረስ ባደረገው ክትትል መሰረት ያቀረበው ሪፖርት እንደሚለው ባለፈው ዓመት መጨረሻ ወር ወደ አላማጣ እና ኮረም ጨምሮ ወደ ትግራይ ደቡባዊ ዞን የተለያዩ አካባቢዎች እንዲሁም ፀለምቲ እና ማይፀብሪ ጨምሮ ወደ ሌሎች የሰሜን ምዕራብ ዞን አካባቢዎች የተመለሱ ተፈናቃዮች ወደቀዬአቸው ለመመለስ ፈቃደኛ ሆነው መመለሳቸው ይገልፃል።
ወደ አላማጣ ከተማ እና አላማጣ ወረዳ የተመለሱ ተፈናቃዮች የድህንነት ስጋት ያለባቸው በመሆኑ ወደ ቤታቸው ተመልሰው ገብተው ለመኖር አለመቻላቸው፤ እንዲሁም በሰሜን ምዕራብ ዞን ወደ ፀለምቲ፣ ላዕላይ ፀለምቲ እና ማይፀብሪ ከተማ አካባቢዎች እንዲመለሱ የተደረጉ ተፈናቃዮችም እንዲሁ የደህንነት ስጋት ያለባቸው በመሆኑ ለዳግም መፈናቀል መዳረጋቸው የኢሰመኮ ሪፖርት አመላክቷል። ከዚህ በተጨማሪ ኢሰመኮ ይህ ሪፖርቱ አስመልክቶ ያወጣው መግለጫ እንደሚያሳየው ክትትል በተደረገባቸው አካባቢዎች አብዛኛዎቹ ተመላሾች ወደ ስራቸው ያልተመለሱ መሆኑ፣ በሌሎች ስራዎች ተሰማርተው ኑሯቸውን ለመምራት የሚፈልጉ ተመላሾችም በፀጥታ ችግር ምክንያት በነፃነት ተንቀሳቅሰው ለመስራት አለመቻላቸው፣ ምግብ እና ሌሎች መሠረታዊ አቅርቦቶችን በበቂ ሁኔታ የማያገኙ በመሆኑ ተመላሾች ለምግብ እጦት እና ተያያዥ ችግሮች መዳረጋቸው ገልፀዋል ሲል ትላንት ሚያዝያ 2 ቀን 2017 ዓመተምህረት ያወጣው ሪፖርት ያሳያል።
በአሁኑ ወቅት በተጠቀሱት አካባቢዎች ያለው ሁኔታ የገለፁልን ስማቸው እንዲገለፅ ያልፈለጉት በሰሜን ምዕራብ ዞን ዲማ የሚኖሩት እና ባለፈው ሰኔ 26 ቀን 2016 ዓመተምህረት ከተፈናቃይ መጠልያ ወደቀዬአቸው የገቡት ተመላሽ፥ ስንመለስ ድህንነታችን የተጠበቀ እንደሚሆን በፌደራል እና ክልል ባለስልጣናት ተነግሮ የነበረ ቢሆንም የተባለው የድህንነት ጥበቃ የለም፥ በዚህም አስጊ ሁኔታ ላይ እየኖርን ነው ብለዋል።
እንዳንዶች ሁኔታው በመፍራት ዳግም ተፈናቅለው ወደ ሽረ እና እንዳባጉና ያሉ መጠልያዎች የሄዱም አሉ ብለዋል። ከአላማጣ ከተማ ያነጋገርናቸው ሌላው አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው ተመሳሳይ ሀሳብ ይሰጣሉ። ከዚህ በተጨማሪ ችግር ላይ ላለው ተመላሽ የተደረገ ማቋቋሚያ ድጋፍ የለም ሲሉም ያነጋገርናቸው ተመላሾች ገልፀዋል።
ኢሰመኮ የክትትሉን ግኝቶችመሠረት በማድረግ ምክረ ሐሳቦችን ለተለያዩ ባለድርሻ አካላት ያቀረበ መሆኑ የገለፀ ሲሆን ከእነዚህ መካከል ደግሞ፥ ተመላሾች በሚገኙባቸው አካባቢዎች ደህንነታቸው በተሟላ ሁኔታ በዘላቂነት ተጠብቆ የሚኖሩበትን ሁኔታ ዕውን ለማድረግ በተለይም በውይይት እና ዕርቅ ሰላምን የማረጋገጥ ጉዳይ ትኩረት እንዲሰጠው፤ ጉዳት የደረሰባቸውን ተቋማት መልሶ በማቋቋም እንዲሁም አስፈላጊ ግብዓቶችን እና የሰው ኃይል በማሟላት የትምህርት፣ የጤና እና ሌሎች የማሕበራዊ አገልግሎት ተቋማት በአፋጣኝ የተሟላ አገልግሎት እንዲጀምሩ እንዲደረግ፤ ተመላሾች ትተዋቸው የሄዷቸውን ቤት እና ሌሎች ንብረቶች መልሰው የሚያገኙበትን እንዲሁም ለሕይወታቸው የሕግና ፍትሕ ዋስትና የሚያገኙበትን ሁኔታ ለማመቻቸት የሲቪል አስተዳደር እንዲዘረጋ እና የፍትሕ ተቋማት አገልግሎት መስጠት እንዲጀምሩ እንዲደረግ የሚሉ ይገኙበታል ብሏል።
ሚሊዮን ኃይለሥላሴ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ